የኬንያው መሪ በጅምላ የፓርላማ አባላትን በሙስና መውቀሳቸው እያወዛገበ ነው
Description
የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ የፓርላማ አባላቱን ጉቦ እየተቀበሉ ነው ብለው ከከሰሱ ወዲህ፤ በሙስና ላይ የሚደረገው የቃላት ጦርነት የኬንያን ፖለቲካ አናግቷል። በሀገሪቱ የተደረገ አዲስ ጥናት ያወጣው መረጃ ደግሞ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን እና የህዝብ ቁጣን እንዲያገረሽ አድርጓል።የ2024 ብሄራዊ የስነምግባር እና የሙስና ዳሰሳ በኬንያ የዕለት ተዕለት ኑሮን አስከፊ ገፅታ ያሳያል። ይህም ዜጎች መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት ብቻ ጎቦ ለመስጠት የሚገደዱ መሆናቸውን ያሳያል።-አሰራሩ የተለመደ በመሆኑ ደግሞ፤ አብዛኛዎቹ ተጎጂዎች ሪፖርት ለማድረግ በጭራሽ አይፈልጉም።በአማካኝ የጉቦ መጠን ቢቀንስም፣ ልምዱ ሥር የሰደደ በመሆኑ ፤አብዛኞቹ ጉዳዮች ሪፖርት ሳይደረግባቸው እንደሚቀሩ ጥናቱ አመልክቷል።በጎርጎሪያኑ ነሀሴ 18 በተደረገው የጋራ የፓርላማ ቡድን ስብሰባ ላይ ፕሬዝዳንት ሩቶ ጉቦ ከሚወስዱት መካከል የህግ አውጭ አካላት እንደሚገኙበት ተናግራዋል።ይህም በኬንያ ፓርላማ ውስጥ ቁጣ ቀስቅሷል። ነገር ግን በባዶ የተስፋ ቃል በሰለቹት በኬንያ ዜጎች ዘንድ ጉዳዩ ድጋፍ አግኝቷል።«የፓርላማን ተአማኒነት የሚያጠፉ ሰዎች አሉ፣ በፓርላማ ስም ገንዘብ እየሰበሰቡ ነው፣ እና ብዙ ጊዜ ገንዘቡ ፓርላማ አይደርስም ፣ ለጥቂት ሰዎች ይደርሳል» ካሉ በኋላ አያይዘውም፤«እኛ ልናሸማቅቃቸው አይደለም፤ ልናስራቸው ነው። ሰጭም ተቀባይም ከዚህ ጋር መጋፈጥ አለባቸው።» ብለዋል።
የማስረጃ ጥያቄዎች
የሩቶ ተቺዎች ክሱ የፀረ ሙስና ትግሉን ፖለቲካ የማድረግ አደጋ አለው ሲሉ፤ ደጋፊዎቻቸው ግን አስተያየቱ የአደባባይ ሚስጥር ሆኖ የቆየ እውነትን ያጋልጣል ይላሉ።
ነገር ግን በርካታ የኬንያ ሕግ አውጭዎችክሱን ፈጥነው ነው የተቃወሙት።የብሔራዊ ምክር ቤቱ የአናሳ ቡድኖች መሪ ጁኔት ሞሃመድ ፕሬዚዳንቱ ያቀረቡትን ክስ እንዲያረጋግጡ ጠይቀዋል።
« ክሱን የሚያቀርበው ሰው ማስረጃ ይዞ መምጣት አለበት፣ የማስረጃ የማቅረብ ሸክም ውንጀላውን የሚያቀርበው ሰው ነው። ከሳሽ ማስረጃ ይዞ መምጣት አለበት - አለቀ።»ብለዋል።
ሚሊ ኦዲያምቦ የተባሉ የፓርላማ አባልም የማስረጃ ጥያቄውን አጠናክሮ በመቀጠል ፓርላማው በአጠቃላይ ከመኮነን ይልቅ ሙስና እንደ ግለሰብ ጉዳይ መታየት እንዳለበት አሳስበዋል።
«ስለዚህ አንድ ሰው በሙስና ከሰራ የግለሰብ ጉዳይ ነው። አባላት ሙስና እንደፈጸሙ ለየብቻ አጣርተው፣ በምን ላይ ሙስና እንደፈፀሙ እና ማን እንደ ሰጣቸው ሊነግሩን ይገባል" ትላለች።የቀድሞ የፓርላማ አባል እና የአስተዳደራዊ ጉዳዮች ተንታኝ ዊልሰን ሶሲዮን የጋራ ጥፋተኝነትን ውድቅ በማድረግ ከህግ አውጭዎች ጋር የተስማሙ ይመስላል።
«በመረጃ ከተነጋገርን እና እውነታውን ከተናገርን ሙስና በኬንያ ባሉ ተቋማት ሁሉ የአኗኗር ዘይቤ ነው። ይህ እውነት ነው። እና ፓርላማው የተለየ ሊሆን አይችልም። እናም ፓርላማ እንደ ተቋም ሳይሆን ግለሰቦች ሊሳተፉ ይችላሉ። ግለሰቦች በግለሰብ ደረጃ ሲሳተፉ ሌላው አባላት እንኳን ላያውቁ ይችላሉ። የስራ አስፈፃሚ አባላት ሲሳተፉም ሌሎቹ ላያውቁ ይችላሉ።» በማለት ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።
ሶሲዮን አክለውም የፕሬዚዳንቱ ንግግር የተሳሳተ መሆኑን ተናግረዋል፡- «ይህን ክስ በቡድን ማውጣቱ ትክክል አይደለም ብዬ አስባለሁ፣ በእርግጥም በጉቦ የተሰማሩ ግለሰቦች ካሉ፣ ያን ፓርላማው አይደለም የሚያደርገው፣ ፓርላማ ውስጥ ያሉት ግለሰቦች ናቸው»ብለዋል።የሥነ ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሊቀ መንበር ጳጳስ ዴቪድ ኦጊንዴ፣ በበኩላቸው ሙስና እየተስፋፋ መምጣቱን ቢሰማሙም፣ አብዛኞቹ ኬንያውያን ሙሰኞች እንዳልሆኑ ተናግረዋል።«ስለዚህ እኛ የምንለው እንደ ሀገር፤ ሙስና ተፈጥሯዊ የሆነበት ቦታ ላይ ደርሰናል፣ የተለመደ ሆኗል። እና እንደ ተራ ዜጋ እንኳን ሙሰኞችን የምናከብር እየመሰለን ነው። ሀብታቸውን እንዴት እንዳመጡ ማስረዳት የማይችሉ ሰዎችን የምናከብር ይመስላል።» ብለዋል።
ኦጊንዴ፤ የዳሰሳ ጥናቱ እንዳመለከተው 70% የሚጠጉ ኬንያውያን በጉቦ እንዳልተሰማሩ ጠቁመው፣ “ኬንያውያን ሙሰኞች ናቸው የሚል አመለካከት አለ። ነገርግን አብዛኞቹን ኬንያውያን ብትመለከቱ ሙሰኞች አይደለንም። ለዚህም ይመስለኛል ሰዎች ሙስናን መዋጋት የሚለውን ሃሳብ የሚያንፀባርቁት ጥቂት ሰዎች እንዳሉ ስለሚገነዘቡ ነው» ብለዋል።
በሩቶ አቋም ላይ ህዝብ ተከፋፍሏል
በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢጎዳናዎች ላይ ተራ ዜጎች በፕሬዚዳንቱ ሀሳብ ላይ የተለያየ አስተያየት ሰጥተዋል።ማቲው ዋፉላ የፕሬዚዳንቱ የሰላ ንግግር ቃናው በአንድ ወቅት ቃል ከገቡት የአማካሪነት ሚና የተለዬ ነው ብለዋል።"ክቡር ፕሬዝዳንቱ ከአማካሪ እና አሳታፊ መሪነት በፓርላማው ላይ ቀጣይነት ያለው ጥቃት ወደመሰንዘር መሸጋገራቸው ብዙ ጥያቄዎችን እያስነሳ ነው" ብለዋል።
ሌሎች ጠንከር ያለው እርምጃ ጊዜ ያለፈበት መሆኑን አጥብቀው ተናግረዋል ። ማክስዌል ኦሉ ለDW እንደተናገሩት ሙስና መዘዝ አለው። «በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ሊታሰሩ ይገባል፣ የህግ የበላይነትም ሊከበር ይገባል፣ ፕሬዚዳንቱም እነዚህ ሁሉ ማድረግ ይችላሉ»ብለዋል። ጄፍ ምዌንድዋ ፕሬዚዳንቱ ራሳቸው የሚመልሱላቸው ጥያቄዎች እንዳሉት ተከራክሯል። «ፕሬዚዳንቱ እራሳቸው የሙስና አካል ሆነው ሳለ፤ የፓርላማ አባላቱን በሙስና መውቀስ አለባቸው የሚለው አይታየኝም።»ብለዋል።ኬንያ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ሽልንግ በሙስና ታጣለች፤ ይህ ገንዘብ ለጤና፣ ለትምህርት እና ለመሰረተ ልማት ሊረዳ ይችላል ሲሉ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይናገራሉ።የአፍሪካ ልማት ባንክ መረጃ እንደሚያሳየው የአገሪቱ ኢኮኖሚ በየዓመቱ ወደ 1.5 ቢሊዮን ዶላር (1.3 ቢሊዮን ዩሮ) ከዝርፊያ እና ከህገወጥ የገንዘብ ፍሰት እንሚጠፋ ይገመታል።
የስርዓቱ ውድቀቶች እና ማሻሻያዎች
ተንታኞች እንደሚናገሩት ተግዳሮቱ የህግ እጥረት ሳይሆን የአፈፃፀም ደካማነት እና የፖለቲካ ፍላጎት ውስንነት ነው። ኬንያ የፀረ ሙስና እና የኢኮኖሚ ወንጀሎች ህግ እንዲሁም የጉቦ ህግን አውጥታለች። ነገር ግን የቅጣት ውሳኔዎች ብዙ አይደሉም። ከፍተኛ የሆኑ የሙስና ቅሌት ክሶች ብዙ ጊዜ ያለ ተጠያቂነት ይጠናቀቃሉ።
የፖለቲካ ኢኮኖሚስት እና ተንታኝ ሺላ ኦላንግ በኬንያ ለስርአቱ ውድቀት ዋና መነሻ የሙስና ቀውስ መሆኑን ይሞግታሉ።«ለዚህ ስርዓታዊ ምላሽ የት አለ? ማይክሮፎን መያዝ እና የህዝበኝነት አቋም መያዝ አይደለም። የሚሉት ተንታኟ ችግሩ በስርዓት መፈታት አለበት ባይ ናቸው።አያይዘውም ጉዳዩ የመሸፋፈን ባህል ነው ሲሉ በብስጭት ገልፀዋል። አክለውም «ነገሮችን ከምንጣፍ ስር የመጥረግ ዝንባሌ አለን። ያንን የምታደርገው ግን መረሳት ከሌለባቸው ሰዎች ጋር ነው።እኛ ኢንተርኔት አለን፤ ስልኮች አሉን፤ ስራ የለንም። ስለዚህ እኛ ማድረግ የምንችለው ነገር ቢኖር አንተን ተጠያቂ ማድረግ፤ ወይንም መስራት ያለብህን ነገር እንድትሰራ ማድረግ ነው።»ሲሉ ገልፀዋል።
የተጠያቂነት መንገድ
የሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖች እና ባለሙያዎች የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥን እንደ አጋዥ መንገድ ይጠቅሳሉ።አንዳንዶች በዲጅታል አሰራር በዜጎች እና በባለሥልጣናት መካከል ፊት ለፊት የሚደረጉ ግንኙነቶችን መቀነስ ጉቦ የማግኘት ዕድልን እንደሚገድብ ይናገራሉ።ሌሎች ደግሞ መከላከያ አሰራሮችን መዘርጋት እና የዳኝነት ነፃነትን ማጠናከር አስፈላጊ እርምጃዎች እንደሆኑ ይጠቁማሉ።በሀገሪቱ ህዝባዊ ተሀድሶ እንዲካሄድ የሚገፋ ጫና እየጨመረ ሲሆን ፤የመብት ተሟጋቾችም ተከታታይነት ያለው አፈፃፀም እና ግልፅነት፤ መተማመንን መልሶ ለመገንባት ብቸኛው መንገድ መሆኑን ይከራከራሉ።ለብዙ ኬንያውያን ፈተና የሆነው የፓርላማ አባላት ጨምሮ በስልጣን ላይ ያሉት ከተራው ዜጋ ጋር በእኩል ደረጃ ይጠየቃሉ ወይ? የሚለው ነው።
ፀሀይ ጫኔ
ሂሩት መለሠ