DiscoverDW | Amharic - Newsበጦርነቱ ወቅት በትግራይ ሴቶች ላይ ደረሰ ስለተባለጾታዊ ጥቃት
በጦርነቱ ወቅት በትግራይ ሴቶች ላይ ደረሰ ስለተባለጾታዊ ጥቃት

በጦርነቱ ወቅት በትግራይ ሴቶች ላይ ደረሰ ስለተባለጾታዊ ጥቃት

Update: 2025-10-18
Share

Description

«የትግራይ ጀኖሳይድ አጣሪ ኮምሽን» በትግራይ ጦርነት ወቅት ተፈጽመዋል ስለተባሉ የፆታ ጥቃቶች ዝርዝር ጥናቱ ይፋ አደረገ። በሁለት ዓመቱ ጦርነት ከ150 ሺህ በላይ የትግራይ ሴቶች በኤርትራ እና የኢትዮጵያ ሐይሎች መደፈራቸው ይፋ ባደረገው ጥናት አመልክቷል። ለእነዚህ ወንጀሎች ዓለምአቀፍ የፍትህ ስርዓት እንዲኖርም ተጠይቋል።



«የትግራይ ጀኖሳይድ አጣሪ ኮምሽን» በሁለት ዓመቱ የትግራይ ጦርነት ወቅት በክልሉ በተለያዩ ሐይሎች ተፈፀሙ ያላቸውን ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች የሚዳስስ የጥናት ውጤት በትላንትናው ዕለት ይፋ አድርጓል። ከጥቅምት 2013 ዓመተምህረት እስከ ጦርነቱ የቆመበት ወቅት ጥቅምት 2015 ዓመተ ምህረት ድረስ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሐይሎች የደረሱ ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች የዳሰሰው ይህ ባለ 166 ገፅ ጥናት በአጠቃላይ 481 ሺህ 201 ሴቶችን በጥናቱ እንደተካተቱ ገልጻል። ከእነዚህ መካከል ከ286 ሺህ በላይ የሚሆኑት ላይ፥ በተለያየ መልኩ ከሚገለፁ የፆታ ጥቃቶች መካከል አንዱ እንደተፈፀመባቸው ያመለክታል።



የፆታ ጥቃቶች



«የትግራይ ጀኖሳይድ አጣሪ ኮምሽን» ጥናት እንደሚያሳየው በሁለት ዓመቱ ጦርነት ወቅት በ152 ሺህ 108የትግራይ ሴቶች መደፈራቸው የሚያመለክት ሲሆን ሌሎች በርካቶች ደግሞ በተለያየ መልኩ የሚገለፁ ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እንደደረሰባቸው አስታውቋል። የዚህ ጥቃት ፈፃሚዎች በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ያስቀመጠው ይህ ላለፉት አራት ዓመታት የተሰራ ጥናት ከአጠቃላይ ጥቃቶቹ 55 በመቶ የሚሆነው በኤርትራ ሰራዊት፣ 35 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ወታደሮች መፈፀማቸው ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪ 5 ነጥብ 7 በመቶ የሚሆነው በአማራ ሐይሎች የተቀሩት ደግሞ የተለያዩ ሐይሎች በጋራ የተፈፀሙ ስለመሆናቸው ጥናቱ አመልክቷል።



ጥናቱ ባደረገው «የትግራይ ጀኖሳይድ አጣሪ ኮምሽን» የሕግ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አለም አብርሃ ጥናቱ ዓለምአቀፍ ደረጃ በጠበቀ መልኩ የተሰራ እና የቤትለቤት ዳሰሳ ጭምር የተደረገበት መሆኑ ለዶቼቬለ ገልፀዋል።



ከ15 ዓመት በላይ የሆኑ የፆታ ጥቃት ሰለባዎች ቀጥታ በማነጋገር ከ15 ዓመት በታች የሆኑት ደግሞ በወላጆች ወይም ቤተሰባቸው በኩል መረጃ ማሰባሰቡ የሚገልፀው የትግራይ ጀኖሳይድ አጣሪ ኮምሽን ሪፖርት በበርካታ ሴቶች በተደጋጋሚ፣ በቡድን እንዲሁም ለወራት ከተፈፀሙ መድፈርና እና ሌሎች ዓይነት የፆታ ጥቃቶች በተጨማሪ 529 ሴቶች ጥቃቱ ከተፈፅሞባቸው በኃላ መገደላቸው በጥናቱ ተረጋግጧል ብለዋል። ባዕድ ነገሮች ወደ ሴቶች መራብያ አካል ማስገባት፣ ለወሲብ ባርነት መገልገል፣ በኬሚካል ማቃጠል እና የመሳሰሉ ሌሎች ተግባራትም በትግራይ ሴቶች ላይ መፈፀማቸው በጥናቱ ተመልክቷል።





ዓለምአቀፍ ወንጀሎች



ያነጋገርናቸው «የትግራይ ጀኖሳይድ አጣሪ ኮምሽን» የሕግ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አለም አብርሃ፥ የተፈፀሙት ድርጊቶች ዓለምአቀፍ ወንጀሎች መሆናቸው በጥናት ተረጋግጥዋል ይላሉ።



ከጥቃቱ ከተረፉ በኃላ ለእርግዝና የተዳረጉ፣ ለፌስቱላእና ኤችአይቪ ኤይድስ በሽታዎች የተጋለጡ፣ ወደ ስነልቦናዊ እና ማሕበራዊ ቀውስ የገቡ ቁጥርም በጥናቱ በዝርዝር ተቀምጧል። በሴቶቹ ላይ የፆታ ጥቃት ሲፈፀምባቸው ብሔራቸው መሰረት ያደረጉ ስድቦች እና የማሸማቀቅ ንግግሮች፣ ዳግም እንዳይወልዱ እና ዘራቸው እንዳይቀጥል የሚዝቱ መልእክቶች በጥቃት ፈፃሚዎቹ በኩል ይተላለፉ እንደነበረ ከተበዳዮች ያሰባሰበው መረጃ እንደሚያመላክት የኮምሽኑ ጥናት አመልክቷል። ከዚህ በዘለለ ከተደፈሩት መካከል 15 በመቶዎቹ ጥቃቱ የቤተሰብ አባል እንዲመለከተው በማስገደድ ጭምር የተፈፀመ ነው። ከሴቶች በተጨማሪ ጥቂት በማይባሉ ወንዶች ጭምር የመድፈር ወንጀል በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሐይሎች መፈፀሙ ጥናቱ ያመለክታል።



ፍትህ ማረጋገጥ



ከፍትህ እና ተጠያቂነት በተገናኘ ደግሞ ዓለምአቀፍ ወንጀል ከመሆኑ አንፃር፥ ዓለምአቀፍ ፍትህ እንደሚሻ አቶ አለም አብርሃ ጨምረው ይገልፃሉ።



በተባበሩት መንግስት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች መርማሪ አካል፣ ዓለምአቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እና ሌሎች ከዚህ በፊት አውጥተውት በነበረ የጥናት ውጤት በትግራይ በሰብአዊነት ላይ ያነጣጠረ እንዲሁም የጦር ወንጀሎች የሚስተካከል ተግባራት በጦርነቱ ተሳታፊዎች መፈፀማቸው መግለፃቸው ይታወሳል።



ከፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት በኃላ በትግራይ ጦርነት ወቅት የተፈፀመው ወንጀሎች «የሽግግር ፍትህ» በተባለ አሰራር እንዲታዩ እንደሚያደርግየኢትዮጵያ መንግስት የገለጸ ሲሆን፥ የኤርትራ መንግስት በበኩሉ የሚቀርቡበት የሰብአዊ መብት ጥሰት ክሶች ውድቅ አድርጓል። በዚህ የኮምሽኑ ሪፖርት ላይ የኢትዮጵያ የኮምኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር ጨምሮ ሌሎች ባለስልጣናት ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ሚልዮን ሃይለስላሴ

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

በጦርነቱ ወቅት በትግራይ ሴቶች ላይ ደረሰ ስለተባለጾታዊ ጥቃት

በጦርነቱ ወቅት በትግራይ ሴቶች ላይ ደረሰ ስለተባለጾታዊ ጥቃት

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ