የኅዳር 15 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
Description
የሊቨርፑል እና ማንቸስተር ሲቲ ነጥብ መጣል ዕድሉን ያሰፋለት አርሰናልን በለንደን ደርቢ ቶትንሀምን በሰፋ የግብ ልዩነት ድል አድርጎ ተጨዋቾቹን እጅግ አበሳጭቷል ። ባዬርን ሙይንሽን ፍራይቡርግን 6 ለ2 አንኮታኩቷል ። የአይንትራኅት ፍራንክፉርት ነውጠኛ ደጋፊዎች የሽቱትጋርት ደጋፊዎችን አውራ ጎዳና ላይ ጠብቀው ከአውቶቡስ በማስወረድ መደብደባቸው ተዘግቧል ። እነ ብራድ ፒት፣ ቢዮንሴ እና ጄዚን የመሳሰሉ የዓለማችን ታዋቂ አርቲስቶች በታደሙበት የላስቬጋሱ የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የሬድ ቡል አሽከርካሪ ማክስ ፈርሽታፐን አሸንፏል ።
25ኛው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ
በርካታ ታዳሚዎች የተሳተፉበት 25ኛው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በትናንትናው ዕለት አዲስ አበባ ውስጥ ተከናውኗል ። በ2018 «ሶፊ ማልት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ» 10 ኪ.ሜ የወንዶች ፉክክር አትሌት ይስማው ድሉ ለድል በቅቷል ። በሴቶች ፉክክር አትሌት መልክናት ውዱ አሸንፋለች ። መነሻ እና መድረሻው መስቀል አደባባይ በሆነው የታላቁ ሩጫ ፉክክር ወደ አምሳ ሺህ ግድም ሰዎች መታደማቸውም ተገልጧል ።
ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እግር ኳስ ከነገ በስትያ ረቡዕ ከኬንያ ጋር ይጋጠማል ። ለዚህ የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ ዝግጅት ቡድኑ ዛሬ ማለዳ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ልምምድ ማድረጉም ተዘግቧል ። በሦስተኛ የምድቡ ግጥሚያ ከሶማሊያ አቻው ጋር ሦስት እኩል አቻ የወጣው ኢትዮጵያ ቡድን ምድቡን በ7 ይመራል ። ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀራት ኬንያ በ4 ነጥብ ትከተላለች ። ሶማሊያ በ3 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ። እንደ ኬንያ ሁለት ጨዋታ አድርገው አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀራቸው ደቡብ ሱዳን እና ርዋንዳ በአንድ እና በምንም ነጥብ ከ4ኛ እስከ 5ኛ ተደርድረዋል ።
በፕሬሚየር ሊጉ ኤቤሬቺ ኤዜ ገንኖ አምሽቷል
አርሰናል በደጋፊዎቹ ፊት ብርታቱን ባሳየበት የትናንቱ ግጥሚያ ቶትንሀምን እንደማይሆን አድርጎ ከኤሚሬትስ ስታዲየሙ ሸኝቶታል ። በደረጃ ሰንጠረዡ በ29 ነጥብ የሚገሰግሰው አርሰናል ቶትንሀምን 4 ለ1 ጉድ አድርጎ ነው ያሰናበተው ። ለአርሰናል ቀዳሚዋን ግብ ሌናርዶ ትሮሳድ አስቆጥሯል ። ከዚያ በኋላ ግን ምሽቱ የኤቤሬቺ ኤዜ ነበር ። እንግሊዛዊው አማካይ አጥቂ ኤቤሬቺ ኤዜ ሦስት ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ሔትሪክ ሠርቷል ።
የአርሰናል አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ በትናንቱ ግጥሚያ የአርሰናል ደጋፊዎችን ጮቤ ያስረገጠው ኤቤሬቺ አንዳች ነገር ለማድረግ አስቀድሞም ቆርጦ እንደነበር ይፋ አድርገዋል ። ከዓለም አቀፍ ውድድር በኋላ የሁለት ቀናት ረፍት ተሰጥቶት የነበረው ኤቤሬቺ ኤዜ ረፍቱን የተጠቀመው አንድ ቀን ብቻ ነበር ። በሁለተኛው ቀን ተጨማሪ ልምምድ ማድረግ እንደሚፈልግ፤ ማሻሻል የሚገባቸው ነገሮች እንዳሉ እና ሌሎችን ነገሮችንም በማንሳት አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታን ይጠይቃል ። እሳቸውም ይስማማሉ ። አንዳች ነገር ማድረግ አስቀድሞ ዓልሞ የነበረው ኤቤሬቺ ኤዜም አርሰናልን በግብ አንበሽብሾ፤ አሰልጣኙንም ደጋፊዎችንም አስቦርቋል ። የኅዳር 1 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
የሚገርመው ደግሞ ኤቤሬቺ ኤዜ ሦስት ግቦችን በተከታታይ ያስቆጠረው ከክሪስታል ፓላስ ሊዘዋወርበት ጫፍ ደርሶ በነበረው ቶትንሀም ላይ መሆኑ ነው ። አርሰናል ኤቤሬቺ ኤዜን ባለቀ ሰአት ነው በ88 ሚሊዮን ዶላር ግድም ከቶትንሀም መንጋጋ ፈልቅቆ ራሱኑ ቶትንሀምን በብርቱ የወጋበት ። ኤቤሬቺ ኤዜ የለንደን ከተማ ዋነኛ ተቀናቃኙ ቶትንሀም ላይ ሔትትሪክ በመሥራት ካለፉት 90 ዓመታት ወዲህ ሦስተኛው ሰው ሁኗል ። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1934 እና በ1978 በአንድ ጨዋታ ቶትንሀም ላይ ሦስት ግቦችን ካስቆጠሩት ቴድ ድሬክ እና አላን ሠንደርላንድ ጋር በመሆንም ታሪክ ጽፏል ።
የቶትንሀሙ ብራዚሊያዊ አጥቂ ሪቻርሊሰን ድንቅ ግብ
በምሽቱ እልህ የተሞላበት ግጥሚያ የቶትንሀሙ ብራዚሊያዊ አጥቂ ሪቻርሊሰን ያስቆጠራት ብቸኛ ግብ ሳትጠቀስ አትታለፍም ። 55ኛው ደቂቃ ላይ የግብ ጠባቂው ዳቪድ ራያን ከግብ ክልሉ መራቅ የተመለከተው ሪቻርሊሰን ከመሀል ሜዳ ግድም ከፍ አድርጎ በመመጠን ኳሷን ወደ ግብ ይልካል ። ዳቪድ ራያን ኳሷን ለማጨናገፍ ወደ ኋላ እየተውተረተረ ያፈገፍጋል ። ዘግይቶ ነበር ። ግብ ጠባቂው ከነኳሷ ከመረብ አርፈዋል ። የአጥቂው ድንቅ ብቃት የታየበት ክስተት ነበር ። ከዚያ ባሻገር ግን ቶትንሀም አንዳችም መፈየድ አልቻለም ። ይልቁንስ የተቆጡ ነብሮች የመሰሉት አርሰናሎች በቶትንሀም ሜዳ እና ተከላካዮች ዘንድ እየተመላለሱ በማስጨነቅ ለወሳኝ ድል በቅተዋል ። አሁን አርሰናል ከተከታዩ ቸልሲ በስድስት ነጥብ ርቆ በ29 ነጥቡ በመሪነት ተኮፍሷል ።
በጨዋታ ዘመኑ መጀመሪያ አካባቢ ልክ እንደ አርሰናል በነጥብ ሌሎቹን ርቆ በአንደኛነት ተኮፍሶ የነበረው ሊቨርፑል ደግሞ የቁልቁለት ሽምጡን ተያይዞታል ። ሊቨርፑል በገዛ አንፊልድ ሜዳው ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በደጋፊዎች ፊት ከፍተኛ ውርደት ተከናንቧል ። አሰልጣኝ አርኔ ስሎት ባለፉት ሰባት ግጥሚያዎች ሊቨርፑል እንዲያሸንፍ ያስቻሉት በአንዱ ብቻ ነው ። ይህም ደጋፊዎች በሊቨርፑል ለዘጠኝ ዓመታት ቆይተው ቡድኑን በተለያዩ ዋንጫዎች ያንበሸበሹት ዬርገን ክሎፕን እንዲመኙ አድርጓል ። በተለይ ደግሞ ሊቨርፑል የዝውውር መስኮቱ ከመዘጋቱ ቀደም ብሎ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ግድም በማፍሰስ እነ ፍሎሪያን ቪርትስ፣ አሌክሳንደር ይሳቅ እና ሑጎ ኢኪቲኬን የመሳሰሉ የዓለማችን ምርጥ አጥቂዎችን አስመጥቶም ድል የራቀው መሆኑ አነጋጋሪ ሁኗል ።
የሊቨርፑል የቁልቅለት ሽምጥ
ሊቨርፑል ቅዳሜ እለት በአንፊልድ ሜዳው 3 ለ0 የተሸነፈው በደረጃ ሰንጠረዡ ከመጨረሻ በአንድ ብቻ ከፍ ብሎ በነጥብ ቁልቁል ይገኝ በነበረው ኖቲንግሀም ፎረስት ነው ። በበርካታ መቶ ሚሊዮናት የተገዙ ተጨዋቾች በቅዳሜው ግጥሚያ ለሊቨርፑል አንዳችም ሳይፈይዱ በዜሮ ተሰናብተዋል ። ወደ ቡድኑ ገና እንደመጡ ባሳዩት ውጤት ብዙ የተነገረላቸው የሊቨርፑል አልጣኝ አርኔ ስሎትም ቅጭም ባለ ፊታቸው ከሜዳው በፍጥነት ወጥተዋል ። በገዛ ሜዳው ብርቱ ሽንፈት የተከናነበው ሊቨርፑል ተጨዋቾችን እስከመጨረሻው ታድመው የደገፉ ቢኖሩም በርካታ ደጋፊዎች በጨዋታ መገባደጃው በፍጥነት ከአንፊልድ ስታዲየም ወጥተዋል ። የትናንቱን ብርቱ ሽንፈት ጨምሮ ሊቨርፑል ላይ በተደጋጋሚ የደረሰው ነጥብ መጣል ለአሰልጣኝ አርኔ ስሎት ብርቱ የማስጠንቀቂያ ደወል ነው ። የጥቅምት 24 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ኖቲንግሀም ፎረስት አንፊልድ ላይ በተቀዳጀው አመርቂ ድል ከወራጅ ቀጣናው 19ኛ ደረጃ ተላቅቆ ወደ 16ኛ ከፍ ብሏል ። በሊቨርፑል የሚበለጠው በ6 ነጥብ ብቻ ነው ። በዘንድሮ የጨዋታ ዘመን የመጀመሪያ ሳምንታት በአንደኛነት ሲመራ የቆየው ሊቨርፑል ዝቅተኛ ነጥብ ባላቸው ቡድኖች በተከታታይ በደረሰበት ሽንፈት በ18 ነጥቡ ተወስኖ አሁን ወደ 11ኛ ደረጃ አሽቆልቁሏል ።
ቸልሲ በርንሌይን 2 ለ0 አሸንፎ ነጥቡን 23 በማድረስ በድል ገስግሷል ። ማንቸሰስተር ሲቲ በኒውካስል ዩናይትድ 2 ለ1 ጉድ ሁኖ በ22 ነጥቡ በሦስተኛ ደረጃ ተወስኗል ። እንደ ሊቨርፑል 18 ነጥብ ሰብስቦ ከሊቨርፑል በግብ ክፍያ ከፍ ብሎ 10ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ ዛሬ ማታ በኦልድ ትራፎርድ ስታዲየሙ ኤቨርተንን ያስተናግዳል ። ማንቸስተር ዩናይትድ በምሽቱ ተስተካካይ ጨዋታው ድል ከቀናው ወደ አምስተኛ አለያም እንደ ግብ ብዛቱ ወደ አራተኛ ደረጃ ሊስፈነጠር ይችላል ።
የአይንትራኅት ፍራንክፉርት ነውጠኛ ደጋፊዎች ኹከት
በኮሎኝ ሜዳ ተጋጥመው 4 ለ3 ያሸነፉት የአይንትራኅት ፍራንክፉርት ደጋፊዎች ከጨዋታው በፊት እና በኋላ ኹከት እና ትርምስ መፍጠራቸው አነጋጋሪ ሁኗል ። የቅዳሜው የቡንደስሊጋ ግጥሚያ ከመጀመሩ በፊት የአይንትራኅት ፍራንክፉርት ደጋፊዎች ስታዲየሙ ውስጥ ተቀጣጣይ ነገር በመጠቀም እና የኮሎኝ ደጋፊዎችን የሚተናኮሉ መፈክሮችን በማንገብ ግርግር ለመፍጠር ሞክረዋል ። ጨዋታውን በድል ካጠናቀቁ በኋላ ደግሞ ወደ ዐርባ የሚጠጉ ነውጠኛ የአይንትራኅክት ፍራንክፉርት ደጋፊዎች አውራ ጎዳና ላይ ያገኙዋቸውን የሽቱትጋርት ደጋፊዎች ከአውቶቡስ አስወርደው መደብደባቸው ተሰምቷል ። የሽቱትጋርት ደጋፊዎች ቡድናቸው ከቦሩስያ ዶርትሙንድ ጋር ተጋጥሞ ሦስት እኩል ከተለያየ በኋላ ወደ ቤታቸው በመመለስ ላይ ነበሩ ። መሰል የደጋፊዎች ጥፋቶች በቡድኖች ላይ ጣጣ እና ቅጣት ማስከተሉ አይቀሬ ነው ።
አይንትራኅት ፍራንክፉርት በ20 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው ። ከበላዩ በሁለት ነጥብ ከፍ ብሎ ሽቱትጋርት ይገኛል ። ፍራይቡርግን ቅዳሜ ዕለት 6 ለ2 የረታው ባዬርን ሙይንሽን ቡንደስሊጋውን በ31 ነጥብ ይመራል ። ላይፕትሲሽ በ25 ይከተላል ። ባዬር ሌቨርኩሰን በ23 ነጥብ ይከተላል ። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ22 ነጥቡ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ።
የቦሩስያ ዶርቱሙንዱ ዮአኪም ቫትሰከ ማን ናቸው?
የቦሩስያ ዶርቱሙንድ የረዥም ዘመን ሥራ አስኪያጅ ሥለጣናቸውን አስረከቡ ። ቦሩስያ ዶርቱሙንድን ለ20 ዐመታት ከፊት ሁነው የመሩት ፈላጭ ቆራጭ ሰው ሥራ አስኪያጅነቱን ቢያስረክቡም አሁን የቡድኑ ፕሬዚደንት ሁነዋል ። ሰውዬው ከአውሮጳ እግር ኳስ ማኅበር አባልነት አንስቶ እስከ ጀርመን ቡንደስታግ ከፍተኛ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ቁንጮ ድረስ ጠንካራ ግንኙነት አላቸው ። ከጀርመን መራኄመንግሥ ፍሬድሪሽ ሜርስ ጋር ወዳጅነታቸው ለ48 ዐመታት የዘለቀ መሆኑ ይነገራል ። ፍሬድሪሽ ሜርስ በቦሩስያ ዶርትሙንድ ለዐሥር ዓመታት ግድም የተቆጣጣሪዎች ቦርድ አባል ሆነው እንዲያገለግሉ ማስደረጋቸው ይነገራል ።
ቦሩስያ ዶርቱሙንድን ከስሮ ሊበተን ባለበት ዘመን ድንገት ብቅ ብለው ታድገውታል ዮአኪም ቫትሰከ ። በኋላ ትሩፋታቸው ለሊቨርፑልም ከተረፈው ጀርመናዊው አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ጋር በመሆንም የቡንደስ ሊጋ ዋንጫን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2011 ብሎም ባመቱ የጀርምን ዋንጫን ጨምሮ በማንሳት የአመራር ብቃታቸውን ዐሳይተዋል ። ቡድኑ ገቢው ከሰማንያ ሚሊዮን ግድም ወደ ግማሽ ቢሊዮን እንዲመነደግም አስችለዋል ። ግን ደግሞ በቦሩስያ ዶርቱሙንድ ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ይታማሉ ። የጥቅምት 17 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ከበርሊን ዶርትሙንድ በግል አውሮፕላን በርረው 12 ሺህ ዩሮ እንደዘበት አውጠተዋል ሲሉ ተቺዎቻቸው እንደ አብነት ያቀርባሉ ። እሳቸው ለቡድኑ ሲባል ለሥራ የወጣ ገንዘብ ነው ነው የሚሉት፤ ቡድኑም በኋላ ላይ አጣርቶ ይህኑ ደግሞታል ።
በቡድኑ የቀድሞ አንድ ባልደረባ ላይ ሦስት ግድም የወሲብ ትንኮሳ ክሶች ቀርበው ወዲያው ውሳኔ አልሰጡም ተብለው ይተቻሉ ። በእርግጥ ትንኮሳ አደረገ የተባለው ሰው በኋላ ላይ ከቦታው እንዲነሳ ተደርጓል ። ያ ሰው ክሶቹን በወቅቱ አስተባብሏል ።
ዮአኪም ቫትሰከ ፈላጭ ቆራጭ ናቸው የሚሏቸውም አሉ ። ለዚያም ይመስላል ከዋና ሥራ አስኪያጅነቱ በጫና መነሳቱ ግድ ሲሆንባቸው በ66 ዐመታቸው የተቋሙ ፕሬዚደንት የሆኑት ። ብቸኛ ተፎካካሪያቸው እና ለዳግም ፕሬዚደንትነት ሊወዳደሩ ከነበሩት ዶ/ር ራይንሆልድ ሎንሆቭ ጋር በጎሪጥ ዕየተያዩ ሰንብተው ነበር ። ኋላ ላይ ራይንሆልድ ፕሬዚደንትነቱን ትተውላቸው ከተፎካካሪነቱ ወጥተዋል ። እሳቸውም በትናንትናው የቡድኑ ምርቻ ደካማ በተባለመልኩ 59 ከመቶ ድምጽ አግኝተው የተመኙትን ፕሬዚደንትነት ቦታ አግኝተዋል ።
የመኪና ሽቅድምድም
እነ ብራድ ፒት፣ ቢዮንሴ እና ጄዚን የመሰሉ የዓለማችን ታዋቂ አርቲስቶች በታደሙበት የላስቬጋሱ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የሬድ ቡል አሽከርካሪ ማክስ ፈርሽታፐን አሸንፏል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ ነኝ
ነጋሽ መሐመድ























