DiscoverDW | Amharic - Newsየኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የማስተማሪያ ሆስፒታሎች በጀት መፈተሽ እንዳለበት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ተናገሩ
የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የማስተማሪያ ሆስፒታሎች በጀት መፈተሽ እንዳለበት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ተናገሩ

የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የማስተማሪያ ሆስፒታሎች በጀት መፈተሽ እንዳለበት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ተናገሩ

Update: 2025-07-02
Share

Description

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥር የሚገኘው የጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን ጨምሮ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የማስተማሪያ ሆስፒታሎች የበጀት አሸፋፈን ሊፈተሽ እንደሚገባ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ተናግረዋል። የገንዘብ ሚኒስትሩ ጉዳዩን ያነሱት ትላንት ማክሰኞ ለ2018 በተዘጋጀው በጀት ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ላነሱት ጥያቄ መልስ በሰጡበት ወቅት ነው።



አቶ ታደሰ ጌጡ የተባሉ የምክር ቤቱ አባል “የማስተማሪያ ሆስፒታሎች ከፍተኛ አገልግሎት እና የማስተማር ሥራ እየሠሩ” ቢሆንም “የትርፍ ሰዓት ክፍያ መክፈል አልቻልንም፤ የማስፋፊያ እና የጥገና ወጪን መሸፈን አልቻልንም። የነጻ ሕክምና አገልግሎት መሸፈን አቻልንም” የሚል አቤቱታ እንዳላቸው ተናግረዋል።



የምክር ቤቱ አባላት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥር የሚገኘውን የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጨምሮ ጎንደር፣ መቐለ፣ ጅማ እና ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ የማስተማሪያ ሆስፒታሎችን ማነጋገራቸውን ለአቶ አሕመድ ሽዴ የገለጹት አቶ ታደሰ “በጀታቸውን በምን መንገድ ነው እያያችሁት ያለ?” ሲሉ ጠይቀዋል።



የኢትዮጵያ መንግሥት የማስተማሪያ ሆስፒታሎች “ጥያቄዎችን በበጀት አስተዳደር” እየደገፈ እንደሚገኝ የተናገሩት የገንዘብ ሚኒስትሩ ይሁንና “ከዘላቂነት አንጻር” ሊፈተሽ ይገባል የሚል አቋም አላቸው። ተቋማቱ በመሠረታዊነት የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል መሆናቸውን የተናገሩት አቶ አሕመድ ነገር ግን ሥራቸውን የሚያከናውኑት “እንደ ዞን ወይ እንደ ክልል ሆስፒታል ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።



ማስፋፊያዎችን ጨምሮ የማስተማሪያ ሆስፒታሎችን “ፌድራል መንግሥት ነው ገንዘብ እየደጎመ ያለው” የሚሉት የገንዘብ ሚኒስትሩ ዘላቂነቱን በተመለከተ “መፈተሽ ያለበት ጉዳይ አለ” ሲሉ አቋማቸውን አስረድተዋል።



“በተወሰነ ደረጃ በእኛ እጅ እስካሉ ድረስ መቀጠል ይኖርብናል” ያሉት የገንዘብ ሚኒስትሩ “ነገር ግን እንዴት ነው ዘላቂነታቸው finance የሚደረገው? የክልሎቹ ሚና ምንድነው? የፌድራል መንግሥት ሚና ምንድነው? የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ሆነው ብቻ መቀጠል አለባቸው ወይ? ወይ ክልሎቹ መረከብ አለባቸው ወይ?” የሚለው ጉዳይ መፈተሽ እንዳለበት ገልጸዋል።



የገንዘብ ጥያቄ የሚነሳው ግን በዩኒቨርሲቲዎች ሥር ለሚገኙ የማስተማሪያ ሆስፒታሎች ብቻ አይደለም። አቶ ተስፋዬ ባንጉ የተባሉ የምክር ቤቱ አባል የወላይታ ዩኒቨርሲቲ የዳውሮ ተርጫ ካምፓስ “እጅግ በጣም የዘገየ፤ ከመጠን በላይ ኪሳራ ውስጥ የገባ ተቋም እንደሆነ” ተናግረዋል።



“ዘንድሮም የተመደበው በጀት ያሉ ችግሮችን የሚቀርፍ ሆኖ አላገኘሁትም” ያሉት አቶ ተስፋዬ “የተገነቡ ግንባታዎች በሙሉ እየፈረሱ ነው፤ እየወደሙ ነው፤ በልዩ ትኩረት የሚፈቱበት ሁኔታ ቢኖር” ሲሉ ለአቶ አሕመድ ጥያቄ አቅርበዋል።



የዳውሮ ተርጫ ካምፓስ የሚገኝበት ወላይታ ዩኒቨርሲቲ ለሚቀጥለው ዓመት 1.9 ቢሊዮን ብር ገደማ ለመደበኛ ወጪ ተመድቦለታል። ከዚህ ውስጥ 159 ሚሊዮን ብር ገደማ የሚሆነው ከራሱ ከዩኒቨርሲቲው ሊሰበሰብ የታቀደ ነው። ዩኒቨርሲቲው ለካፒታል ወጪ 850,000,000 ብር ተመድቦለታል። ይህ የዩኒቨርሲቲውን መደበኛ እና ካፒታል በጀት ድምር ወደ 2.8 ቢሊዮን ብር ገደማ ያደርሰዋል።



በትምህርት ሚኒስቴር ሥር ከሚገኙ 47 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል ከፍተኛ በጀት የተመደበው ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው። ዩኒቨርሲቲው ለሚቀጥለው ዓመት በመደበኛ ወጪ 4.1 ቢሊዮን ብር እንዲሁም በካፒታል ወጪ አንድ ቢሊዮን ብር በድምሩ ብር 5.1 ቢሊዮን ብር ተመድቦለታል።



ለዩኒቨርሲቲው ከተፈቀደው መደበኛ ወጪ ወደ 1.6 ቢሊዮን ብር የሚሆነውም በራሱ የሚሸፈን ነው። ጎንደር ዩኒቨርሲቲ 3.9 ቢሊዮን ብር፣ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ 3.7 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ጅማ ዩኒቨርሲቲ 3.5 ቢሊዮን ብር ለመደበኛ እና ካፒታል ወጪ ተመድቦላቸዋል።



መንግሥት ለሚቀጥለው ዓመት ለትምህርት ዘርፍ በአጠቃላይ 114.7 ቢሊዮን ብር ገደማ መድቧል። በመገባደድ ላይ በሚገኘው የ2017 በጀት ዓመት የትምህርት መደበኛ እና ካፒታል ወጪ 79.3 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን የብር የምንዛሪ መዳከም ጫና እንዳለ ሆኖ 44 በመቶ ገደማ ጭማሪ አሳይቷል።





ከ2018 መደበኛ እና ካፒታል በጀት በቢሊዮን ብር ከፍተኛው መጠን የተመደበላቸው 10 ዩኒቨርሲቲዎች





ከ2018 የትምህርት በጀት 71 ቢሊዮን ብር ለመደበኛ ወጪ የተቀረው 43.7 ቢሊዮን ብር ገደማ ደግሞ ለካፒታል ወጪ የተደለደለ ነው። ይህ በጀት ለትምህርት ሚኒስቴር፣ የቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት፣ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት እና የትምህርት እና ስልጠና ባለስልጣን የተመደበውን ያጠቃልላል። በትምህርት ሚኒስቴር ሥር ለሚገኙ 47 ዩኒቨርሲቲዎች ለመደበኛ እና ካፒታል ወጪ በጠቅላላ የተመደበው 106 ቢሊዮን ብር ገደማ ነው።



የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ “ዩኒቨርሲቲዎቹ የሚጠበቅባቸውን ያደርጋሉ አያደርጉም፤ የተከፈቱበት ምክንያት ከፍተኛ ትምህርትን ከማዳረስ ነው ወይስ ሌላ ፖለቲካዊ ምክንያት አለው የሚለው እንዳለ ሆኖ” ኢትዮጵያ ብዙ ዩኒቨርሲቲዎች በማቋቋሟ “ሳንወድ በግድ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ወደ እነሱ መመደብ አለብን” ሲሉ ይናገራሉ።



የአፍሪካ የኢኮኖሚ ጥናት ኮንሰርቲየም (AERC) ባልደረባ አቶ ሐብታሙ ግርማ ኢሕአዴግ በብልጽግና ፓርቲ ከመተካቱ በፊት አብዛኞቹ ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ ላይ የነበሩ በመሆናቸው “ከአጠቃላይ በጀት ከ10 እስከ 15 በመቶ ይወስዱ ነበር” ሲሉ ይናገራሉ። አሁንም በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ያልተጠናቀቁ ግንባታዎች እና “በጣም አስቸኳይ የሆኑ ካፒታል ኢንቨስትመንቶች” መኖራቸውን የገለጹት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ተመራማሪው “ከዚያ ውጪ በአብዛኛው የሥራ ማስኬጃ ወጪ ነው ያለው” ይላሉ።



የተማሪዎች ምግብ፣ የትራንስፖርት፣ የነዳጅ እና የጽህፈት መሳሪያዎችን ጨምሮ “የሥራ ማስኬጃ ወጪው ደግሞ በአብዛኛው በዋጋ ግሽበት በጣም የተጠቃ ስለሆነ ባለፉት ዓመታት” መጨመሩን አስረድተዋል። አቶ ሐብታሙ “በሀገር ላይ ጫና ያመጣው በፊት በካፒታል ኢንቨስትመንት ላይ በነበረው ጊዜ የነበረው ጫና አይነት ነው። አልቀነሰም” ሲሉ ተናግረዋል።



በተያዘው በጀት ዓመት ትምህርት፣ መንገድ፣ ጤና፣ ግብርና፣ ውኃ እና ኢነርጂ እንዲሁም ከተማ ልማት ከኢትዮጵያ ጠቅላላ በጀት 34 በመቶ ድርሻ ነበራቸው። ይህ ለ2018 በተዘጋጀው እና ነገ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ይጸድቃል ተብሎ በሚጠበቀው በጀት ያለው ድርሻ ወደ 25.2 በመቶ ዝቅ ብሏል።



“በዩኒቨርሲቲዎች ያሉ ፕሮጀክቶች በርካታ ከመሆናቸውም በላይ” “ለማጠናቀቅ የሚያስፈልገው በጀት ከፍተኛ” እንደሆነ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ሰነድ ያሳያል። በዚህም ምክንያት “በቀጣይ በጀት አመት ለሚካሄዱ ነባር ፕሮጀክቶች ብቻ አስፈላጊው በጀት እንዲመደብ” መደረጉ በሰነዱ ሠፍሯል።



“በከፍተኛ ትምህርት ረገድ ካሁን በኋላ የምናወራው ስለ ሥራ ማስኬጃ ወጪ ነው። ምክንያቱም ግንባታዎች ቆመዋል። ከሞላ ጎደል ዩኒቨርሲቲዎች ተሠርተው አልቀዋል” የሚሉት አቶ ሐብታሙ መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎችን እየደጎመ መዝለቅ አይችልም የሚል አቋም አላቸው።



ዩኒቨርሲቲዎች ለመምህራን ክፍያ፣ ለምግብ፣ የጽህፈት መሣሪያዎችን ለመሳሰሉ ግብዓቶች የሚያወጡት እና ተማሪዎቻቸውን የሚያስከፍሉት ቢሰላ ከፍተኛ ልዩነት እንደሚኖረው የሚናገሩት የኢኮኖሚ ባለሙያው አሁን ባለው አሠራር መቀጠል “ዘላቂ አይደለም” የሚል አቋም አላቸው። የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ነጻ “ቢሆን ማንም አይጠላም። ነገር ግን አሁን ካለው ሁኔታ ጋር የሚሔድ አይደለም” ሲሉ አስረድተዋል።



በዋናነት ማስተማር እና ምርምር ማካሔድ የሚጠበቅባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ኃላፊነታቸውን ምን ያክል ተወጥተዋል በሚለው ረገድ ከፍተኛ ትችት ይቀርብባቸዋል። በተለይ በቅርብ ዓመታት የተመሠረቱ ዩኒቨርሲቲዎች በመምህራን እና በተመራቂዎቻቸው ብቃት ረገድ ብዙ ሥራ ይጠብቃቸዋል። ዶክተር አብዱልመናን በተለይ እርሳቸው በተካኑበት የፋይናንስ እና የኢኮኖሚ ዘርፍ “ለረጅም ዘመን የረባ ጽሁፍ ከሀገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አይወጣም። አብዛኛው ምርምር የሚወጣው ውጪ ሀገር ካሉ ተቋማት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።



የኢትዮጵያ መንግሥት አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች መመሥረት አቁሟል። ከዚህ በኋላ የሚቋቋሙትም “ራስ ገዝ” ይሆናሉ። አንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከሐምሌ 2015 ጀምሮ “ራስ ገዝ” ሆኗል። ለዩኒቨርሲቲዎቹ “የውስጥ አስተዳደርን በራስ የመወሰን፣ አስተዳደራዊ መዋቅሮችን የመዘርጋት፣ የትምህርት መርኃ ግብሮችን የመቅረጽ፣ ሥርዓተ ትምህርት የማዘጋጀት እና የማጽደቅ” ተቋማዊ ነጻነት በመስከረም 2016 የጸደቀው የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ አዋጅ አጎናጽፏቸዋል።



ከዚህ በተጨማሪ “ተማሪዎችን በራሳቸው መሥፈርት የመቀበል፣ የገንዘብ ምንጮችን የማፈላለግ እና አጠቃቀሙን የመወሰን ንብረት የማፍራት፣ የመሸጥ የመለወጥ ሠራተኞችን የመቅጠርና የማስተዳደር” ነጻነት አላቸው። የኢትዮጵያ መንግሥት በመቐለ፣ ባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ ጅማ፣ ሐዋሳ እና አርባ ምንጭ የሚገኙትን ጨምሮ አስር ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ የማድረግ ዕቅድ እንዳለው አስታውቆ ነበር።



ዩኒቨርሲቲዎቹ ራስ ገዝ ሲሆኑ ተማሪዎቻቸውን የሚያስከፍሉት ክፍያ መጨመር እንደሚኖርባቸው የሚናገሩት ዶክተር አብዱልመናን ይህ ገንዘብ ያላቸው ብቻ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲገቡ ሊያደርግ እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ። ከፍተኛ ውጤት ያመጡ እና ሴቶችን ለመደገፍ የሚያስችሉ ሥርዓቶች ዩኒቨርሲቲዎች መዘርጋት ቢችሉም አሠራሩ ግን ገንዘብ ወዳላቸው ሊያደላ እንደሚችል ሥጋት አላቸው።



አርታዒ ነጋሽ መሐመድ

Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የማስተማሪያ ሆስፒታሎች በጀት መፈተሽ እንዳለበት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ተናገሩ

የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የማስተማሪያ ሆስፒታሎች በጀት መፈተሽ እንዳለበት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ተናገሩ

Eshete Bekele