“ወደ ሰላም አማራጭ ተመልሰዋል” የተባሉ ታጣቂዎችና የዘላቂ ሰላም ተስፋ
Description
“ወደ ሰላም አማራጭ ተመልሰዋል” የተባሉ ታጣቂዎችና የዘላቂ ሰላም ተስፋ
በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ወለጋ እና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች በተያዘው ወር ብቻ ከ280 በላይ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን ፈተው ወደ ሰላም አማራጭ መመለሳቸውን መንግስታዊ ምንጮች አመክተዋል፡፡
እንደ መረጃዎቹ እነዚህ ከትጥቅ ትግል የተመለሱ የታጣቂ ቡድኑ አባላት ወደ ሰላማዊ መንገድ የተመለሱት አባገዳዎች እና የአገር ሽማግሌዎች ባቀረቡላቸው የሰላም ጥሪ መሰረት ነው ተብሏል።
ለመሆኑ በታጣቂዎች በተናጥል ወይም በውስን ቡድን የመመለስ ሂደቱ በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ምን ያህል ያግዘው ይሆን?
በምስራቅ ወለጋ ዞን ከ200 በላይ ታጣቂዎች ዛሬ ቅዳሜ ትጥቅ ፈተው መመለሳቸውን ዋነኛው የክልሉመንግስታዊ የመገናኛ ብዙኃን በምስል አስደግፎ ዘግቧል።
ከትናንት በስቲያ ሐሙስ በኦሮሚያ ታጣቂዎች በስፋት ከሚንቀሳቀሱባቸው አከባቢዎች አንዱና ዋነኛው በሚባልለት ደቡባዊ የክልሉ አከባቢ በምዕራብ ጉጂ ዞን ደግሞ 23 የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታጣቂዎች ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ አማራጭ መመለሳቸው ተዘግቧል፡፡ ለኢትዮጵያ መንግስት ቅርበት ያላቸው መገናኛ ብዙሃን እና የዞኑ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን በዚህ ወር ብቻ በእነዚሁ ዞኖች ከ280 በላይ ታጣቂዎች ትጥቅ ፈተው ወደ ሰላማዊ ትግል መመለሳቸውን አመልክተዋል፡፡
መሰል ዜናዎች የተሰሙት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች በታጣቂዎች ላይ ሰፊ ወታደራዊ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን በሚገልጽበት ወቅት ላይ ነው፡፡
በኦሮሚያ ክልል ታጣቂዎች በስፋት ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ መንገድ መመለሳቸው በተነገረበት በምዕራብ ጉጂ ዞን እስከ መስከረም ወር አጋማሽ ላይ 114 ታጣቂዎች ትጥቅ መፍታታቸቸውን እንዲሁም በዚህ ዓመት በዞኑ ብቻ 500 ያህል ታጣቂዎች ከጫካ መመለሳቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት በወቅቱ ተናግረዋል፡፡
ለመሆኑ የታጣቂዎቹ በተወሰኑ ቡድኖች እና በተናጥል መመለስ በክልሉ የሚፈለገውን ሰላም ለማረጋገጥ መልካም ጅማሮ ይሆን? በክልሉ ተደማጭነት ያለው የተቃዋሚው ኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረንስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና አይመስለኝም የሚል አስተያየት ነው ያጋሩን፡፡ “የፖለቲካ ችግሩ ከምንጩ ካልደረቀና ካልተፈታ የተወሰኑ ግለሰቦች እና ቡድኖች መግባታቸው ብቻ አቅጣጫውን የሚቀይር አይመስለንም” ያሉት ፕሮፌሰር መረራ፤ እስካሁንታጣቂዎች በስፋት ገብተዋል በተባለባቸው አከባቢዎች የጸጥታ ችግሩ መሰረታዊ ተግዳሮቶች ሳይፈቱ መቀጠላቸውን አመልክተዋል፡፡ “ግጭቱ ሰውን አግቶ ገንዘብ መጠየቁ አሁንም አለ” ያሉት መረራ “በኛ በኩል ተስፋ ሰጪ ለውጥ የለም” ሲሉም ነው ሃሳባቸውን ያጋሩት፡፡
ከሁለት ወራት በፊት በመስከረም ወር አጋማሽ በሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ እና ሻምቡ ዙሪያ እንዲሁ ታጣቂዎች በገፍ ትጥቅ አስቀምጠው ወደ ሰላም መመለሳቸውን የአከባቢዎቹ ባለስልጣናት እና
መገናኛ ብዙሃን በወቅቱ በስፋት ዘግበዋል፡፡ በወቅቱም አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡት የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ መሰል ሂደቶች ግጭትን እየቀነሱ ሰላምን በዘላቂነት ለማጽናት ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡ “ታጣቂ ቡድን ተቆራርጦም ቢሆን በገባ ቁጥር ሰላም እየሰፈነ ይሄዳል” ያሉት አቶ ኃይሉ መንግስት በየትኛውም ስፍራ ለው መረጋጋት ፍጹም ነው የሚል ግምገማ ባይኖረውም ታጣቂዎች በተመለሱባቸው አከባቢዎች ላይ አንጻራዊ ሰላም እየሰፈነ መምጣቱን ግን አስረድተዋል፡፡
ፖለቲከኛ መረራ ጉዲና ግን ዘላቂ መፍትሄ የሚመጣው በዚህ ነው ይላሉ፡፡ “መንግስትም ሆኑ ታጣቂዎች ይህንን ችግር ያመጣው መሰረታዊ ነገር ምንድነው ብለው የፖለቲካ ችግሩን መፍታት ነው” በማለት ተፋላሚዎች በሰጥቶመቀበል መርህ ጥያቄዎችን መፍታት ዘላቂውን ተፈላጊ ሰላም እንደሚያመጣ አስረድተዋል፡፡
አሁን ላይ ትጥቃቸውን አስቀምጠው ስለሚመለሱትም ታጣቂዎች ከዚህ በፊት አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የኦነግ-ኦነሰ ከፍተኛ አዛዥ አማካሪ አቶ ጅሬኛ ጉደታ፤ “መንግስት አላማቸውን ረሱ ሰዎች ጋር እየተገናኘ ወደ ሰላም መልሻለሁ የሚለው” በማለት ይህንንም በፕሮፓጋንዳ ከሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ በፊት በሁለት ዙር ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) ጋር በታንዛንያ ሰላም ለማውረድ ያደረገው ጥረት ፍሬ ሳያፈራ ያለስምምነት መቋጨቱ አይዘነጋም፡፡
ስዩም ጌቱ
ታምራት ዲንሳ























