የገዋኔ ነዋሪዎች የተቃውሞ ሰልፍ
Description
በአፋር ክልል ገዋኔ ወረዳ ትናንት ጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ለ 8 ወራት ደመወዝ አልተከፈለንም ያሉና የመንግስት ሰራተኞች የመጠጥ ውኃ በአግባቡ እየቀረበ አይደለም የሚሉ የወረዳው ነዋሪዎች የኢትዮጵያ ጅቡቲን አውራ ጎዳና መንገድ ለሰዓታትበመዝጋት ተቃውሟቸውን ማሰማታቸው ተነገረ፡፡ ለተቃውሞወደ አደባባይ የወጡ የገዋኔ ነዋሪዎች እንደገለፁት በወረዳውየሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች በተገቢው መንገድ ደመወዝ እየደረሰን አይደለም ይላሉ፡፡ ‹‹ደመወዝ ከነጭማሪው ወደ 8 ወራት አልተከፈለንም፡፡ በ2017 ዓ.ም ግማሽ አለ፡፡ ከ2018 ዓ.ም ያልተከፈለ የደመወዝ ጉዳዩን ማን ይስማ፡፡››
የመልካም አስተዳደር ጦት
አሁን በወረዳው ህዝብ ላይ የሚታየው ቅሬታ «ከመልካም አስተዳደር እጦት» የመጣ ነው የሚሉት ነዋሪዎች የክልሉ መንግስት ጉዳዩን ትኩረት ሰጥቶ መመልከት አለመፈለጉን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ ሰው የሰራበትን የሚያጣ ከሆነ ማጣቱ ብቻ ሳይሆን የበላይ አካል እንደዚህ አይነት ነገር መኖሩን ሰምቶ በቀጥታመረዳት ካልቻለ ነገሩን የተያያዘ ነው ማለት ነው፡፡»
በገዋኔ ወረዳ ከዓመታት በፊት ተሰርቶ ለአገልግሎት የበቃ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ለወራት አገልግሎት ሳይሰጥ በመቋረጡ ከፍተኛ ወጭ እያወጣን ውሃ እየገዛን ነው የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎች በቦቴ ይቀርብ የነበረው ውሃም አሁን ቆሟል ይላሉ፡፡ ‹‹ለ8 ዓመታት ከክልሉ አደጋ መከላከል ውሃ በቦቴ መኪና እየቀረበልን ነበር። መሃል ላይ የነዳጅ ብር ያልተከፈለ በመሆኑ ውሃው ቆመ፡፡ ሰሞኑን ደግሞ በውሃ ችግር ሰዎቹም እየተንከራተቱ ነው፡፡››
ተገቢዉ ምላሽ ካልተሰጠን ተቃዉሞ እንቀጥላለን
እንደወረዳው ነዋሪዎች ገለፃ የትናንቱተቃውሞ ከሰዓታት በኋላ የተቋረጠው መንገደኞች ሊደርስባቸው የሚችለውን እንግልት ለመቀነስ እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በተደረገ መግባባት ቢሆንም ጥያቄው ካልተፈታ ከቀናት በኋላ በድጋሚ አደባባይ እንወጣለን ይላሉ፡፡ ‹‹መንገደኛ ምንም በማያውቀው ነገር ከሚንገላታ ተብሎ ነው እንጂ ሊከፍቱ ሃሳባቸዉ አይደለም፤ ለዚያ ደግሞ ሽማግሌዎች እኛ መንግስትን ጠይቀን ደመወዝ እንዲከፈል እናደርጋለን 3 ቀን ስጡን ስላሉ ነው፡፡ ከ3 ቀን በኋላደግሞ ካልተመለሰ ተመልሰው ይህንኑ ያደርጋሉ፡፡››
በአፋር ክልል ገዋኔ ወረዳ የፋይናንስ እና የኢኮኖሚ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ሙሚን መሀመድ ሙሚን እንደተናገሩት ሰራተኞቹ ያልተከፈላቸው የ3 ወር ደመወዝ ሲሆን እነኝህ 5 መስሪያ ቤቶች ደግሞ ሰራተኞች ደግሞ በልዩ ሁኔታ የደመወዝ ክፍያ ተፈፅሞላቸዋል ይላሉ፡፡
ለሰራተኞቹ ደመወዝ ይከፈላል
‹‹በትክክለኛው 3 ወር ነው፤ ቅድሚያ የምንሰጣቸው 5 መስሪያቤቶች አሉ፤ ፖሊስ፣ ትምህርት፣ ፍርድቤት፣ ፍትህ፣ ጤና ለእነኝህ ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ ከዚያ ውጭ ያሉት ነገሮች ሲስተካከሉየ ሚሆን ይሆናል፡፡›› የገዋኔ ወረዳ ፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ልማት ጽ/ቤት በበኩሉ በክልሉ መንግስት የተጣለበት የሚሰበሰብ የገቢ ግብር ከፍተኛ መሆኑ እና የተሰበሰበው ማነስ ለመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ መክፈል እንዳይችል እና የልማት ስራዎች እንዲቆራረጡ አድርጓል ይላሉ፡፡ ‹‹ደመወዝ ብቻም ሳይሆን ሌሎች ተከፋዮች አሉ፤ እጥረቱ ተባብሷል ከክልል በኩል መላክ ያለባቸውን እየላኩነው፡፡ እኛ እምንሰበስበው ማነስ ነው ችግሩ። ሁለተኛ ደግሞ ወደ አራት የሚደርሱ ቀበሌዎች ተቀንሰውብናል፤ አሁን ላይ እነዚያን ቀበሌዎች በማስረከባችን ትልቁ ጫና እኛ ላይበዛ፡፡››
አሁን በወረዳው ያለውን ሁኔታ የፖለቲካ ችግር የማድረግ አዝማሚያ አለው የሚሉት አቶ ሙሚን መሀመድ የኢትዮጵያ ጅቡቲን መንገድ ወደ መዝጋት መሸጋገር አልነበረበትም ይላሉ፡፡ በጉዳዩ ላይ የአፋር ክልል የፋይናንስ ቢሮ እና የክልሉን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎች ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።
ኢሳያስ ገላዉ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
አዜብ ታደሰ