የትግራይ ክልል ኃይሎች «ተቃውሞው ስህተት ነው በማለት ይቅርታ ጠየቁ ሲሉ የክልሉ መንግሥት እና የሕወሓት ሚዲያዎች ዘገቡ
Description
ባለፈው ሳምንት ሰኞ በመቐለ መንገድ በመዝጋት የጀመረውየትግራይ ክልል ኃይሎች አባላት ሰልፍና ተቃውሞ ሰሞኑን ሙሉ በተለያዩ የትግራይ ከተሞች ቀጥሎ ሰንብቷል። በመቐለ፣ ሞኳኒ፣ ውቅሮ፣ ዓዲግራት እና ሌሎች ከተሞች ተቃውሟቸውን ሲገልፁ የሰነበቱትየትግራይ ኃይሎችአባላት በዋነኝነት የደሞዝ እና ጥቅማጥቅም ጥያቄዎች ሲያቀርቡ፥ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ተቃውሞዎች ሲያሰሙ ነበረ።
ሰሞኑን ሙሉ የተቃውሞ ሰልፎቹ ሲደረጉ ያልዘገቡት የትግራይ ክልል መንግስት ሚድያዎች እንዲሁም የህወሓት ልሳናት ሰልፉ የሚኮንን እና የሰራዊት አባላቱ ይቅርታ ስለመጠየቃቸው የሚያመለክቱ መረጃዎች በትላንትናው ዕለት አሰራጭተዋል።
ተቃውሞው የጀመሩት በመቐለ ያሉየትግራይ ክልል ሐይሎች አባላት በትላንትናው ዕለት በመቐለ ሓወልቲ ሰማእታት አደራሽ ሰብሰባ ያደረጉ ሲሆን፥ ከትግራይ ሐይሎች ከፍተኛ አዛዦች መካከል የሆኑት ጀነራል ዮሐንስ ወልደጊዮርጊስ የተቃውሞ ሰልፎቹ እና መንገድ የመዝጋት እርምጃዎች አውግዘዋል።
በሠራዊቱ አባላቱ የተጠየቁ የጥቅማጥቅም እና ደሞዝ ጥያቄዎች ግን ተቀባይነት አላቸው፣ የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደርም ምላሽ ይሰጥበታል ብለዋል ጀነራሉ። እንደ ጀነራል ዮሐንስ ወልደጊዮርጊስ ገለፃ በተደረጉት የተቃውሞ ትእይንቶች 'ጠላቶቻችን' ያሏቸው ሐይሎች ተደስተዋል ሲሉም አክለው ገልፀዋል።
ጀነራል ዮሐንስ "ጠላቶቻችን በዚህ ሁነት ተደስተዋል። ከዚህ በፊት መቐለ ሲገቡ እንደዚህ የተደሰቱ አይመስለኝም። ሰራዊታችን ጥያቄ ጠየቀ እንጂ፥ ትግራይን አሳልፌ እሰጣለሁ አላለም። ይህ ፍላጎታችሁ እና ምኞታችሁ መክኖ የሚቀር ስለሆነ፥ በማይሆንላችሁ ግዜ አታጥፉ ማለት ነው ያለብን" ብለዋል።
ባለፈው ሰኞ በመቐለ ሰልፍ ያደረጉት የትግራይ ክልል ኃይሎች አባላት ከከተማዋ ወደ አየር መንገድ የሚወስድ መንገድ ዘግተዋል። ይህ ተከትሎ በሌሎች የትግራይ ክፍሎች ያሉ የሰራዊቱ አባላትም ተመሳሳይ ጥያቄዎች በመያዝ ከመቐለ ዓዲግራት፣ ተንቤን፣ ማይጨው እና ሞኾኒ እንዲሁም ሌሎች አካባቢዎች የሚወስዱ ጎዳናዎች ዘግተው ሰንብተዋል። የሰራዊቱ ክፍል የሆነው አርሚ 22 አባላት የአቋም መግለጫ ተብሎ በንባብ የቀረበ መግለጫ እንደሚለው፥ ጥያቄዎቹ ትክክል ቢሆኑም የቀረበበት መንገድ ስህተት ነው ሲል ይገልፃል።
የትግራይ ክልል ኃይሎች አባላት ተቃውሞ ተከትሎ ባለፈው ሳምንት አስቸኳይ ስብሰባ አድርጎ የነበረው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ካቢኔ የሰራዊቱ አባላት ጥያቄ የሚመልስ የተባለ አዋጅ አፅድቆ ወደሚመለከተው አካላት መምራቱ መግለፁ ይታወሳል። ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ለሁለት ዓመት ጦርነት ላይ የነበሩት የትግራይ ሐይሎች፥ ከፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት በኃላ በትጥቅ ማስፈታት እንዲሁም ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለስ ሂደት ያልፋሉ ተብሎ የነበረ ቢሆንም አብዛኛው ሰራዊት አሁንም በዚሁ ሂደት አላለፈም።
ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ