የአራት ሀገራት የሰብአዊ መብት ተቋማት ስደተኞችን የተመለከተ ጥሪ
Description
የአራት ሀገራት የሰብአዊ መብት ተቋማት ስደተኞችን የተመለከተ ጥሪ
ኢትዮጵያን ጨምሮ የኬንያ፣ የሞዛምቢክ እና የዛምቢያ ብሔራዊ የሰብአዊ መብት ተቋማት የስደት መተላለፊያ የሆኑ የደቡባዊ ቀጣና ሀገራት "መብትን መሰረት ያደረገ" የስደት ፖሊሲዎችን እንዲከተሉ በጋራ ጠየቁ። ብሔራዊ የመብት ተቋማቱ ትናንት በጋራ ባወጡት መግለጫ መንግሥታት ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን፣ የስደተኞች ብዝበዛን፣ ጾታዊ ጥቃትን፣ የዘፈቀደ እሥራትን እና መድልዎን የሚገቱ ጠንካራ ትብብር እና ስምምነት ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል። የመብት ድርጅቶቹ የዓለም አቀፍ የስደተኛ ሰራተኞች እና የቤተሰቦቻቸው አባላት መብቶች ጥበቃ ስምምነትን እንዲያፀድቁ እና እንዲተገብሩም በመግለጫቸው አሳስበዋል። ይህ የተቋማቱ የጋራ አቋም ለስደተኞች ምን ማለት ነው የሚለውን የጠየቅናቸው በዘርፉ ላይ የሚሠሩ ባለሙያ መሰል ጥሪዎች "ስደተኞች ለሚያበረክቱት በጎ አስተዋጽዖ እውቅና የሚሰጥ ነው" ብለዋል።
በምስራቅ አፍሪካአካባቢ መደበኛ እና መደበኛ ያልሆነ ወይም የሕገ-ወጥ ፍልሰት ዋነኛ መነሻ፣ መተላለፊያ ቀጣና የሚባሉት የደቡባዊ ሀገራት ማለትም የኢትዮጵያ፣ የኬንያ፣ የሞዛምቢክ እና የዛምቢያ ብሔራዊ የሰብአዊ መብት ተቋማት ግጭቶች፣ የአየር ንብረት ለውጥ ውጤቶች፣ ኢኮኖሚያዊ እና የመተዳደሪያ ዕድሎች እንዲሁም የተንዛዙ አሠራሮች የሚያስከትሏቸው ችግሮች ስደተኞች የበለጠ አደገኛ መንገዶችን እንዲከተሉ እየገፋፋቸው መሆኑን በአጽንኦት ጠቅሰዋል። እነዚህ ተቋማት "በጥልቅ የሚያሳስበን" ያሉትን የስደተኞች ድንበር ተሻጋሪ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት፣ ብዝበዛ፣ ሕገ-ወጥ ዝውውር፣ ጾታ ላይ የተመሰረተ ጥቃት፣ የዘፈቀደ እስራትን እና መድልዎን ለመግታት ሀገራቱ በትብብር እንዲሠሩ ጠይቀዋል።
ተቋማቱ የየሀገራት መንግሥታት መደበኛ ስደትን በማስተዋወቅ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ፣ ጥቃቶችን በመከታተል ጥሰቶችን እንዲመዘግቡ እና በመብቶች ላይ የተመሰረተ የፍልሰት አስተዳደርን በመቅረጽ እንዲንቀሳቀሱም አሳስበዋል።
መንግሥታት ትርጉም ያለው ግንኙነትን ለማጠናከር፣ ተገቢውን ምላሽ ሊሰጡ ይገባል
የአራቱ ሀገራት የሰብአዊ መብት ተቋማት ትናንት ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀን ሲከበር ባወጡት መግለጫ የስደተኞች ጥበቃ ላይ ትብብርን እና ውይይትን ለማሻሻል መድረኮችን ለመፍጠር እና ለማጠናከር እንዲተባበሩ፣ ከስደተኞች እና ከዋና ባለድርሻ አካላት ጋር "ትርጉም ያለው ግንኙነትን" ለማጠናከር፣ ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጡም ጠይቀዋል። ተመላሽ ስደተኞችን በማገዝ የሚታወቀው አጋር ኢትዮጵያዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር አበራ አደባ ይህ ለፍልሰተኞች ምን ማለት እንደሆነ ጠይቀናቸው ምላሽ ስጥተዋል።
“እንዲህ ያሉ ትብብሮች ከተተገበሩ ለስደተኞች በጎ ውጤት ይኖራቸዋል”
በግጭት፣ በጦርነት፣ በአለመረጋጋት ብሎም በድርቅ እና በኢኮኖሚያዊ ችግሮች ከፍተኛ የስደት እና የመፈናቀል አደጋ የተጋረጠባት ኢትዮጵያ ለብዙ ሕገ ወጥ ስደተኞችመነሻ፣ መሸጋገሪያ እና መድረሻ መሆኗና ይህንንም የመከላከል ሥራ ለማጠናከር ተጨባጭ ሥራ እንደሚያስፈልግ IOM ገልጿል። ድርጅቱ በዓለም ላይ በአሁኑ ወቅት ያለው የፖለቲካ ምህዳር ለስደተኞች አስቸጋሪ ነው ሲልም ከዚህ በፊት አስታውቋል። የአራቱ ሀገራት የመብት ድርጅቶች ባወጡት መግለጫ መንግሥታት ስደተኞችን የተመለከቱ የሁለትዮሽ እና የባለ ብዙ ወገን ስምምነቶችን እንዲመሰርቱ ሲጠይቁ ይህም የጥገኝነት መብትን ያጠናክራል፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን እና ሀገር አልባነትን በከፊል ያስወግዳል የሚል እምነት እንዳላቸው አመልክተዋል።
ስደተኞች የችግር ሁሉ ምንጭ ብቻ አለመሆናቸው
ስደተኞች የማህበረሰቦች ችግሮች ሁሉ ምንጭ ተደርገው ሲወነጀሉ እንጅ የመፍትሄ አካል ተደርገው ሲቆጠሩ አይታይም ያለው IOM ስደት አሁን ድረስ በብዙ ሃገሮች ሥጋት ሆኖ የሚታይ በመሆኑ ለሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ሲል በሌላ ጎኑ ቤታቸውንና ሃብታቸውን ለስደተኞች የሚያጋሩ መልካም ማህበረሰቦች የሚታሰቡበት የማህበራዊ ትስስር ጉዳዮችም ልብ ሊባሉ እንደሚገባ በየጊዜው ይጠቅሳል። የአጋር ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር አበራ አደባም በዚህ ይስማማሉ። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአፍሪካ የሰዎችና ሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን የዓለም የፍልሰተኞች ቀንን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ የአፍሪካ መንግሥታት ፍልሰተኞችን በጅምላ መመለስ እና ማሠር እንዲያቆሙ ጠይቋል። ኮሚሽኑ አክሎም ሀገራት የስደተኞችን የነፍስ አድን ተግባራት እንዲያጠናክሩና የሚሰጡትን ከለላ ከፍ እንዲያደርጉ ጭምር አሳስቧል።
ሰለሞን ሙጬ
አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሠ























