የናይሮቢ-አዲስ አበባ ቀጥታ የአውቶብስ ትራንስፖርት ውጥን
Description
የየብስ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሞላው ክፍተት
አቢሲኒያ የግል ትራንስፖርት ኩባንያ የኢትዮጵያ እና ጎረቤት ኬንያ መዲናዎችን በየብስ ትራንስፖርት በቀጥታ ለማገናኘት ወጥኖ እንቅስቃሴ መጀመሩን ያሳወቀው ባሳለፍነውው ሳምንት ነው፡፡ በአውቶብስ መንገደኞችን በእየለቱ ከአዲስ አበባ ናይሮቢ እና ከናይሮቢ አዲስ አበባ ለማጓጓዝ ወጥኖ እንቅስቃሴ የጀመረው ድርጅት በመሰረታዊነት ግንዛቤ ውስጥ ያስገባው ሃሳብ ምን ይሆን? የኩባንያው ዳይሬክተር ሚካኤል ጀምስ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት ሀሳቡን ለማመንጨት የገፋፋቸውን እውነታ እንዲህ በማስረዳት አስተያየታቸውን ጀምረዋል፡፡ “የኛ ሀሳብ ሁለቱ ጎረቤታሞች አገራት መካከል ሰፊ የህዝብ እንቅስቃሴ አለ፡፡ ሁለተኛው ሃሳባችን ደግሞ ከአዲስ አበባ ናይሮቢ ለመሄድ ለሁለት ሰዓት በረራ በአየር ትራንስፖርት የሚጠየቀው 1 ሺኅ 300 ዶላር ግድም ነው፤ ወደ መቶ አርባ ሺኅ ብር እንደማለት ነው፡፡ እኛ ግን ለአንድ ጉዞ የምናስከፍለው ከናይሮቢ አዲስ አበባ 15 ሺኅ ሽሊንግ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ናይሮቢ 16 ሺህ ብር ነው” በማለት የተጓዦችን ፍላጎት እና አቅም በማገናዘብ ይህን ክፍተት ለመድፈን ሀሳቡ መመንጨቱን አስረድተዋል፡፡
አሁን አቢሲንያ የህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርትኩባንያ ወደ ስራ ለመግባት ከመወጠኑ በፊት ሮያል አላይድ (Royal Allied) የተሰኘ የህዝብ ማመላለሻ አገልግሎት ሰጪ አውቶብሶች ከናይሮቢ ሞምባሳ እና የኬንያ-ኢትዮጵያ የድንበር ከተማዋ ሞያሌ ድረስ መሰል አገልግሎትን ሲሰጥ ብቆይም ከዚያ ግን አልተሻገረም፡፡ እየናረ የመጣው የአየር ትራንስፖርት እና በተለይም በንግድ ስራ ሁለቱ አገራት መካከል ለሚመላለሱ በየቦታው ለመውረድ እድል አለመስጠቱ ደግሞ የሁለቱን አገራት ዋና ከተሞች ለማገናኘት ለተያዘው ውጥን ዋናው መነሻ ነው ተብሏልም፡፡ እናም የአቢሲንያ ቅንጡ የአውቶብሶች ማጓጓዣ አገልግሎት ተደራሽነቱን እውን ለማድረግ በናይሮቢ በኩል ስምንት አውቶብሶች መሰናዳታቸውን የገለጹት የኩባንያው ዳይሬክተር በአዲስ አበባ በኩልም ስምንት አውቶብሶችን ለማስገባት ግዢ ተፈጽሞ በሂደት ላይ ነው ብለዋል፡፡ “በኢትዮጵያ በኩል የባሶቹ ግዢ ገና ሂደት ላይ ቢሆንም በናይሮቢ ስምንት አውቶቢሶች ተነናድተዋል፡፡ ዓለማው ከነተጠባባቂ አውቶቢሶች 16 ያህሉን ማዘጋጀት ነው” ብለዋል፡፡
የአውቶብሱ ተደራሽነትና የመዳረሻ ሰዓት
የማጓገዋዣ አውቶቢሱ በዋናነት ዓላማ አድርጎ የተነሳው መንገደኞችን መንገድ ላይ ማሳደር ሳያስፈልግ በ24 ሰዓት ውስጥ ከመዳረሻቸው ማድረስ ነው የሚሉት ኃላፊው፤ ጉዞው በምክንያታዊ ዋጋ ተፈላጊ አገልግሎት መስጠት እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ “ባሱ ቀጥታ ስለሚገባ ተሳፋሪዎች መንገድ ላይ አያድሩም፤ ለምሳሌ ከዚህ ከአዲስ አበበባ አውቶብሱ ማለዳ 10፡30 ግድም ብነሳ ሞያሌ አመሻሽ 11፡00 ሰዓት ይደርሳል፡፡ ከዚያን የኢምግሬሽን ፍተሻ ከተከናወነ በኋላ ጉዞውን በመቀጠል ንጋቱን ናይሮቢ የሚገባ ይሆናል” ነው ያሉት፡፡
ሆኖም የጸጥታ ጉዳይ ታስቦበት ጥናት ተካሂዶም እንደሆን የተጠየቁት ዳይሬክተሩ፤ “ከአዲስ አበባ ሞያሌ ቀንም ሆነ ሌሊት መጓዝ ደህንነቱ የተጠበቀ በመሆኑ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ግን ለጊዜው ባሶቹ በቀን ብቻ እንዲጓዙ መርሃግብር ይወጣላቸዋል” ብለዋል፡፡
እያንዳንዱ አውቶብሶች 46 መቀመጫ እንዳላቸው የተገለጸ ሲሆን አውቶብሶቹ በኢትዮጵያ ውስጥ ሲያልፉ እንደ ያበሎ፣ ቡሌሆራ፣ ዲላ እና ሃዋሳ ያሉትን ከተሞች አቋርጠው አዲስ አበባ እንደሚገቡም ተመልክቷል፡፡
የፀጥታው ጉዳይ…
ከኢትዮጵያ ተነስቶ ዓለማቀፍ ድንበር የሚሻገር የሰው ማጓጓዣ ትራንስፖርት በሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት እስኪቋረጥ ከዚህ በፊት ከኢትዮጵያ ካርቱም አገልግሎቱ ይሰጥ የነበረ ቢሆንም ይህ ቀጥታው የናይሮቢ አዲስ አበባ የትራንስፖርት አገልግሎት ወደ ስራ ከገባ ረጅሙና በመስመሩ የመጀመሪያው በመሆኑ የሁለቱን አገራት ኢኮኖሚያዊ ትስስር ያጠናክራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
መልካም ጉርብትና እንዳላቸው በሚነገርላቸው ኢትዮጵያ እና ኬንያ መካክል ሰፊ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ስለመኖሩ ይነገራል፡፡ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ እና የግብርና ምርቶችን ወደ ኬንያ ስትልክ በዋናነት የምግብ ነክ ውጤቶች ከኬንያ በስፋት ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ፡፡ የኢትዮጵያ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴርመቀመጫውን ኬንያ ናይሮቢ ያደረገው አቢሲንያ ሌግዠሪ ኮች ጋር ተወያይቶ አገራቱን በየብስ ለማገናኘት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ አስፈላጊ ያለውን የሕግ ማዕቀፎች በማመቻቸት ላይ እንደሆነ ትናንት በይፋዊ ማህበራዊ ገጹ አስታውቋል፡፡
ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ