ከማዳጋስካር የወጣቶች ተቃውሞ በኋላ የመፈንቅለ-መንግሥት መሪ ኮሎኔል ፕሬዝዳንት ሆኑ
Description
የማዳጋስካር ወጣቶች በሚመሩት ተቃውሞ ሥልጣን የጨበጡት ኮሎኔል ሚካኤል ራንጄሬሪና ፕሬዝደንት ሆነው ትላንት አርብ ቃለ-መሐላ ፈጽመዋል። የ51 ዓመቱ የጦር መኮንን ከማዳጋስካር ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ፊት ቃለ-መሐላ የፈጸሙት በፈረንሳይኛ ምህጻሩ ካፕሳት (CAPSAT) ተብሎ የሚጠራው የጦሩ ልዩ ኃይል በሣምንቱ መጀመሪያ የመንግሥት ሥልጣን መቆጣጠሩን ካስታወቀ በኋላ ነው።
ኮሎኔል ሚካኤል ራንጄሬሪና ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር እስከ ሁለት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ምርጫ እንደሚካሔድ ቃል ገብተዋል። ይሁንና ቃለ መሐላ ያስፈጸማቸው ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ምርጫው በ60 ቀናት ውስጥ ሊካሔድ ይገባል የሚል አቋም ቢኖረውም ወታደሩ ፕሬዝደንት አስፈላጊ ማሻሻያዎች ተግባራዊ መደረግ አለባቸው በሚል አመክንዮ ሳይቀበሉት ቀርተዋል።
ወታደራዊ የደንብ ልብሳቸውን በሙሉ ሱፍ ቀይረው ሥልጣን የተረከቡት ኮሎኔል ማዳጋስካር የምታልፍበትን ሽግግር “ታሪካዊ” ያሉት ሲሆን በንግግራቸው የቀድሞውን መንግሥት ኮንነው ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ወጣቶችን አሞግሰዋል።
“እነዚህ ወጣቶች የፍትኅ እጦት፣ የሐብት ዘረፋ፣ የሕዝብ ንብረት ያለ አግባብ ብዝበዛ ሰለባዎች ናቸው” ያሉት ኮሎኔል ሚካኤል ራንጄሬሪና በእንግሊዘኛ “ጄን ዚ” ተብሎ የሚጠራው ትውልድ “አባላት በሁሉም የማዳጋስካር ሕዝብ ድጋፍ አደባባይ ወጥተው ብሔራዊ መልሶ ግንባታ እንዲጀመር የሀገሪቱ ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በተለይም የኤሌክትሪክ በተደጋጋሚ መቆራረጥ መፍትሔ እንዲበጅላቸው ጠይቀዋል” ሲሉ ተናግረዋል።
ኮሎኔል ሚካኤል ራንጄሬሪና ቃለ-መሐላ የፈጸሙበት መርሐ ግብር ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች፣ ፖለቲከኞች እና የወጣቶች ተወካዮች ታድመዋል። የአውሮፓ ኅብረት፣ የጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ አሜሪካ፣ ቻይና እና ሩሲያ ዲፕሎማቶችም በቦታው ነበሩ። ይሁንና የአፍሪካ ኅብረት የቀድሞው ፕሬዝደንት አንድሬ ሮጄሊና ከሥልጣን ተባረው በኮሎኔል ሚካኤል ራንጄሬሪና የተተኩበትን ሽግግር ተቃውሟል።
የአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና ጸጥታ ምክር ቤት ማዳጋስካርን ከኅብረቱ አባልነት አግዷል። ማዳጋስካር ወደ ሕገ-መንግሥታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምትመለስበትን ሰላማዊ መንገድ ለማመቻቸት ባለሥልጣናት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ፣ የወጣቶች ተወካዮችን ጨምሮ በባለድርሻ አካላት መካከል ሐቀኛ እና ገንቢ ውይይት እንዲጀመር የተቀናጀ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አስፈላጊ እንደሆነ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ማሕሙድ አሊ ይሱፍ አሳስበዋል።
የተባበሩት መንግሥታት እንደ አፍሪካ ኅብረት ሁሉ በማዳጋስካር ወታደሮች ሥልጣን መቆጣጠራቸውን ተቃውሟል። የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ “የተፈጸመውን ሕገ-መንግሥታዊ ያልሆነ የመንግሥት ለውጥ በማውገዝ ወደ ሕገ-መንግሥታዊ እና ሕጋዊ ሥርዓት እንድትመለስ ጥሪ አድርገዋል” ሲሉ ቃል አቀባያቸው ስቴፈን ዱጃሪች ተናግረዋል።
የቀድሞው የማዳጋስካርፕሬዝደንት አንድሬ ራጄሊና መንግሥታቸው ከገጠመው ብርቱ ሕዝባዊ ተቃውሞ በኋላ በማዳጋስካር ምክር ቤት ከሥልጣን ተነስተው ሀገር ጥለው ሸሽተዋል።
አንድሬ ራጄሊና በጎርጎሮሳዊው 2009 ሥልጣን የያዙት በፈረንሳይኛ ምህጻሩ ካፕሳት (CAPSAT) ተብሎ በሚጠራው የጦሩ ልዩ ኃይል ድጋፍ በተካሔደ ሀገራዊ ተቃውሞ የቀድሞው ፕሬዝደንት ተባረው ነበር። በወቅቱ የዋና ከተማዋ አንታናናሪቮ ከንቲባ የነበሩት ሮጄሊና በአስር ሺሕዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በአደባባይ እየሰበሰቡ የቀድሞው ፕሬዝደንት ማርክ ራቫሎማናና መንግሥት ሥልጣን እንዲለቅ ግፊት አድርገዋል። ከጎርጎሮሳዊው 2019 ጀምሮ ራጆሊና የማዳጋስካር ፕሬዝዳንት ነበሩ።
ታዛቢዎች እንደሚሉት አሁን በማዳጋስካር እየተፈጠረ ያለው ሁሉ ከቀድሞው የሚመሳሰል እና ቸል ሊባል የማይችል ነው።
በማዳጋስካርከመስከረም ወዲህ በቅርብ ታሪኳ ከገጠሟት ሁሉ የከፋ የወጣቶች የአደባባይ ተቃውሞ ተቀስቅሶ የፖለቲካ ምኅዳሩ ተለውጧል። በአንታናናሪቮ አደባባይ የወጡ ተቃዋሚዎች በተደጋጋሚ ፕሬዝደንቱ ሥልጣናቸውን እንዲለቁ ጠይቀዋል። ፕሬዝዳንቱ መንግሥታቸውን አፍርሰው አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሾሙም የተቃዋሚዎቹን ግፊት ማቆም አልቻሉም። የተቃዋሚዎቹ ጥያቄ ፕሬዝደንቱ ላይ ብቻ ያነጣጠረ አይደለም።
“የአዲሱ ትውልድ አባላት አዲስ ሕገ-መንግሥት እና የበለጠ ግልጽነት እንዲኖር ተስፋ እናደርጋለን” በማለት በተቃውሞ ከተሳተፉ ወጣቶች አንዱ ተናግሯል። በማዳጋስካር “ሙስና መኖር የለበትም” የሚል አቋም ያለው ወጣት “ባለሥልጣናቱ ሕዝቡን ለመጠበቅ የበለጠ እንዲሳተፉ” ይፈልጋል።
ሌላ ስሙ እንዳይገለጽ የጠየቀ የተቃውሞ ተሳታፊ ወጣት “በማዳጋስካር ያለውን ሙሰኛ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ መለወጥ እንፈልጋለን። መሪዎቻችን ወጣቶችን የበለጠ ያዳምጣሉ ብለንም ተስፋ አለን” በማለት ተመሣሣይ ሐሳብ አጋርቷል።
የወጣቶቹ ተቃውሞ የበረታው በተለይ ካፕሳት ተብሎ የሚጠራው የጦሩ ልዩ ኃይል ድጋፉን ከገለጸ በኋላ ነበር። ልዩ ኃይሉ የማዳጋስካር የጸጥታ አስከባሪዎች በተቃዋሚዎች ላይ እንዲተኩሱ የሚሰጣቸውን ትዕዛዝ እንዳይቀበሉ አሳስቧል። ይህ ጦር በቀጥታ በውጊያ አውድማዎች የሚሰለፍ አይደለም።
ልዩ ኃይሉ የወታደሮች ጉዳይ፣ አስተዳደራዊ ድጋፍ፣ የስንቅ እና ትጥቅ አቅርቦት የመሳሰሉትን ጨምሮ በመደበኛው ጦር ውስጥ ቁልፍ ጉዳዮችን ይቆጣጠራል። የፖለቲካ ተንታኟ ሮዘ ሙማንያ እንደሚሉት ይህ ክፍለ ጦር ከወታደራዊ ጉዳዮች የዘለለ ትሥሥር ከማዳጋስካር ልሒቃን ጋር አበጅቷል።
በኮሎኔል ሚካኤል ራንጄሬሪና የሚታዘዘው ካፕሳት “ከሜሪና ቡድን በተውጣጡ ልሒቃን የሚመራ እና ከሀገሪቱ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እና ባለጸጎች ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ነው” በማለት አስረድተዋል። “አብዛኞቹ አባላቱ አሁን የራጄሊና ደጋፊ አይደሉም” የሚሉት ሮዘ ሙማንያ “ባለፉት ሦስት እና አራት ዓመታት ሮጄሊናን በጥርጣሬ ሲመለከቱ እና ጥቅሞቻቸው መጣጣማቸውን ሲያጠይቁ ቆይተዋል” በማለት አስረድተዋል።
ሮዘ ሙማንያ በማዳጋስካር የወታደሮቹ ሥልጣን መቆጣጠር ብዙ መዘዝ ሊኖረው እንደሚችል ሥጋት ያሰጋቸዋል። ለሦስት ሣምንታት በአደባባይ ተቃውሞ ያሰሙ ወጣቶች ጥያቄዎቻቸው መልስ ለማግኘታቸው እርግጠኛ አይደሉም።
ዓለም ባንክ ከሦስት ዓመታት በፊት ይፋ ያደረገው ጥናት ከማዳጋስካር 30 ሚሊዮን ሕዝብ ሦስት እጁ ከድሕነት ወለል በታች እንደሚኖር አሳይቷል። ከማዳጋስካር ሕዝብ ኤሌክትሪክ የሚያገኘው 36 በመቶው ብቻ ሲሆን እርሱም በየቀኑ ስለሚቆራረጥ አስተማማኝ አይደለም።
አርታዒ ታምራት ዲንሳ