ኬንያ ፕሬዝደንትነት አምስት ጊዜ የሸሻቸው ራይላ ኦዲንጋን ተሰናበተች
Description
የራይላ ኦዲንጋ አስከሬን ባለፈው ሐሙስ በኬንያ አየር መንገድ ተጉዞ ናይሮቢ ሲደርስ ተከታዮቻቸው ለሰዓታት እየተጠባበቁ ነበር። የኬንያ ብሔራዊ መዝሙር ተዘምሮ ጸሎት ከተደረገ በኋላ አስከሬናቸው ወደ ካሳራኒ ስታዲየም ሲያመራ አረንጓዴ ቅጠል ያላቸው የእጽዋት ዝንጣፊ የያዙ፣ የሀገራቸውን ሰንደቅ ዓለማ የሚያውለበልቡ ደጋፊዎቻቸው እየጨፈሩ እና እየዘመሩ ተመሙ።
በካሳራኒ ስታዲየም ድንገት ጩኸት በረከተ። የራይላ ኦዲንጋ አስከሬን በወታደሮች ታጅቦ ነበር። አስከሬናቸውን ለማየት እና እውቁን የተቃውሞ መሪ ለመሰናበት የተሰበሰቡ በአስር ሺሕዎች የሚቆጠሩ ሐዘንተኞችን ለመበተን ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ ተኮሰ። በዕለቱ አራት ኬንያውያን ተገደሉ። የኦዲንጋ ሕልፈት የሌላ ሞት መነሾ ለመሆን በቃ።
አድናቂዎቻቸው እና ተከታዮቻቸው “ባባ” እያሉ የሚጠሯቸው ራይላ አሞሎ ኦዲንጋ በሕንድ በሕክምና ላይ ሳሉ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው የተሰማው ጥቅምት 6 ቀን 2018 ነበር። ኦዲንጋ ለጤና ምርመራ በሔዱበት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት በልብ ድካም እንደሆነ አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል። 80 ዓመታቸው ነበር።
ባለቤታቸው፣ ቤተሰቦቻቸው እና በሺሕዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በተገኙበት መርሐ-ግብር ኬንያውያን ትላንት አርብ ኦዲንጋን በይፋ ተሰናብተዋል። ሥርዓተ-ቀብራቸው ነገ እሁድ ከኪሱሙ በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ቦንዶ የተባለ የእርሻ ቦታቸው ይፈጸማል።
የኬንያ ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ የሰባት ቀናት ብሔራዊ ሐዘን ያወጁ ሲሆን የሀገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ ይውለበለባል። ሩቶ ለሀገራቸው ሕዝብ የኦዲንጋን ሞት ሲያረዱ “የዴሞክራሲያችንን አባት አጥተናል” በማለት ሐዘናቸውን ገልጸዋል።
“ለበርካታ አስርት ዓመታት በዘለቀ የፖለቲካ ሕይወታቸው ራይላ አሞሎ ኦዲንጋ በመርኅ ላይ የተመሠረተ አሳማኝ የፖለቲካ ሞዴል አቅርበዋል” ያሉት ዊሊያም ሩቶ “በሀገራችን ጉዞ ቁልፍ ምዕራፍ ሁልጊዜም ከግለሰባዊ ጥቅም በፊት ኬንያን አስቀድመዋል” ሲሉ ተደምጠዋል።
ራይላ ኦዲንጋ ለረዥም ዓመታት በኬንያ ፖለቲካ ከፍተኛ ተጽዕኖ የነበራቸው ቢሆንም ባለፉት ዓመታት ዕድሜ እየተጫናቸው እና ጤናቸው እየታወከ ሲሔድ ተሰሚነታቸው ተቀዛቅዟል። በተለይ በጎርጎሮሳዊው 2018 ከቀድሞው ፕሬዝደንት ኡኹሩ ኬንያታ እና ባለፈው ዓመት ከአሁኑ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ጋር የመሠረቱት ጥምረት እምብዛም አልተወደደላቸውም። ምክንያቱም ኦዲንጋ ለረዥም ዓመታት በሥልጣን ላይ የሚገኙ ግለሰቦችን እና ፓርቲዎችን በመገዳደር የሚታወቁ ነበሩ።
የሉዎ ጎሳ አባል የሆኑት ኦዲንጋ በምዕራባዊ ኬንያ በምትገኘው የኪሱሙ አውራጃ ማሴኖ በተባለ ቦታ በጎርጎሮሳዊው ጥር 7 ቀን 1945 ተወለዱ። አባታቸው ጃራሞኚ ኦጊንጋ ኦዲንጋ በኬንያ የነጻነት ትግል ውስጥ ግንባር ቀደም ከነበሩ መሪዎች አንዱ ሲሆኑ የሀገሪቱ መጀመሪያው ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው አገልግለዋል።
ራይላ ኦዲንጋ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በትውልድ አካባቢያቸው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ነው። በምሥራቅ ጀርመን በሜካኒካል ምኅንድስና ከተመረቁ በኋላ በናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ሠርተዋል።
የፖለቲካ ሕይወታቸው የተገራው በኬንያ አንድ ፓርቲ በገነነበት የጎርጎሮሳዊው 1980ዎቹ ነበር። በጎርጎሮሳዊው 1982 በቀድሞው ፕሬዝደንት ዳንኤል አራፕ ሞይ ላይ በማሴር ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለስድስት ዓመታት ታስረዋል። ከአስራ ሁለት ዓመታት ገደማ በፊት በታተመ ግለ-ታሪካቸው በእስር ላይ ሳሉ አካላዊ ድብደባ እና ስነ-ልቦናዊ ጫናን ጨምሮ ስቅየት እንደተፈጸመባቸው ጽፈዋል።
ከእስር ከተፈቱ በኋላ በኬንያ የሰፈነውን የአንድ ፓርቲ የበላይነት በመቃወማቸው ሁለት ጊዜ በቁጥጥር ሥር በመዋላቸው ወደ ኖርዌይ ተሰደው ነበር። ግን በዚያው አልቀሩም። ተመልሰው የፖለቲካ ሥራቸውን ቀጠሉ።
ለመጀመሪያ ጊዜ ለፕሬዝደንትነት የተወዳደሩት በአባታቸው ይመራ የነበረው “ፎረም ፎር ሪስቶሬሽን ኦፍ ዴሞክራሲ-ኬንያ” ፓርቲን በመወከል በጎርጎሮሳዊው 1997 ነበር። ከዳንኤል አራፕ ሞይ እና ከምዋይ ኪባኪ በመለጠቅ ሦስተኛ ሆነው አጠናቀቁ።
አባታቸው ሲሞቱ “ፎረም ፎር ሪስቶሬሽን ኦፍ ዴሞክራሲ-ኬንያ” ፓርቲን ጥለው በመውጣት የብሔራዊ ልማት ፓርቲ (NDP)ን መሠረቱ። በጨዋታ አዋቂነታቸው ተቃዋሚዎችን በማስተባበር የመሠረቱት ብሔራዊ ቀስተደመና ጥምረት በጎርጎሮሳዊው 2002 ኪባኪን ለሥልጣን አበቃ። እርሳቸውም ከ2003 እስከ 2005 በኪባኪ መንግሥት ውስጥ የመንገድ፣ የመንግሥት ሥራዎች እና ቤቶች ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል። ነገር ግን ከኪባቢ ጋር መቃቃር በመፈጠሩ ወደ ተቃዋሚነት ተመለሱ።
በፖለቲካ ሕይወታቸው ትልቅ ቦታ የሚሰጠው በጎርጎሮሳዊው 2007 የተካሔደውው ምርጫ ነው። የሕዝብ አስተያየቶች ራይላ ኦዲንጋ ድምጽ ከሰጠው መራጭ ከፍተኛውን እንዳገኙ ቢያሳዩም የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ግን ምዋይ ኪባኪን አሸናፊነት አወጀ። በውጤቱ ምክንያት በመላ ሀገሪቱ በተቀሰቀሰ ድኅረ ምርጫ ኹከት ከ1,000 በላይ ሰዎች ሲገደሉ በርካቶች ቆሰሉ። በቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሀፊ ኮፊ አናን አሸማጋይነት በተደረሰ የሥልጣን ክፍፍል ሥምምነት ቀውሱ ሲቆም በምዋይ ኪባኪ መንግሥት ሥር ከ2008 እስከ 2013 በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሠርተዋል።
በጎርጎሮሳዊው 2010 በተካሔደ ሕዝበ-ውሳኔ በኬንያ የመንግሥት አወቃቀር የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን ሲሰረዝ ኦዲንጋ ሙሉ በሙሉ ወደ ተቃዋሚነታቸው ተመለሱ። ከዚያ በኋላ በጎርጎሮሳዊው 2013፣ 2017 እና 2022 በተካሔዱ ምርጫዎች ለፕሬዝደንትነት ቢወዳደሩም አልተሳካላቸውም።
በ2013 የተካሔደው ምርጫ “እንከኖች አሉበት” በማለት ኡኹሩ ኬንያታን በፍርድ ቤት ቢሟገቱም አቤቱታቸው ተቀባይነት አላገኘም። በ2022 ከማርታ ካሩዋ ጋር በመሆን ተወዳድረው በዊሊያም ሩቶ ተሸንፈዋል። በድጋሚ የምርጫውን ውጤት በተመለከተ ያላቸውን ቅሬታ ለፍርድ ቤት አቅርበው ተረተዋል።
ራይላ ኦዲንጋ ለረዥም ዓመታት በዘለቁበት ተቃዋሚነታቸው የመከበራቸውን ያክል ትችቶችም ይሰነዘሩባቸዋል። ከወቀሳዎቹ መካከል በኬንያ ያለውን የጎሳ ልዩነት በተለይ ከሉዎ ብሔር ደጋፊ ለማሰባሰብ ተጠቅመውበታል የሚለው ይገኝበታል። ንግግሮቻቸው አንዳንድ ጊዜ ልዩነቶችን አባብሰዋል በሚልም ይነቀፋሉ።
ከኬንያ ፖለቲካ ባሻገር ራይላ ኦዲንጋ የአፍሪካን አንድነት የሚያቀነቅኑ ፖለቲከኛ እንደነበሩ ደጋፊዎቻቸው ይመሰክራሉ። በጎርጎሮሳዊው 2025 ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ ደቡብ ሱዳን ወደ አዲስ ቀውስ መንሸራተት ስትጀምር ኦዲንጋን በአሸማጋይነት መድበው ነበር። ሹመቱ ከፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸው ጭምር ለራይላ ኦዲንጋ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የተሰጠ እውቅና ተደርጎ ይቆጠራል።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበርነት ለመወዳደር ፍላጎት እንዳላቸው በጎርጎሮሳዊው 2024በይፋ አሳውቀው የምረጡኝ ዘመቻ ጭምር ጀምረው ነበር። ይሁንና በምርጫው በቀድሞው የጅቡቲ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ማሕሙድ አሊ ይሱፍ ተሸንፈዋል።
አርታዒ ታምራት ዲንሳ