DiscoverDW | Amharic - Newsየግል መረጃ ጥሰት እና የፊት ገፅታን ለይቶ የማወቂያ ቴክኖሎጂ
የግል መረጃ ጥሰት እና የፊት ገፅታን ለይቶ የማወቂያ ቴክኖሎጂ

የግል መረጃ ጥሰት እና የፊት ገፅታን ለይቶ የማወቂያ ቴክኖሎጂ

Update: 2025-07-02
Share

Description

ድሮ ዱሮ በሳይንስ ልብወለድ ፊልሞች ላይ የምናየው ፤የፊት ገፅ መለያ ቴክኖሎጂ፡/ Facial recognition/ በአሁኑ ወቅት የዕለት ተዕለት ሕይወታችን አንድ አካል ሆኗል።ይህ ቴክኖሎጂ የስማርት ስልኮችን ከመክፈት ጀምሮ ለግብይት፣በጤና ተቋማት ታካሚዎችን ለመከታተል፣በአውሮፕላን ማረፊያዎች ላይ የመንገደኞችን ማንነት ለመለየት እንዲሁም የወንጄል ተጠርጣሪዎችን ለመከታተል እና የህግ አስከባሪ አካላትን ለማገዝ ጥቅም ላይ ይውላል። በዚህ መልኩ ተደራሽነቱ እያደገ የመጣው ይህ ቴክኖሎጂ በጤና ፣በገንዘብ እና በትምህርት ተቋማት እንዲሁም በግብይት ቦታዎች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።የሳይበር ደህንነት ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ብሩክ ወርቁ እንደሚሉት ቴክኖሎጂው የሰዎችን ተፈጥሯዊ የፊት ገፅታ በመለየት ውሳኔ የመስጠት አቅምን ያግዛል።



የግለሰብን ማንነት ለመለየት እና ለማረጋገጥ



የፊት ለይቶ ማወቂያ ቴክኖሎጂ የሰዎችን የፊት ገፅታ በመጠቀም የግለሰብን ማንነት ለመለየት ወይም ለማረጋገጥ የሚጠቅም ዘዴ ነው።ከባዮሜትሪክ ወይም በሰው ልጆች መረጃ ላይ ከተመሰረቱ የደህንነት መጠበቂያ ዘዴዎች ውስጥ የሚመደበው ይህ ቴክኖሎጂ ፤ሰዎችን በፎቶ፣ በቪዲዮ ወይም በአካል ለመለየት ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል። እያንዳንዱ የፊት ለይቶ ማወቂያ ዘዴ ብዙውን ጊዜ በተለያዩ በስልተ ቀመሮች ላይ የተመሰረተ እና በተለየ መንገድ የሚሰራ ቢሆንም ፤በተሰጠው መረጃ ላይ ተመስርቶ የመለየት ፣የመተንተን ፣ምስልን ወደ መረጃ የመቀየር እና እውቅና የመስጠት ሂደቶችን በደረጃ ያከናውናል። ውጤቱም እንደ አቶ ብሩክ ለልየታ የሚቀርበው የፊት አሻራ ቀደም ሲል በመረጃ ቋት ከተቀመጠው የውሂብ ክምችት ጋር ባለው መቀራረብ የሚወሰን ነው።



መረጃዎች እንደሚያሳዩት ይህ ቴክኖሎጂ በጎርጎሪያኑ 2022 ዓ/ም፣ ገበያ ላይ የነበረው ድርሻ 5.15 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሲሆን ከ 2023 እስከ 2030 ባሉት ዓመታት ደግሞ 14.9% ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል ። ከዚህ ጋር, ተያይዞም የፊት ገፅታን ለይቶ ማወቂያ ስልተ ቀመሮች ይበልጥ ውስብስብ እየሆኑ መጥተዋል።የሚሰጣቸው ጥቅሞች እና አገልግሎቶችም በዚያው ልክ እያደገ ነው።



ቴክኖሎጂው የሚሰጣቸው ጥቅሞች እና አገልግሎቶች



የፌት ገጽታን የመለየት ቴክኖሎጂ ቅኝት ለማድረግ ፣ድንበር ለመጠበቅ ፣የህግ አካላትን ለማገዝ፣ የትራንስፖርት ፍሰትን ለመቆጣጠር ፣ለባንክ አገልግሎት፣ እንዲሁም ለገበያ እና ማስታወቂዎችን ለመስራት ጥቅም ላይ ይውላል።በዚህም ወንጀልን ለመከላከል ፤ የደህንነት ስጋትን ለመቀነስ፣የተፋጠነ አገልግሎት ለመስጠት እና የተሻለ ውሳኔ ለመወሰን ያግዛል።



ይሁን እንጅ ይህ ቴክኖሎጂ ከሚሰጣቸው አስደናቂ ጥቅሞች ባሻገር፤ በአተገባበር ላይ የሚታዩ የህግ እና የሥነምግባር ጥያቄዎች አሉ።ከነዚህም መካከል ቴክኖሎጂው በመረጃ ግላዊነት እና ደህንነት ችግር ላይ በዘር እና በማንነት መድሎ እንዲሁም ተቃዋሚዎችን ዒላማ ለማድረግ በመንግስታት ጥቅም ላይ እየዋለ ነው በሚል በርካታ የሥነምግባር ጉዳዮች ይነሱበታል። በአሁኑ ወቅት በርካታ ድርጅቶች በሰዎች ምትክ የፊት ገፅታን ለመለየት የሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን /AI / እየተጠቀሙ መሆናቸው ደግሞ ችግሩን የበለጠ አድርጎታል።



የሰውሰራሽ አስተውሎት ችግሩን አባብሶታል



ይህ መሰሉ ችግር በሶስት መንገድ ሊከሰት ይችላል የሚሉት አቶ ብሩክ፤የመጀመሪያው ስህተት ወደ መረጃ ቋት የሚገባው እና የሚሰበሰበው የመረጃ ናሙና በጣም ውሱን መሆን ነው።ይህም አንድን ግለሰብ ወይም ማህበረሰብ ያለ አግባብ እንዲወከል ያደርገዋል ይላሉ።



ሁለተኛው ስህተቱ የሚከሰትበት መንገድ የመረጃ ስርዓቱ የሚመሰረትበት ስልተቀመር ወይም አልጎሪዝም አድሏዊ መሆን ነው።ይህም የመረጃ ቋቱን የቀረፁት ሰዎች ሁሉንም ባገናዘበ መንገድ ሳይሆን በአብዛኛው በአደጉ ሀገራት መረጃ ላይ እና ቴክኖሎጂው በተሰራበት አካባቢ ባለ ማኅበረሰብ መረጃ ላይ ተመስርተው በመስራታቸው ነው።ሶስተኛው እና የመጠረሻው የችግሩ መነሻ ደግሞ የሚሰበሰበው መረጃ ቴክኖሎጂው የሚተገበርበትን ቦታ አውድ ያላገናዘበ መሆኑ ነው።ይህም ባለሙያው እንደሚሉት ውሳኔን እንዲዛባ ሊያደርግ ይችላል።የግለሰቦችን መረጃ የመጠበቅ ችግርም በዚህ ቴክኖሎጂ ላይ የሚነሳ ሌላው ስጋት ነው።



አናሳ ቡድኖችን እና አንቂዎችን የመከታተል ስጋት



የዲጅታል መብት ተከራካሪዎች በበኩላቸው ከግላዊ መረጃ ደህንነት በተጨማሪ መንግስታት ዜጎችን ለመሰለልእንዲሁም አናሳ ቡድኖችን እና አንቂዎችን ለመከታተል ጥቅም ላይ ሊያውሉት ይችላል በሚል ይተቻሉ።ለምሳሌ ቻይና ከ700 ሚሊዮን በላይ የስለላ ካሜራዎችን በመትከል በመላ አገሪቱ ያሉ ግለሰቦችን የፊት ገፅታ ለመለየት ትጠቀማለች።በዚህም በሀገሪቱ ዜጎች ላይ የጅምላ ቅንት እና ክትትል ይደረጋል።በምስራቅ አውሮፓዊቷ ሀገር ሃንጋሪም መንግስትን በሚቃወሙ በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ይህንኑ ቴክኖሎጂ መጠቀሟን ዘገባዎች ያሳያሉ።ይህም ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ይጥሳል በሚል እየተወቀሰች ነው።



ችግሩን ለመቀነስ የመፍትሄ ርምጃዎች



በሌላ በኩል እንደዚህ ባለ ሰፊ የውሂብ ክምችት መረጃውን ማን ሊያገኘው ይችላል? እንዴትስ ጥቅም ላይ ይውላል? የሚሉት ጥያቄዎች መልስ የላቸውም።ስለሆነም ፤ ከህግ ማስከበር ጋር ተያይዞ በመንግስታት በኩል የሚፈፀመውን የግል መረጃ ጥሰት መከላከል አስቸጋሪ ቢሆንም፤ይህንን ቴክኖሎጂ ለንግድ አገልግሎት በሚጠቀሙ ድርጅቶች ላይ ግን፤የመረጃ ደህንነትን ለመጠበቅ የወጡ የአሰራር መመሪያዎችን እና ህጎችን መተግበርን ጨምሮ ሌሎች ችግሩን ለመቀነስ መወሰድ ያለባቸው ርምጃዎች መኖራቸውን አቶ ብሩክ ወርቁ ገልፀዋል።



የመረጃ ክምችቱ በበቂ ናሙና ላይ ተመስርቷል ወይ?፣በቂ ሙከራ ተደርጎበታል ወይ?የተሰራበትን አውድ ባማከለ ሁኔታ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው ወይ?፣መረጃው የተወሰደው በግለሰቡ ግልፅ ስምምነት ነው ወይ?የሚሉት ነገሮች መታየት እንዳለባቸው አስረድተዋል።የመረጃ ግላዊነትን መጠበቅ እና ከሳይበር ጥቃት መከላከል እንዲሁም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ብዝሃነት ባለባቸው ሀገራት የመረጃ ክምችት ብዙሃኑን ያማከለ እንዲሆን የመረጃ ቋትን ኦዲት ማድረግም አስፈላጊ መሆኑን አቶ ብሩክ አስምረውበታል።



ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጥነው ያድምጡ።





ፀሐይ ጫኔ



ነጋሽ መሐመድ

Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

የግል መረጃ ጥሰት እና የፊት ገፅታን ለይቶ የማወቂያ ቴክኖሎጂ

የግል መረጃ ጥሰት እና የፊት ገፅታን ለይቶ የማወቂያ ቴክኖሎጂ