ትኩረት በአፍሪቃ፣ የትራኦሬ ዝናና አገዛዝ፤ የአንጎላ ተማሪዎች ብሶትና ተቃዉሞ
Description
ሥልጣን የያዙበት እድሜ እንደ ሙዓመር ቃዛፊ፣ እንደ ሳሙኤል ካንዮን ዶ 20ዎቹ ማብቂያ አልነበረም ይልቅዬ በዕድሜም በማዕረግም ከመንግሥቱ ኃይለማርያም ጋር ይቀራረባሉ።እንደ ሁሉም ቆፍጣና ወታደር ናቸዉ።እንደ ሁሉም ሥልጣን የያዙት በመፈንቅለ መንግስት ነዉ።እንደ መንግሥቱ ሻለቃ።መንግሥቱን በአንድ ዓመት በልጠዉ ሐቻምና መስከረም በ34 ዓመታቸዉ የቡርኪና ፋሶ መሪ ሆኑ።ኢብራሒም ትራኦሬ።
ከቶማስ ኢሲዶሬ ንኦሌ ሳንካራ ጋር ደግሞ በብዙ ነገር ተመሳሳይ ናቸዉ።እርግጥ ነዉ እንደ ሳንካራ የማርክሲስት ሌኒኒስትን አስተምሕሮ ማንበብ-ማጥናት መመሰጣቸዉ በግልፅ አይታወቅም።ግን ከሳንካራ ጋር የአንድ ሐገር ልጅ፣ እንደሳንካራ ወታደር፣ ከካፒታሊስቱ አስተሳሰብ ፈቀቅ-ራቅ፣ ወደ ግራዉ ርዕዮተ-ዓለም ዘንበል፣ አፍሪቃዊነትን ጠበቅ የሚያደርግ መርሕ ይከተላሉ።ልክ እንደ ሳንካራ በወጣቶች ዘንድ ዝነኛ፣በማበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ደግሞ ጀግና ናቸዉ።ሻለቃ ኢብራሒም ትራኦሬ።
«በዓለም አቀፍ ደረጃም የወጣት አብዮተኛ አብነት ናቸዉ» ይላሉ የቻተም ሐዉስ የፖለቲካ ተንታኝ ፓዉል ሜሊ።
«በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢብራሒም ትራኦሬ የቀድሞዋን ቅኝ ገዢ የፈረንሳይን ጫና የተቋቋሙ፣ የወጣት አብዮተኞች አብነት ናቸዉ።እንግሊዝኛ በሚናገሩት ሳይቀር በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከፍተኛ ዝና ያተረፉ ናቸዉ።ምዕራብ አፍሪቃም በዲያስፖራዉም ዘንድ በእዉነቱ ከፍተኛ አድናቆት እያገኙ ነዉ።»
የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ግን ሥለ ትራኦሬ የሚሉት ከዚሕ ፍፁም ተቃራኒ ነዉ።ተቃርኖዉ እንዴት ይብራራል? እንሞክር እስኪ።
የቡርኪና ፋሶ አዲስ ምዕራፍ
ጥር 2022 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ።ዋጋዱጉ።ኮሎኔል ፓዉል-ሔንሪ ሳንዳኦጎ ዳሚባ የመሯቸ,ዉ የቡርኪና ፋሶ የጦር መኮንኖች በምርጫ ሥልጣን የያዙትን የፕሬዝደንት ሮሽ ማርክ ክርስቲያን ካቦሬን መንግስት አስወግደዉ ሥልጣን ያዙ።መስከረም 30፣ 2022 ኢብራሒም ትራኦሬና የቅርብ ጓዶቻቸዉ በቅጡ ያልጠናዉን የኮሎኔል ፓዉል-ሔንሪ ሳንዳኦጎ ዳሚባ ወታደራዊ መንግሥትን ከሥልጣን አስወገዱ።ለቡርኪና ፋሶ አዲስ ምዕራፍ።
ትራኦሬ መፈንቅለ መንግሥት ለማድረጋቸዉ የሰጡት ምክንያት የኮሎኔል ዳሚባ መንግስት የ«አሸባሪዎችን» ጥቃት በቅጡ አልመከተም የሚል ነበር።ወጣቱ ሻለቃ አሸባሪዎቹን በሥድስት ወራት ዉስጥ ለማጥፋት፣ በአንድ ዓመት ዉስጥ ምርጫ ለመጥራትም ቃል ገቡ።ዘንድሮ ሶስተኛ ዓመታቸዉ። የብሪታንያዉ የጥናት ተቋም የቻተም ሐዉስ የፖለቲካ ተንታኝ ፓዉል ሜሊ እንደሚሉት አሁንም ሰባ በመቶዉ የቡርኪና ግዛት ከመንግስት ቁጥጥር ዉጪ ነዉ።
«ምናልባት 70 በመቶዉ የሐገሪቱ ግዛት በጀሐዲስት ቡድናት ቁጥጥር ነዉ።ወይም መንግስት አይቆጣጠረዉም።»
ቃል በነነ።ትራኦሬ ሥልጣን በያዙ በ6ኛዉ ወር «ምርጫ አሁን ቅድሚያ የሚሰጠዉ ጉዳይ አይደለም» በማለት ሁለተኛ ቃላቸዉንም አሽቀንጥረዉ ጣሉት።እና ዘገቦች እንደሚጠቁሙት በየጦር እዙና በየመንግስት መዋቅሩ ታማኞቻቸዉን እየሰገሰጉ፣ ተቃዋሚ ድምፆችንና ነፃ መገናኛ ዘዴዎችን ፀጥ አደረጉ።ጭጭ።
ጥር 2023።ትራኦሬ፣ ሐገራቸዉ ከቀድሞ ቅኝ ገዢዋ ከፈረንሳይ ጋር የነበራትን ግንኙነት በጥሰዉ ጣሉት።አሸባሪነትን ለመዋጋት ቡርኪና ፋሶ ሰፍሮ የነበረዉን የፈረንሳይና የተባባሪዎችዋን ሐገራት ጦር አባረሩም።የምዕራብ አፍሪቃ የምጣኔ ሐብት ማሕበረሰብ (ECOWAS) መጀመሪያ ማሊ፣ ቀጥሎ ቡሪኪና ፋሶና ኋላ ኒዠር የተደረገዉን መፈንቅለ መንግሥት አዉግዞ፣ ሶስቱን ሐገራት አግልሎ ነበር።
ትራኦሬ ናይጄሪያ የምትዘዉረዉ ማሕበር ለወሰደዉ ርምጃ አልተጨነቁም።ከሁለቱ ሐገራት ጋር ሆነዉ ከኤኮዋስም 5 ሐገራትን ከሚያስተናብረዉ የሳሕል የፀጥታ ትብብር አባልነትም ወጡ።ሶስቱ ሐገራት የሳሕል መንግስታት ትብብር (AES-በምሕጻሩ) የተባለዉን ማሕበር መሠረቱ።ከሩሲያ ጋር ተወዳጁም።
ኢብራሒም ትራኦሬ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ኮኮብ
ሩሲያ ለሶስቱ ሐገራት ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊና የቅስቀሳ ድጋፍ ትሰጣለች።ይሕ ለምዕራባዉያን ኮስኳሽ ነዉ።ሥም፣ዝና ዉዳሴን በመሸመቱ ግን የማሊዉ አሳሚ ጎይታም ሆነ የኒዠሩ አብዱረሕማን ሳኒ በትራኦ ጫፍ ላይ አይደርሱም። በተለይ በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች «የትራኦሬ ርዕይ»፣«ትራኦሬ አፍሪቃን ይገነባሉ» የሚሉትና ሌሎች ገፆች የሚያንቆረቁሩት ዉዳሴ ወጣቱን ሻለቃ የአፍሪቃ አዳኝ አስመስሏቸዋል።
ትራኦሬ አምስት የፈረንሳይ ወርቅ አምራች ኩባንዮችን ባንድ ጊዜ ማባረራቸዉ ላጭር ጊዜም ቢሆን በየኩባንያዉ ለሚሰሩ የሐገሬዉ ተወላጆች ጉዳት፣ ለሐገሪቱ አጠቃላይ ምጣኔ ሐብትምትም ኪሳራ ማስከተሉ አልቀረም። ሕዝቡ በተለይ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዉ ግን ትራኦሬን የቅኝ ገዢዎች መቅሰፍት፣ የአፍሪቃ ትንሳኤ፣ የዕድገቷ ፈር-ቀዳጅ፣ ዳግማዊ ቶማስ ሳንካራ እያለ አንቆለጳጰሳቸዉ።
ፀረ-ምዕራባዉያን መልዕክቶች የሲቪል ነፃነትን መደበቂያ ሥልት
አሁን በስደት ስዊድን የሚኖረዉ ጋዜጠኛ ጀስቲን ያርጋ እንደሚለዉ ትራኦሬና ተባባሪዎቻቸዉ በተለይ አሸባሪነትን በመዋጋቱ ሒደት ዉድቀታቸዉን ለመደበቅ የመገናኛ ዘዴዎችን ቅስቀሳ እንደጥሩ መሸፈኛ እየተጠቀሙበት ነዉ።ወጣቱም ይቀበላቸዋል።
«ጥናት በምናደርግበት ወቅት ሰዎች ያሉኝን አልረሳዉም።» ይላል ጋዜጠኛዉ።«የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ቢኖርም፣ምንም አያሳስበንም።እኛን የሚያሳስበን በፈረንሳይ ላይ የወሰዱት ርምጃና የያዙት አቋም ትክክል መሆኑ ነዉ ብለዉናል»
ኬንያዊዉ ብሎገር ፓትሪክ ጋተራ የቡርኪና ፋሶ ስደተኛ ጋዜጠኛን አስተያየት ይጋራል«እንደሚመስለኝ እንዲያዉ ባጠቃላይ ሳሕል አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች የሚያድናቸዉ ይፈልጋሉ» ይላል ጋተራ።ጥያቄዉ «ጥሩ መሪ እናግኝ ሳይሆን ጥሩ ሥርዓት ይኑረን መሆን ነበረበት» አከለ ጋተራ።
ቡርኪና ፋሶ ዉስጥ ግን ባሁኑ ወቅት ይሕ የሚቻል አ,ይመስልም።ባለፈዉ ሳምንት ሐገሪቱ ብዙ ጉዳዮችን የሚነካካ አዲስ ሕግ አዉጥታለች።ከሕጎቹ አንዱ የቤተሰብ የተባለዉ ነዉ።በዚሕ ሕግ መሠረት ተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት የሚያደርግ ቡርኪናቤ በወንጀል ይቀጣል።ሌላዉ ደግሞ ፕሬዝደንት ትራኦሬን በይፋ የሚወቅስ የቡርኪናቤ ዜግነቱን እስከመቀማት የሚያደርስ ቅጣት ይበየንበታል።
የቡርኪና ፋሶ፣ የማሊና የኒዤር ወታደራዊ ገዢዎች ሐገሮቻቸዉን ከምዕራቡ የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሐብትና የማሕበራዊ ጉዳይ ጫናና አስተሳሰብ ለማላቀቅ አብክረዉ እየጣሩ ነዉ።ይሁንና የአምንስቲ ኢንተርናሽናል ባልደረባ አልይ ዲያሎ እንደሚሉት ከምዕራቡ ጫና የመላቀቅና ሉዓላዊነትን የማስከበሩ እርምጃ የሰዎችን መሠራታዊ መብቶች የሚጥስና በሕግ ፊት እኩል መሆናቸዉን የሚቃረን ነዉ።
«ይሕ በቡርኪና ፋሶ ማሕበረሰብ ባሕልና እንቅስቃሴ ሁሉ እየተንፀባረቀ ነዉ።ሉዓላዊነትን የማስከበር ፍላጎት የሰዎችን መብትና በሕግ ፊት እኩል መሆናቸዉን ለመጣስ እየዋለ ነዉ።»
ትራኦኤሬና ደጋፊዎቻቸዉ ግን ትችት ወቀሳዉን መስሚያ ጆሮ ያላቸዉ አይመስሉም።
የአንጎላ ተማሪዎች ብሶት፣ ተቃዉሞና ሥጋቱ
ጥያቄ፣ ወቀሳዉ አዲስ አይደለም።ጠያቂ-ወቃሾችን የሚያረካ መልስ ሥላላገኘ እደግና ይጠየቃል።እያሰለሰም ነዉ።አንጎላ።ፕሬዝደንት ዦዋ ሉሬንዞ ሥልጣን ከያዙ በመጪዉ ሳምንት 8 ዓመት ይደፍናሉ።እስካሁን የተቃዋሚዎች ግፊት፣ የጋዜጠኞች ትችት፣ የፖለቲካ ተንታኞች ማሳጣት በመከላከያ ሚንስትርነት በኩል ለሉዋንዳ ቤተ-መንግሥት ያበቃቸዉን የኃይል-ጉልበት፣ የፖለቲካ- ብልጠትን የሚፈታተን አልሆነም።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በ71 ዓመቱ ፕሬዝደንትና በመንግሥታቸዉ ላይ ጥያቄ፣ ትችት፣ ወቀሳዉን የሚያዥጎደጉት ትናንትሽ ልጆችና ወጣቶች ናቸዉ።ተማሪዎች።አሁን አስተማሪዎቻቸዉም ተጨምረዋል።ጥያቄዉ የመማሪያ ሥፍራ፣መሳሪያና ቁሳቁስ ይሻሻል የሚል ነዉ።ተማሪና አስተማሪዎች እንደሚሉት በየትምሕርት ቤቱ በቂ ወንበር፣ ጠረጴዛ፣ መፀዳጃና የማስተማሪያ ቁሳቁስ የለም።አንዳዱጋ ደግሞ ይሕም ቅንጦት ነዉ።
ተማሪዎቹ የመሰረቱት የአንጎላ ተማሪዎች ንቅናቄ (በፖርቱጋልኛ ምህጻሩ (MES) ቃል አቀባይ ፍራንቼስኮ ታክሲሪያ እንደሚሉት በዛፍ ጥላ ሥር የሚማሩ አሉና።
«ትምህርት ቤቶቹ ያሉበት ሁኔታ በዕዉነት በጣም አሳዛኝ ነዉ።ሉዋንዳን ጨምሮ በብዙ ክፍለ-ሐገራት ወንበርና ጠረጴዛ ሥለሌለ ተማሪዎች የሚማሩት መሬት ተቀምጠዉ ነዉ።ዛፍ ሥር የሚማሩም አሉ።አንጎላ ዉስጥ 19 ሺሕ ዛፎች እንደመማሪያ ክፍሎች ያገለግላሉ።ተማሪዎቹ ጥላ ሲዞር አብረዉ ይዞራሉ።ይሕ አሳፋሪ ነዉ።»
የወጣቶቹ ጥያቄ፣ ሰልፍ የኃይል ርምጃ
ተማሪዎቹ በተደጋጋሚ ላቀረቡት ጥያቄ ከመንግስት ያገኙት መልስ ሶስት ነዉ።የመማሪያ ግብር መጨመር፣ MESን የተቃዋሚዎች መሳሪያ እያለ ማጣጣል።ባለፈዉ ግንቦት የተደረገዉን የተማሪዎች ሰልፍ በኃይል መደፍለቅ።-ሶስት።ተቃዉሞ ሰልፈኛዉን ለመበተን የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት የኃይል እርምጃ ብዙ ተማሪዎች ቆስለዋል።ሌሎች ታስረዋል።እርምጃዉ በተማሪዎች፣ በአስተማሪዎችና በወላጆች ላይ ያሳደረዉ ቂም ዛሬም አልበረደም።የMES ቃል አቀባይ ፍራንቼስኮ ታክሲሪያ መንግሥት ለተማሪዎቹ ጥያቄ መልስ ካልሰጠ ሌላ ተቃዉሞና አመፅ መቀስቀሱ እንደማይቀር አስጠንቅቀዋል።
የፕሬዝደንቱ ተስፋ፣ አዲሱ የትምሕርት ዘመን
ፕሬዝደንት ዦዋ ሉሬንዞ ባለፈዉ ሳምንት በተደረገ አንድ ሥብሰባ ላይ መንግሥታቸዉ ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ለትምሕርት 450 ሚሊዮን ዩሮ መመደቡን አስታዉቀዋል።
«ይሕ ገንዘብ አዳዲስ ትምሕርት ቤቶችን ለመገንባት ማለት ለአዳዲስ የመሠረተ-ልማት አዉታር ብቻ ሳይሆን ለአስተማሪዎች ሥልጠና የሚዉልም ነዉ።»
የትምሕርት ሚንስትር ሉኢዛ ማርያ አልቬስ ግሪዮም መንግስታቸዉ የተማሪዎቹን ችግር እንደሚያቃልል ተናግረዋል። የተቃዉሞ ሰልፍ እንደማያስፈልግ አስታዉቀዋልም።የትምሕርት ቤቶቹ ይዞታ ሳይሻሻል አዲሱ የትምሕርት ዘመን ተጀምሯል።በ2025/2026 የትምሕርት ዘመን 10 ሚሊዮን ተማሪዎች ተመዝግበዋል።
መምሕራን ሥራ ለማቆም እየዛቱ ነዉ
አዲሱ የትምሕርት ዘመን የተጀመረዉ መንግሥት የገባዉን ቃል ገቢር ማድረግ አይደለም ገቢር ለማድረግ ፍንጭ እንኳን ሳያሳይ ነዉ።የተማሪዎቹ ንቅናቄ እንደሚለዉ አንጎላ ዉስጥ የመማሪያ መፅሐፍት መታተም ወይም ለተማሪዎች መታደል ከቆመ ሁለተኛ ዓመቱን ይዟል።
የንቅናቄዉ ቃል አቀባይ ፍራንቼስኮ ታክሲሪያ እንዳሉት ችግሩ ሥር የሰደደ ነዉ።በአንጎላ የትምሕርት ሚንስቴር አቅም ብቻ የሚፈታም አይደለም።መንግሥት በአፋጣኝ መልስ ካልሰጠ ተቃዉሞ መቀጠሉ አይቀርም።የአንጎላ የመምሕራን ማሕበረም ለተማሪዎቹ ድጋፉን እየገለጠ ነዉ።የማሕበሩ ዋና ፀሐፊ አድማር ይንጉማ እንዳሉት ማሕበሩ የሥራ ማቆም አድማ ሊጠራ ይችላል።
«ሐገር አቀፍ የሥራ ማቆም አድማ በየትኛዉም ጊዜ ሊደረግ ይችላል።ለጊዜዉ አድማ ያልጠራነዉ ለዉይይት ጊዜ ለመስጠት ነዉ።መንግሥት ግን ይሕን በግልፅ ሊረዳዉ ይገባል።የሆነ ጊዜ ትዕግስታችን ማለቁ አይቀርም።»
እያሽቆለቆለ የመጣዉ የአንጎላ የትምሕርት ይዞታ በተማሪዎች ጀምሮ አሁን የአስተማሪዎችን ተቃዉሞ አስከትሏል።የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች፣ አብያተ ክርስቲያናትና ተቃዋሚ ፖለቲከኞችም ከተማሪ-አስተማሪዎቹ ጎን ቆመዉ መንግስት እየወቀሱ ነዉ።ሐገር አቀፍ አድማና ተቃዉሞ ሰልፉ መደረጉ ወይም የሚደረግበት ወቅት አይታወቅም።ተቃዉሞዉ መጠናከሩ ግን እርግጥ ነዉ።
ነጋሽ መሐመድ
ማንተጋፍቶት ሥለሺ