«ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝግጅት እና የኢትዮጵያ ተስፋ» እንወያይ
Description
በኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ሰባተኛውን ሀገራዊ ምርጫ እንደምታደርግ እና ምርጫው ፍትሃዊ ፣ ሰላማዊ ፣ ተአማኒ እና በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው መንግስት በሃላፊነት እንደሚሰራ የኢፌድሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀስላሴ የሁለቱን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ በከፈቱበት ወቅት አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ከነበሩ ግጭቶች እና የኤኮኖሚ አለመረጋጋት በተጨማሪ እንደምርጫ ቦርድ ባሉ የዴሞክራሲ ተቋማት ላይ በሚነሱ የነጻነት እና የገለልተኝነት ጥያቄዎች መጪው ምርጫ ምን ያህል ይሳካ ይሆን የሚሉ ጥያቄዎች ሲነሱ ይሰማሉ።
የተቃዋሚ ፓርቲዎች በሀገሪቱ ከምርጫ ህጎች ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጉዳዮችን ጨምሮ የአንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች መታሰር ፣ የአባላት እንቅስቃሴ መገደብ ብሎም የመገናኛ ብዙኃንን በፍትሃዊነት የመጠቀም ዕድል የማጣት ችግሮች ሲያነሱ ይደመጣል።
በዚያው ልክ የአንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በራሳቸው በውስጣቸው በፈጠሯቸው መከፋፈል እና የምርጫ ጊዜ ሲደርስ ብቻ መከሰት በሀገሪቱ ጠንካራ ውድድር የሚጋብዝ ምርጫ እንዳይኖር የበኩላቸውን አሉታዊ አስተዋጽዖ አበርክተዋል ፤ የሚል ትችት ሲቀርብባቸው ይሰማል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምርጫ ከምርጫ ውድድር ባሻገር ፤ በሀገሪቱ ግጭቶች ቆመውዘላቂ ሰላም ሊያሰፍን የሚያስችል ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት የሚጠይቅ እንደመሆኑ መጠን የተለያዩ ፖለቲካዊ ፍላጎቶችን እና የማህበረሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግም ሲነገር ቆይቷል።
በኢትዮጵያ ግጭት ለቀሰቀሱ የፖለቲካ ፍላጎቶች መልስ ለመስጠት ፣ ሀገሪቱ የምትከተለው መንግስታዊ ስረዓት ብሎም ቀጣናዊ እና ዓለማቀፋዊ ሚናዋን የሚወስነው ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ፣ ፍትሃዊ ፣ ተአማኒ እና ተቀባይነት ያለው እንዲሁም የሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች ተሳትፎ ባረጋገጠ መልኩ እንዲካሄድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የውድድር ዝግጅት ወሳኝ ነው።
«ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝግጅት እና የኢትዮጵያ ተስፋ» የሳምንቱ እንወያይ ዝግጅታችን ርዕስ ነው ።
በውይይቱ ላይ
ፕሮፌሰር ዳምጠው ተሰማ ከአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ አብን ከአዲስ አበባ
አቶ ሙላቱ ገመቹ ከኦሮሞ ፍዴራሊስት ኮንግረንስ ከአዲስ አበባ
ዶ/ር ሙሉዓለም ተገኘ ወርቅ ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ ኢዜማ
ዶ/ር ራሄል ባፌ ከኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ኢሶዴፓ ተገኝተዋል።
አዋያይ ጋዜጠኛ ታምራት ዲንሳ