ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር ኢድሪስ ሲታወሱ
Description
“ሰው ሁኑ፤ከሃይማኖትም ከዘርም ሰው መሆን ይቀድማል” “የሰው ልጅ እኩል ነው አባቱም አደም ነው እናቱም ሀዋ ነች የተፍጠሩትም ከአፈር ነው“ እነዚህ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር ኢድሪስ ከሚታወሱባቸው በርካታ የሰላም መልዕክቶቻቸው ጥቂቶቹ ናቸው።
በፍቅር እና በአንድነት አስትምህሮታቸው የሚታወቁት ታላቁ የእስልምና ሃይማኖት አባት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር ኢድሪስ የቀድሞው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በ94ዓመታቸው ነበር ጥቅምት 09 ቀን 2018 ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ።ለተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ አስከሬን በኑር መስጂድ የሶላተል ጀናዛ ሥነ ስርዓት ከተፈጸመ በኋላ፣ ታላቁ ብሔራዊ የሽኝት መርሐ ግብር የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ታዪ አፅቀ ሥላሴ በተገኙበት በሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂድዋል ።
በሚሊኒየም አዳራሽ በተደርገው የሽኝት መርሐ ግብር ላይ ንግግር ያደርጉት ፕሬዚዳንት ታዪ አፅቀ ሥላሴ «አትዪጵያ ዛሪ ታላቅ ሰው አጥታለች ሲሉ መልዕክት አስተላልፍዋል
«የኔ ብቻ አባት አልነበሩም» ያሉት ልጃቸው አህመድ ኡመር የአባቱ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ አስክሬን በከብር በመሸኘቱ ምስጋና አቅርበዋል፤መልዕክትም አስተላልፈዋል።
በተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ አስክሬን ሀገራዊ የክብር ሽኝት መርሃ ግብር ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖትን ጨምሮ የተለይዩ የሃይማኖት መሪዎችና ከፍተኛ የመንግስት ሀለፊዎች ተገኝተዋል።
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ከአባታቸው አቶ ኢድሪስ ዘለቀ እና ከእናታቸው ወ/ሮ መነን ሽፋው፣ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1924 በወሎ ቦረና ገነቴ አካባቢ ልዩ ስሙ “ዳሎታ” በተባለ መንደር ተወለዱ። እድሜያቸው ለትምሀርት እንደደርሰ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር “ገነቴ ዳሎታ” ከሸህ ከማል እሸቴ የቅዱስ ቁርኣን ከፊል ነቢብ ተማሩ። “ለገሂዳ” ከሸህ አሊ ገመች የቅዱስ ቁርኣን ነቢብ፣ ሥነ መለኮት ትምህርት ገበዩ። በዳሎታ እና “ጥላንታ” ከሸህ ከማል ሸህ አሊ አደም እና ከሸህ ዩሱፍ የሥነ ሕግ ዕውቀት አጠናቀቁ።
በዕውቀት መምህሮቻቸው ከ1958፣ እስከ 1960 ከሦስት መምህሮቻቸው “የመምህርነት ፈቃድ አገኙ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ከ1960 ጀምሮ እስከ መስከረም 2018 ድረስ በአንዋር እና በኑር መስጅዶች፣ በበኬ እና በሰፈራ አካባቢ ባቋቋሟቸው የዕውቀት ማዕከላት ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል የመጡ እልፍ አዕላፍ ዕውቀት ፈላጊዎችን ያሰተማሩ ነበር፡፡
በ1967 የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጠቅላይ ም/ቤት ሲቋቋም ከቀዳሚ አባላት መካከል በመኾን በተቋም ግንባታው ሂደት እስከ 2014 ድረስ ደማቅ አሻራ አስቀምጠዋል፡፡ ለተቋሙ ሕጋዊ ተክለ-ሰውነት በማጎናጸፍ ጥረት ውስጥም የጎላ ስኬት አስመዝግበዋል፡፡ የኢስላማዊ ባንክ፣ ሚዲያዎች፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እንዲመሠረቱና እንዲስፋፉ በማበረታታት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
እሳቸው የሀይማኖት አጥር ሳይገድባቸው የሁሉም አባት ነበሩ ስትል ለዶቼቨሌ የተናገረችው ጋዜጠኛ መስከረም ጌታቸው «ሁሉም የኔ አባት የሚላቸው ሲናገሩ የሚሰሙ ናቸው ስትል ትገልፃቸዋለች። በ1959 ወደ አዲስአበባ ከአቀኑበት ጊዜ ወዲህ ደግሞ፤ ከ1960 ጀምሮ በኑር መስጅድ ለ16 ዓመታት በምክትልነት እና ለ3 ዓመታት በዋና ኢማምነት በ1967 የቀዳሚው የእስልምና ጉዳይ ጠ/ም/ቤት መስራች አባል ሆነው ሰርተዋል የቀዳሚው የኢትዮጵያ ዓሊሞች ጉባኤ ሰብሳቢ የቀዳሚው የኢትዮጵያ ዓሊሞች የፈትዋ ኮሚቴ መስራችና አባል ነበሩ የሐገር አቀፍ የዑለማ ጉባኤ ሰብሳቢና ሙፍቲ የነበሩ ሲሆን በዚሁ ወቅት በዐስራ አንድ ዓመታት ውስጥ በ58 የኢትዮጵያ ከተማዎች ተዟዙረው በሙስሊሞችና በሙስሊሞች እንዲሁም በሙስሊሞችና በሌሎች ወገኖች መካከል ከ130 በላይ ለቅራኔና ለግጭት የጋበዙ አጀንዳዎችን እልባት መስጠት ችለዋል፡
፡የአዲስአበባ የእስልምና ጉዳዮች ጠ/ም/ቤት ምክትል ሰብሳቢና ለዘጠኝ ዓመታት ዋና ሰብሳቢ እንደዚሁም የኢፌድሪ የእስ/ጉ/ጠ/ም/ቤት የሐጂ እና ዑምራ ዘርፍ እንዲሁም የዳዕዋና የትምህርት ዘርፍ ተጠሪ .በ2010 በተቋቋመው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ .ከ2011-2014 የኢትዮጵያ የእስ/ጉ/ጠ/ም/ቤት ፕሬዝደንትበ2011 የ አንጋፋው የአዲስ አብባ ዪንቨርስቲ የክብር ዶክትሪት ተሰጣቸው። ከዚህ በተጨማሪም በብሔራዊ የሰላም፣ የዕርቅ፣ የሽምግልና፣ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ኮሚቴዎች እና ቡድኖች አባል በመሆን ሀገር በፈለጋቸው ጊዜ ሁሉ አገልግለዋል።.
ሀና ደምሴ
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ