የካሜሩን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለ43 ዓመታት ሀገሪቱን የመሩትን የፓል ቢያን ሥልጣን ያራዝም ይሆን ?
Description
ማዕከላዊ አፍሪቃዊቷ ሀገር ካሜሩን ነገ እሁድ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ታካሂዳለች። በዚህ ምርጫ ለ43 ዓመታት ካሜሩንን የመሩት የ92 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ፖል ቢያ ለ8ተኛ የስልጣን ዘመን መወዳደራቸው ትኩረት ስቧል።ቢያ ከተመረጡ ወደ 100 ዓመት እስኪጠጉ ድረስ ስልጣን ላይ ሊቆዩ ይችላሉ። የተከፋፈሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከካሜሩን ከፍተኛው የሥልጣን መንበር አልላቀቅም ያሉትን የቢያን የስልጣን ዘመን ለመግታት እየተጣጣሩ ነው።
ቢያ የምርጫ ዘመቻ ሲያካሂዱ ብዙ አልታዩም፤ ይህም ከጤና ችግር ጋር ይያያዛል እየተባለ ነው። በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ግን ማውራ በተባለችው ሰሜናዊ ከተማ ዋነኛ የሚባል የምርጫ ዘመቻ አካሂደዋል። በዚሁ ወቅትም የአካባቢ ፀጥታን መልሶ ለማስፈን፣ የወጣት ስራ አጥነትን ለመቀነስ እና መሠረተ ልማቶችን ለማሻሻል ቃል ገብተዋል። ለፖል ቢያ፣ ምርጫውን ማሸነፍ፣ ሥልጣናቸውን ለተጨማሪ ዓመታት ማራዘም ብቻ ሳይሆን የአገዛዙ ስልጣን አሁንም ሕጋዊ መሆኑን ለአገር ውስጥ እና ለዓለም አቀፍ ታዳሚዎች ማረጋገጥም ነው።
ዋነኛው የቢያ ተፎካካሪ ማውሪስ ካማቶ ነበሩ። ይሁንና የካሜሩን ምርጫ ቦርድ የካማቶን ፓርቲ የእጩዎች ደንቦችን ተላልፏል ሲል ከምርጫው ሰርዟቸዋል። ተችዎች እርምጃውን ፖለቲካዊ ምክንያት ያለውና ለነጻ ትክክለኛና ግልጽ ምርጫ ተስፋ የሚያስቆርጥ ብለውታል። የካሜሩን የመንግስት አስተዳደርና የምርጫ ጉዳዮች ተንታኝ ቭዮሌት ፎኩም ህዝቡ በምርጫው ላይ ያለው እምነት ቀንሷል ሲሉ ለዶቼቬለ ተናግረዋል።«እንደሚመስለኝ አሁንም የህዝቡ እምነት በጣም ዝቅተኛ ነው። ምክንያቱም አሁንም ዜጎች ሂደቱን ምናልባት ሌላ ከሚተካበት እውነተኛ የውድድር ክስተቶች ይልቅ ይበልጥ የይስሙላ አድርገው ይመለከቱታል።»
ካሜሩን ለለውጥ ዝግጁ ናትን?
አንጋፋውን ፖለቲከኛ ቤሎ ቡባ ማይጋሪን ለመደገፍ፣ ተቃዋሚዎቹ አኬሬ ሙና እና አቴኪ ሴታ በቅርቡ ራሳቸውን ከምርጫው አግለዋል። ይሁንና ይህ እርምጃቸው እውነተኛ ለውጥ ማምጣት አለመምጣቱ የተቀላቀለ ስሜት ፈጥሯል። ሙና፤ ማይጋሪን በመደገፍ በጎርጎሮሳዊው መስከረም 28 ቀን ከምርጫው ራሳቸውን አግለዋል።ብዙም ሳይቆይ ሴታም ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩትን የ78 ዓመቱን ማይጋሪን በእጩ ተወዳዳሪነት አጸደቁ። ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንዲት ነጋዴ ነገሮች ከባድ እየሆኑ ቢሄዱም ሁኔታዎች ይሻሻላሉ ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ለዶቼቬለ ተናግረዋል።
«ነገሮች ይሻሻላሉ ብለን ተስፋ እንደርጋለን። የሀገሪቱ ሁኔታ እየተባባሰ ነው። ምርጫውን የሚያሸንፈው ሁኔታዎቹን፣ ዜጎች የሚጋፈጡዋቸውን ችግሮች መመልከት አለበት።ስለዚህ ለምርጫ መውጣት ያለብን ምክንያት ይኽው ነው።»
የደኅንነት ስጋቶች በእንግሊዘኛ ተናጋሪዎች
ይህ ጉጉት ግን በተግባር ከሚታዩት ፍራቻዎች ጋር ይጋጫል። ገንጣዮች ለዓመታት እንቅስቃሴዎችን በሚገድቡባቸው እንግሊዘኛ ተናጋሪዎች በሚገኙበት በካሜሩን ሰሜን ምዕራብና ደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች ህጻናትን ከትምህርት ገበታ አስቀርተዋል። አሁንም በምርጫ ቀን ተመሳሳይ ዘዴዎችን ሊጠቀሙ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ። ፎኩም አሁን የተባባሰውን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በምርጫው እለት ድምጽ ለመስጠት መውጣት መቻላችንን መጠየቅ ጀምሬያለሁ ብለዋል። ሁሉ ነገር ከተዘጋጋ መኪና ካልተንቀሳቀሰ ለመምረጥ ወደ ምርጫ ጣቢያ እንዴት እንሄዳለን ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ከዚህ ሌላ የተቃዋሚዎች ድክመት ሌላው በተደጋጋሚ የሚነሳ ጉዳይ ነው። የፖለቲካው ሜዳ ቢያ እንዳይመረጡ የማድረግ ጥንካሬ አለው ወይ ተብለው የተጠየቁት ፎኩም ፣በድፍረት የለውም ፣ በቂ ጥንካሬ ያላቸው አይመስለኝም ብለዋል። በቅርብ ጊዜ ከተደረጉት ስምምነቶች በስተጀርባ ያለውን የፖለቲካ ገበያ በማንሳትም አኬሬ ሙና እና አቴኪ ሲታ ማጋሪን ያጸደቁት ካሸነፉ ለነርሱ የሚኒስትርነት ቦታ እንዲሰጣቸው ወይም ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ ባቀረቡት ቅድመ ሁኔታ መሆኑንም ፎኩም ጠቁመዋል።
የወጣትና የሴት መራጮች አዲስ ኃይል
እንዲህ ያለው ድርድር “ስልጣን ፈላጊ ሰዎች የህዝቡን ጥቅም በተጨባጭ ከመወከል ይልቅ የራሳቸውን ጥቅም ለማርካት ይፈልጋሉ” የሚለውን ሃሳብ እንደሚያጠናክርም ተናግረዋል።
ሴቶችና ወጣት መራጮች የምርጫውን ውጤት ሊወስኑ ይችላሉ። ምንም እንኳን ሁኔታው የደበዘዘ ቢሆንም በወጣትና በሴት መራጮች ዘንድ አዲስ ኃይል ይታያል። ሄርሚነ ፓትሪሽያ ንዳም ንጆያን የመሳሰሉ እጩ ተወዳዳሪዎችም የዚህ ማሳያ ናቸው። እጩ ተወዳዳሪዋ ወንዶች የሚያመዝኑበትን የካሜሩን የስልጣን መዋቅር ጥሰው ለመግባት እየሞከሩ ነው። ወጣቶችን ፣ከተሜ መራጮችንም ያነጋግራሉ። ሆኖም ለምርጫ ዘመቻ ከሚሰጠው ገንዘብ ውስንነት እስከ አነስተኛ የብሔራዊ የመገናኛ ብዙሀን ሽፋን ድረስ ከባድ መሰናክሎች ከፊታቸው ተጋርጦባቸዋል። በካሜሩን ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩት ሬቤካ ኤኖንቾንግ ከምርጫው በፊት ያዩት የህዝቡ ስሜት ተለይቶባቸዋል።
«አሁን የማየውን ዓይነት ኃይል እስካሁን አይቼ አላውቅም። በእውነት በጣም የተለየ ስሜት ነው የሚታየው። ካሜሩናውያን ተሰላችተዋል። በቅቷቸዋል። እናም ለውጥ ይፈልጋሉ። አሁን ነው የሚፈልጉትም ።ይህ በማንኛውም ደረጃ በሚገኝ ኅብረተሰብ ውስጥ አለ። በጎዳና ላይ ከሚገኙ ህጻናት አንስቶ እስከ ትላልቅ ነጋዴዎች እና ባለሥልጣናት ድረስ ።እርግጥ ነው፣በግልጽ አይናገሩትም። ሆኖም ሁሉም ሰልችቶታል፤ከፓውላ ቢያ ጋር ሌላ ሰባት ዓመት ለመቆየት አልተዘጋጀም። »
ፎኩም እንደሚሉት ምንም እንኳን ከካሜሩን ህዝብ 51 በመቶው ሴቶች ቢሆኑም፤ እጩ ተፎካካሪዋ የነርሱን ድጋፍ አላገኙም። በተንታኞች አስተያየት የአዳም ንጆያ ዘመቻ ስር የሰደደ የአካታች ፖለቲካ ጉድለት እንዳለ የሚያሳይ ነው። በመገናኛ ብዙሀን እኩል እድል ከሌለ ተቃዋሚዎች ከይስሙላ ዘመቻ ባሻገር የትም ሊደርሱ አይችሉም።ሆኖም ለተቃዋሚዎች አንድ እጩ ጠንካራ ሁለተኛ ደረጃ ቢያገኙ እንኳን ቢያገኝ እንደ ስኬት ይቆጠራል። ለፎኩም፣ የመራጮች ቁጥር በፀጥታ እጦት ወይም በጭፍን ጥላቻ ምክንያት ካነሰ ምርጫው የተሀድሶ መንገድ ሳይሆን “የይስሙላ” ነው የሚለውን ግንዛቤ ያጠናክራል። ነገር ግን መራጮች እንቅፋቶችን ከተቃወሙ ምርጫው ያልተጠበቀ ለውጥ ማምጫ መንገድ ሊሆን ይችላል።
አንድሪው ቫሲከ / ኂሩት መለሰ
ፀሐይ ጫኔ
የኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ አማጽያን የመንግስት ግልበጣ ዛቻ
በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ከሚንቀሳቀሱት አማጽያን AFC M23 ከተባለው የአማጽያን ቡድን መሪዎች አንዱ የሀገሪቱን ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ችሴኬዲን እንገለብጣለን ሲሉ ዝተዋል። የአማጽያኑ መሪ ኳታር ውስጥ በመንግስትና በአማጺው በM23 መካከል አዲስ ንግግር ሊጀመር ጥቂት ሲቀረው ለሰነዘሩት ዛቻ ኪንሻ በበኩልዋ በብሔራዊ ጦሯን ጥንካሬ እንደምትተማመን መልሳለች። ከምሥራቅ ኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ የተወሰነውን ክፍል የሚቆጣጠሩት አማጽያን በአካባቢው ከ7ሺህ በላይ አዲስ ምልምል ተዋጊዎችን አስፍረዋል። ቡድኑ ባወጣው መግለጫ ከ9ሺህ በላይ የሚሆኑት ባለፈው ሳምንት ስልጠናቸውን ያጠናቅቃሉ ተብሎ ይጠበቅ ነበር።
የኮንጎ ወንዝ ኅብረት በምኅጻሩ AFC የተሰኘው ይኽው ቡድን በቀድሞው የኮንጎ ብሔራዊ የምርጫ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት የሚመራ የኮንጎ አማጽያን ኅብረት ነው። ትልቁ ጉልበቱም «የመጋቢት 23 ንቅናቄ» ወይም በምህጻሩ M23 የተባለው ኃይል ነው። ቡድኑ ከጎረቤት ሩዋንዳ ድጋፍ በማግኘት ይከሰሳል።
በቻንዙ ሰሜን ኪቩ ክፍለ ሀገር በተካሄደው በአዳዲሶቹ ተዋጊዎች የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ የቡድኑ ወታደራዊ መሪ ጀነራል ሱልጣኒ ማኬንጋ አማጽያኑ« መጥፎ አገዛዝ» ያሉትን የኪንሻሳን መንግሥት ለመገልበጥ ቆርጠው መነሳታቸውን ተናግረዋል። ይሁን እንጂ እየጨመረ የመጣው የጦርነት ንግግር በዚህ ሳምንት እንደገና እንዲቀጥል በተቀጠረው የሰላም ድርድር ላይ ቀላል ተጽእኖ የሚያሳድር ብቻ ሊሆን ይችላል ሲሉ ተንታኞች ገልጸዋል።
በጉዳዩ ላይ ዶቼቬለ ያነጋገራቸው የክራይስስ ግሩፕ የምስራቅ ኮንጎ ጉዳዮች ተንታኝ ዋንስፎር ሴማቱምባ የM23 አማጽያኑ ዛቻ አዲስ እንዳይደለ ፣ መንግሥትን መገልበም የረዥም ጊዜ ግባቸው መሆኑን ገልጸው ሆኖም በቀድሞው ፕሬዝዳንት በጆሴፍ ካቢላ ካባናጅ ላይ ሰሞኑን መፈረዱ ግን የዶሃውን ሂደት ሊያበላሽ እና መጠነ ሰፊ ጦርነት እንደገና ሊያስጀምር ይችላል።» ሲሉ ስጋታቸውን ተናግረዋል።
ከጥቂት ቀናት በፊት አንድ የኮንጎ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ካቢላን በከፍተኛ የሀገር ክህደት እና የጦር ወንጀሎች ጥፋተኛ ሲል በይኖባቸዋል። ካቢላ በሴራና መንግሥትን ለመገልበጥ በማቀድም ጥፋተኛ ተብለዋል። ከጎርጎሮሳዊው 2001 እስከ 2019 በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገችውን የኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክን የመሩት አሁን በስደት ደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩት ካቢላ ግን ክሶቹን በሙሉ አስተባብለዋል።
ከቻተም ሀውስ ተንታኝ አሌክስ ቪነስ የአማጽያኑ ቡድን ቢያስፈራራም አቅም ግን የለውም ብለዋል። «M23 በመደበኛነት የኪንሻሳውን የችሴኬዴን አስተዳደር የመገልበጥ እቅድ አለኝ ሲል ያስፈራራል። እውነታው ግን እነርሱ ከዋና ከተማዋ በጣም ርቀው ነው የሚገኙት። የአቅርቦት ሰንሰለትም ሆነ ኪንሻሳ የመግባት አቅሙ የላቸውም። ስለዚህ ይህን፣ ቁም ነገር ብዬ አልወስደውም።»
የፕሬዝዳንት ችሴኬዲ ፓርቲ «አንድነት ለዴሞክራሲ እና ለማኅበራዊ እድገት» በምህጻሩ UDPS፣ የM23 ዛቻ አስደንጋጭ እንዳይደለ ገልጾ፤ ፕሬዝዳንት ችሴኬዲም« ከኪጋሊም ሆነ ከሌላ ቦታ የሚገኙ በርቀት የሚቆጣጠሩዋቸው አሻንጉሊቶች» ሲሉ በገለጹዋቸው አይገለበጡምም ብሏል።ከዚሁ ጋር መንግስትና ጦሩ ዝግጁ፣ ህዝቡም ቆራጥ መሆኑን ፓርቲው ጠቅሶ አማጽያኑንም እንደመስሳቸዋለን ሲል ለዶቼቬለ ተናግሯል።
በጉዳዩ ላይ ለዶቼቬለ አስተያየታቸውን የሰጡት ኦታዋ ካናዳ ከሚገኘው የሴንት ፓውል ዩኒቨርስቲ የግጭት ጥናት ትምሕርት ክፍል ኢቮን ሙያ እንዳሉት ሁለቱ ወገኖች ሰሞኑን እነዚህን መግለጫዎች የሚሰጡት ከድርድሩ በፊት የየበኩላቸውን አቋም ለማጠነከር ነው ።
«ዛሬ ጉዳዩ ይህ ነው። ምክንያቱም ማየት እንደምንችለው ግጭቶች እየተካሄዱ ነው። ዋነኛ ተዋናዮቹ ብዙውን ጊዜ በድርድሩ ጠረጴዛ ላይ አቋማቸውን ለማጠናከር ይሞክራሉ»
ሌላው ተንታኝ ሄንሪ ፓሲፊክ ማያላ የሰጡት አስተያየት ሁኔታው ባለበት ተራዝሞ ይቀጥላል ወደሚለው ያዘነብላል ።በሩዋንዳ ይደገፋሉ የሚባሉት አማጽያኑ የሰሜን ኪቩ ክፍለ- ግዛት ዋና ከተማ ጎማን እና የደቡብ ኪቩ ዋና ከተማ ቡካቩን ተቆጣጥረዋል። ሌሎች የያዟቸው ከተሞችም አሉ።
ማርቲና ሽቪኮቭስኪ / ኂሩት መለሰ
ፀሐይ ጫኔ