የኢትዮጵያ ክልሎች እና ከተሞች የማዘጋጃ ቤት ቦንድ ቢያወጡ ማን ያበድራቸዋል?
Description
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የሲዳማ ክልል በቁልፍ የልማት ዘርፎች ረገድ ያለባቸውን የገንዘብ እጥረት ለመቅረፍ ቦንድ በማውጣት ከገበያው የመበደር ፍላጎት እንዳላቸው የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን በቅርቡ ይፋ ያደረገው አንድ ጥናት አሳይቷል። አዲስ አበባ እና ሲዳማ ቀልባቸው ያረፈው ከፌድራል መንግሥቱ በታች የሚገኙ አስተዳደራዊ መዋቅሮች በሚያወጧቸው የማዘጋጃ ቤት ወይም የከተማ አስተዳደሮች ቦንዶች ላይ ነው።
የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 51 “ክልሎች ከውስጥ ምንጮች ስለሚበደሩበት ሕግና መመሪያ ያወጣል” የሚል ሥልጣን ለፌድራል መንግሥት ይሰጣል። “የክልል መንግሥታት ሊበደሩ የሚችሉትን የገንዘብ መጠን” የመወሰን ሥልጣን በሀገሪቱ የፋይናንስ አስተዳደር አዋጅ ለገንዘብ ሚኒስቴር የተሰጠ ነው።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የፋይናንስ አስተዳደር አዋጅ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር ለምሳሌ የብድር ሰነድ በማውጣት ከገበያው መበደርን ይፈቅዳሉ። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት የሕግ ባለሙያ ፈቃዱ ጴጥሮስ “የከተማ አስተዳደሮችም በራሳቸው አዋጅ ላይ ይኸንን ሥልጣን ሊሰጡ ይችላሉ። ክልሎችም በራሳቸው ሕጎች ላይ ይኸን ሥልጣን ለራሳቸው መፍጠር ይችላሉ” ሲሉ ተናግረዋል።
የማዘጋጃ ቤት ወይም የከተማ አስተዳደር ቦንዶች ሁለት ዐይነት ሊሆኑ ይችላሉ። የጠቅላላ ግዴታ ቦንዶች (General Obligation Bonds) የሚባሉት የሚያወጣው ወገን በሚበደረው ገንዘብ በሚሠራው ዕቅድ ሳይሆን ግብር በመሰብሰብ ሥልጣኑ አማካኝነት ባለው ዕዳ የመክፈል አቅም ላይ የሚወሰኑ ናቸው።
የገቢ ቦንዶች (Revenue Bonds) በአንጻሩ የብድር ሰነዱን የሚያወጣው ወገን በሚበደረገው ገንዘብ የሚሠራው ፕሮጀክት በሚያስገኘው ገቢ ላይ መሠረት ያደርጋሉ።
የማዘጋጃ ቤት ወይም የከተማ አስተዳደር ቦንዶች ለምን ዐይነት ሥራ ያስፈልጋሉ?
በዓለም አቀፍ ደረጃ የከተማ አስተዳደር ወይም የማዘጋጃ ቤት ቦንዶች መንገዶች፣ የመኖሪያ ቤቶች እና የሕዝብ መጓጓዣ የመሳሰሉ መሠረተ-ልማቶች ለመገንባት ገንዘብ መበደሪያ የዕዳ ሰነዶች ናቸው። ክልላዊ መንግሥታትም ይሁኑ የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች አንገብጋቢ መሠረተ-ልማቶችን ለመገንባት በዋናነት በፌድራል መንግሥት በጀት ላይ ጥገኞች ናቸው። በልማት አጋሮች አሊያም በብድር የሚሠሩ መሠረተ-ልማቶች ቢኖሩም የሕዝብን ጥያቄ በበቂ ሁኔታ የሚፈቱ አይደሉም።
የሕዝብን ጥያቄ የሚፈቱ መሠረተ-ልማቶች ለመገንባት “ሥራ ላይ ያልዋለ ካፒታል ሰብስቦ መሥራት” አንዱ አማራጭ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ፈቃዱ “እውነት ገበያው የሚፈጠር ከሆነ፤ እውነት ሕዝብ አምኖ ያለውን ገንዘብ አምጥቶ የሚገዛ ቢሆን አስፈላጊ ነው” የሚል ዕምነት አላቸው።
የሕግ ባለሙያው ክልላዊ መንግሥታት እና የከተማ አስተዳደሮች ቦንድ በማውጣት ከገበያው የሚበደሩበት ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊነት ላይ እርግጠኛ ቢሆኑም “ነገር ግን ይቻላል ወይ? ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር አቅማችን ይፈቅዳል ወይ? ለዚያ ዝግጁ ነን ወይ?” የሚሉ ጥያቄዎች ይሰነዝራሉ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ግብ የማዘጋጃ ቤት ቦንዶች ሸጦ የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ ውኃ፣ ጤና እና የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ከተማዋ የሚያስፈልጓትን መሠረተ-ልማቶች ግንባታ ማከናወን እንደሆነ ጀነሲስ አናሊቲክስ በተባለ ኩባንያ የተከናወነው እና በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን በኩል የተሠራጨው ጥናት ያሳያል። የሲዳማ ክልል በአንጻሩ የማዘጋጃ ቤት ቦንድ ማውጣት የሚፈልገው የካፒታል ወጪዎችን በተለይም የግብርና ዘርፍ ኢንቨስትመንትን ለመደገፍ ነው።
በጀነሲስ አናሊቲክስ የተሠራውን ጥናት የተመለከቱት የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪውዶክተር ሚኪያስ ሙሉጌታ በጥናቱ ከተካተቱ አራት ክልሎች እና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች “አዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ክልል ናቸው ጠንካራ የፊስካል መሠረት እና የተሻለ ፕሮፌሽናል የሰው ኃይል አላቸው” የሚል ድምዳሜ ላይ መደረሱን ተናግረዋል። ይሁንና አዲስ አበባም ይሁን የኦሮሚያ ክልል “ከዘመናዊ የካፒታል ገበያ ሒደት አንጻር የሚቀራቸው ክህሎቶች አሉ።”
የሲዳማ፣ ሶማሌ እና የአማራ ክልሎች እንዲሁም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር “የፊስካል በጀታቸው አንዳንዶቹ በፌድራል መንግሥት ዝውውር ላይ ጥገኝነት ያለባቸው እንዲሁም የተደራጀ ፋይናንሺያል ዳታ በበቂ የሌላቸው” መሆናቸውን ጥናቱን እያጣቀሱ ዶክተር ሚኪያስ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከገበያው የሚበደርባቸውን የዕዳ ሰነዶች የሚያስተዳድረው የገንዘብ ሚኒስቴር ነው። የክልል መንግሥታት በተመሳሳይ መንገድ ከገበያው መበደር ቢጀምሩ የፋይናንስ እና የኢኮኖሚ ልማት ቢሮዎች የማዘጋጃ ቤት ቦንዶችን የማውጣት እና የማስተዳደር ሥልጣን እንዲሁም ኃላፊነት ሊኖራቸው ይችላል። በሕግ ግብር የመሰብሰብ እና በጀት የማስተዳደር ሥልጣን የተሰጣቸው እነዚህ ቢሮዎች ወደ ፊት የሚመጣውን ኃላፊነት ለመወጣት ከውስብስቡ የካፒታል ገበያ ሥርዓት ጋር የሚጣጣም አቅም ያስፈልጋቸዋል።
“አጠቃላይ የካፒታል ገበያ ሥነ-ምህዳር ገና የገባንበት፤ ገና በጣም ከፍተኛ ሥራ የሚጠይቅ ነው። ውስብስብ የሆኑ የብድር መሣሪያዎች የሚሸጡ የሚገዙበት ገበያ ነው” የሚሉት ዶክተር ሚኪያስ የፋይናንስ እና የኢኮኖሚ ልማት ቢሮዎች “የተለየ ተቋማዊ ጥናካሬ ያስፈልጋቸዋል” የሚል አቋም አላቸው።
“አደጋን (Financial risk) መረዳት እና መተንተን፤ የመረጃ አሰጣጥ በተለይም ከኢንቨስተሮች ጋር፣ ከሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር መረጃን በአግባቡ ተንትኖ፣ አጠናቅሮ የማቅረብ ሁኔታ፣ የብድር አሰጣጥ እና የመመለስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የሰው ኃይል የመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ በበቂ ሁኔታ መዘጋጀት የሚጠይቅ ነው” ሲሉ አብራርተዋል።
የክልል መንግሥታት ወይም የከተማ አስተዳደሮች ሊያወጧቸው የሚችሉ የዕዳ ሰነዶችን በማስተዳደር ረገድ “የአቅም ውስንነት” ሊኖር እንደሚችል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ፈቃዱ ጴጥሮስ ይስማማሉ።
“ለምን ዘርፍ ነው የምትበደረው? ምን ያህል ነው የምትበደረው? ተበድረህ እንዴት ነው የምትከፍለው? የሚሉት ጉዳዮች በጣም ጠንካራ እውቀት እና ትንታኔ የሚጠይቁ ናቸው” የሚሉት የሕግ ባለሙያው አቶ ፈቃዱ “እንዲሁ ዝም ብለህ ተነስተህ አትበደርም። ያውም ከሰፊው ሕዝብ ማለት ነው” በማለት የጉዳዩን ክብደት በአጽንዖት አስገንዝበዋል።
የማዘጋጃ ቤት ወይም የከተማ አስተዳደር ቦንዶች ማን ይገዛል?
የፌድራል መንግሥት በካፒታል ገበያ በኩል እንደሚሸጣቸው የዕዳ ሰነዶች ሁሉ የማዘጋጃ ቤት ቦንዶች በመግዛት ሊያበድሩ የሚችሉት ጥሪት ያላቸው ባወረቶች እና ተቋማዊ ኢንቨስተሮች ይሆናሉ። በመሰል የብድር ሥርዓቶች ለመሳተፍ ግን በአጠቃላይ ሀገራዊ ሁኔታው እምነት ሊኖራቸው እንደሚገባ አቶ ፈቃዱ ጴጥሮስ ተናግረዋል። ዜጎች እና ተቋማት በረዥም ጊዜ የዕዳ ሰነዶች ግብይት ለመሳተፍ “የሀገር መረጋጋት እና የመንግሥት መጽናት” ታሳቢ ይደረጋሉ።
“ኢትዮጵያ መንግሥት ዜጎች የጣሉበትን ዕምነት የመሸርሸር ልማድ የሌለባት ሀገር አይደለችም። መንግሥት ሙሉ በሙሉ ዕምነት የሚጣልበት [አይደለም።] እንደ ግለሰብ opportunist ሆኖ ውሎችን ያለመፈጸም ልማዶች አልፎ አልፎ ይታያሉ” የሚሉት የሕግ ባለሙያው ይህ ሊዘረጋ በታቀደው የብድር ሥርዓት “ዜጎች ዕምነት እንዳይጥሉ ሊያደርግ ይችላል” የሚል ሥጋቸውን ለዶይቼ ቬለ አጋርተዋል።
ቦንዶቹን የሚያወጡ ተቋማት በመክፈል አቅም እና ፍላጎት ረገድ ግለሰቦችም ይሁኑ ተቋማዊ ኢንቨስተሮች የሚኖራቸው ዕምነት ሌላው ቁልፍ ጉዳይ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የዋጋ ንረትን ጨምሮ የማክሮ ኢኮኖሚው አጠቃላይ ጤንነት “ስኬቱንም ሆነ ውድቀቱን“ እንደሚወስን ዶክተር ሚኪያስ ያምናሉ።
ዶክተር ሚኪያስ “አሁን ሀገሪቱ ውስጥ ያለው የዋጋ ግሽበት፣ የብር የመግዛት አቅም፣ የዕዳ ሽግሽግ ሁኔታዎች እጅግ መሠረታዊ ጉዳዮች ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል። ኢትዮጵያውያን ባለሐብቶችም ይሁኑ ከውጭ የሚመጡ ኢንቨስተሮች “እዚህ ገበያ ውስጥ ገብተው ለመሳተፍ እና በካፒታል ገበያ ውስጥ የራሳቸውን ድርሻ ለመወጣት የማክሮ ኢኮኖሚው ጤንነት ወሳኝ ነው።”
ዶክተር ሚኪያስ የሀገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሳያዎች ወይም አመልካቾች “የተረጋጉ ካልሆኑ፤ ለረጅም ጊዜ የሚቀመጡ ቦንዶችን የመግዛት ሁኔታቸው፤ አጠቃላይ በዚህ ሁኔታ ውስጥ በካፒታል ገበያ የመሳተፍ [ዕድላቸው] ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው” የሚል አቋም አላቸው። “ቦንድ ከማውጣት ወይም ደግሞ ካፒታል ገበያው ላይ በደንብ ከመሥራታችን በፊት የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ ሥርዓትን መፍጠር አስፈላጊ ነው” በማለት ተናግረዋል።
መንግሥት ከፍተኛ ተስፋ የጣለበት የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ የጥቂት ባንኮች እና የግምጃ ቤት ሰነዶች በማሻሻጥ በሐምሌ 2017 በይፋ ወደ ሥራ መግባቱን ቢያበስርም የነቃ ግብይት እስኪፈጠር ገና ጊዜ የሚወስድ ይመስላል። ግብይቱን ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች የሚቀላቀሉበት ሒደት ገና በይፋ ባይገለጽም አቶ ፈቃዱ ጴጥሮስ ግን ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ይመክራሉ።
“ይኸን ነገር መሞከሩ መልካም ነው። የሕግ ማዕቀፎች ይዘጋጁ” ይበሉ እንጂ አቶ ፈቃዱ የተሻለ አቅም አለው ተብሎ በሚታመነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተጀምሮ “ቀስ እያለ” ወደ ክልል መንግሥታት ቢስፋፋ ይመርጣሉ። የሕግ ባለሙያው እንደ ኢትዮ-ቴሌኮም ያሉ የመክፈል አቅም ያላቸው ኩባንያዎች በሚያወጧቸው ኮርፖሬት ቦንዶች ገበያውን ማለማመድ ሌላው አማራጭ ሊሆን እንደሚችልም ተናግረዋል።
አቶ ፈቃዱ “እንዲያው ዝም ብሎ በተፎካካሪነት ሁሉም የከተማ አስተዳደር ገብቶበት ነገርየው እንዳይበላሽ ጥንቃቄ ተደርጎ በሒደት እየተማርን ብንሔድ” የሚል ምክር አላቸው።
























