የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሲዳማ እና የደቡብ የክልሎች ጉብኝት
Description
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ በሲዳማ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች የሥራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት እንዳሉት መንግሥት የአገልግሎት አሠጣጡን ለማዘመን ከአዲስ አበባ ወጭ በሚገኙ ከተሞች መሶብ ተብሎ የሚጠራውን የአንድ መስኮት የኤሌክትሮኒክስ ሥርዓት እየዘረጋ ይገኛል ብለዋል ፡፡
በሲዳማ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ጉብኝት ያደረጉት ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የሀዋሳ የኢንዱስትሪያል ፓርክን ጎብኝተዋል ፣ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላም አከናውነዋል ፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ በሀዋሳ ፣ በአርባ ምንጭ እና በዎላይታ ሶዶ ከተሞችሲገቡ የአገር ሽማግሌዎችና የከተማው ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል ፡፡
የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትን ለማሻሻል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በጉብኝታቸው ወቅት በሰጡት መግለጫ ህዝቡ ቅሬታ የሚያቀርብባቸው የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትን ለማሻሻል እየተሠራ ይገኛል ብለዋል ፡፡ መንግሥት የአገልግሎት አሠጣጡን ለማዘመን በአዲስ አበባ መሶብ ተብሎ የሚጠራውን የአንድ መስኮት የኤሌክትሮኒክስ ሥርዓት ከወራት በፊት ማስጀመሩ ይታወቃል ፡፡ አሁን ላይ አገልግሎቱን ከአዲስ አባባ ውጭ ባሉ የክልል ከተሞችም ለማስፋት እየተሠራ ይገኛል ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ “ የሀዋሳው አያያዙ ጥሩ ነው “ በማለት አድንቀዋል ፡፡
ቶዮ ለማኑፋክቸሪንግ ተስፋ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለማኑፋክቸሪንግ ማደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል የተባለውን በሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክየሚገኘውን የቶዮ የጸሐይ ብርሃን ኃይል ማመንጫ ፋብሪካንም ጎብኝተዋል ፡፡የቶዮ ኩባንያ ከወራት በፊት በቬይትናም በነበራቸው ጉብኝት ከኩባንያው ፕሬዚዳንት ጋር ባደረጉት ሥምምነት ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን ያስታወሱት አብይ “ ተጨማሪ ባለሀብቶች ወደ አገር እንዲገቡ የመጣውን በደንብ ማስተናገድና መያዝ ያስፈልጋል “ ብለዋል ፡፡
ቀጣይ ትኩረት
ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ እየተጠናቀቀ ባለው 2017 ዓ.ም የሲዳማ እና የደቡብ ኢትዮጵያን ክልሎች ሲጎበኙ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው ፡፡ ዶቼ ቬለ የጠቅላይ ሚንስትሩን ጉብኝት አስመልክቶ የግል አስተያየታቸውን የጠየቃቸው በሲዳማ ክልል በተቃዋሚ ፓርቲ አመራርነት የሚንቀሳቀሱት አቶ ገነነ ሀሰና ጉብኝቱ ለክልሉ በጎ መነሳሳት እንዳለው ጠቅሰዋል ፡፡ ክልሉ ሠፊ የተፈጥሮ መስህብና በርካታ የሰው ሀይል ጉልበት ያለው መሆኑን የተናገሩት አቶ ገነነ “ ነገር ግን እስከአሁን ቀደምሲል ከተሠሩ ሆቴሎችና ሪዞርቶች በስተቀር በገበታ ለአገር አይነት የሚሠሩ ፕሮጀክቶች አልታዩም ፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ በቀጣይ ይህ የልማት ዕድል ለክልሉ ይሰጣሉ የሚል ተስፋ አለኝ “ ብለዋል፡፡
ዘገባ ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ሂሩት መለሠ
ፀሀይ ጫኔ