በኢትዮጵያ ኬንያ እና ሶማሊያ ድርቅ ሊከሰት ይችላል ተባለ
Description
የኢጋድ የአየር ንብረት ትንበያ እና ትግበራ ማዕከል በእንግሊዝኛው ምህፃሩ (ICPAC) ሰሞኑን ይፋ ባደረገው የአየር ንብረት ትንበያ መሰረት እስከ ጎርጎሪያኑ ጥር 2026 ድረስ ከመደበኛ በታች የሆነ የዝናብ መጠን የሚጠበቅ በመሆኑ፤ በደቡብ ምስራቅኢትዮጵያ፣ ምስራቃዊ ኬንያ እና ደቡባዊ ሶማሊያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን አደጋ ላይ የሚጥል የከፋ ድርቅ ሊያጋጥም ይችላል።
በአዲሱ የአየር ንብረት ትንበያ፤ የዝናብ ወቅት ከገባበት ጊዜ አንስቶ በቀጠናው ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ደረቃማ ሁኔታዎች እየታዩ ሲሆን ይህንን ተከትሎ የአፈር እርጥበት እጥረት እና የእጽዋት መጠውለግ እየጨመረ መሆኑን ጠቁሟል።ከነሐሴ እስከ ጥቅምት ባሉት ወራት በመደበኛ የዝናብ መጠን መረጃ ጠቋሚ ትንተና መሰረት በአብዛኛው በአፍሪቃ ቀንድ ምስራቃዊ ክፍል ጉልኅ የሆነ የዝናብ እጥረት መኖሩን አመልክቷል። የደን ሥነምህዳር ባለሙያው ዶክተር ይተብቱ ሞገስ እንደሚሉት እየጨመረ ከመጣውየአየር ንብረት ለውጥ አኳያ ሁኔታው የሚጠበቅ ነው።
ሁኔታውን እንዲባባስ ያደረገው የላ ኒና ክስተት
እንደ ትንበያው ሁኔታውን እንዲባባስ ያደረገውም የቀጠለው የላ ኒና ክስተት እና የህንድ ውቅያኖስ ዲፖሌ (አይኦዲ) የሚባለው አሉታዊ ተፅዕኖ ነው። ይህ ክስተት የአካባቢውን የዝናብ መጠን የመገደብ ተደጋጋሚ ታሪክ እንዳለውም ማዕከሉ አመልክቷል።
አሁን የሚታየው የባህር ወለል የሙቀት መዛባት በጎርጎሪያኑ በ2010 እና በ2022 ዓ/ም በኬንያ፣ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በተከሰተው እና ከፍተኛ ጉዳት ባደረሰው ድርቅ ወቅት የታዩ ምልክቶች ናቸውም ብሏል።
አሉታዊው የህንድ ውቅያኖስ ዲፖሌ (IOD) ተፅዕኖ እስከ ታኅሣስ 2025 ድረስ የሚቆይ ሲሆን፤ የላኒና ሁኔታዎች ግን እስከ የካቲት 2026 ድረስ ሊቆዩ እንደሚችል ትንበያው አመልክቷል። ይህም ቀድሞውንም ደካማ የነበረውን የአካባቢውን ሁኔታ ሊያባብሰው ይችላል።
የዓየር ንብረት ለውጥ ላለፉት 30 ዓመታት ከፍተኛ የምዕተ ዓመቱ ችግር ሆኖ መቀጠሉን የገለፁት ባለሙያው፤ ቻይና፣ አሜሪካ እና አውሮፓ ለዓለማችን የካርቦን ልቀት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳላቸው ገልፀዋል። ነገር ግን አፍሪቃ በችግሩ በከፍተኛ ሁኔታ እየተጎዳች መሆኑን አመልክተዋል። ከነዚም መካከል የምስራቅ አፍሪቃ ተደጋጋሚ ድርቅ አንዱ መሆኑን አስረድተዋል።
ጉዳት በሰዎች እና በእንስሳት ላይ
እንደ ትንበያው ከህዳር 2025 እስከ ጥር 2026 ከመደበኛ በታች የሆነ ዝናብ የመቀጠል እድሉ ከፍተኛ ሲሆን፤ ይህም በክልሉ በጣም ወሳኝ በሆኑ ዘርፎች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ማዕከሉ አያይዞም በግብርና እና በምግብ ምርቶች ላይ ተጨማሪ እጥረት ሊያጋጥም እንደሚችል አስጠንቅቋል። በግጦሽ እና በውኃ መቀነስ ሳቢያ የእንስሳት መኖ በከፍተኛ ሁኔታ ሊቀንስ እንደሚችል ጠቁሟል። የውሃ አቅርቦት መቀነስ ከእንስሳት ባሻገር በተጋላጭ ህዝቦች ላይ የጤና እና የአመጋገብ ችግሮችን ከፍ ሊያደርግ እንደሚችልም አመልክቷል። ኅብረተሰቡ ካለፈው የድርቅ ዑደቶች ሙሉ በሙሉ ባላገገምበት በዚህ ወቅት ተጨማሪ የዝናብ እጥረት መከሰቱ የምግብ ዋስትና እጥረትን ሊያፋጥን እንደሚችልም ተጠቁሟል።
ቅድመ ዝግጅት ያስፈልጋል
ማዕከሉ መንግስታት፣ እና ግብረሰናይ ድርጅቶች ችግሩ ከመከሰቱ በፊት አስቀድመው የዝግጅት እርምጃዎችን እንዲያጠናክሩ አሳስቧል። ከኮፕ 27 ወደህ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአየር ንብረት ተጎጂ የሆኑ አዳጊ ሀገራትን ለመደገፍ የተቋቋመ ፈንድ መኖሩን የገለፁት ባለሙያው፤ ነገር ግን እስካሁን ሥራ ባለመጀመሩ ችግሩን የመወጣት ጫና በመንግስታት እና በግለሰቦች ትከሻ ላይ የወደቀ መሆኑን አመልክተዋል። በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራርን አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ፀሐይ ጫኔ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
























