እስራኤል በደቡባዊ ጋዛ የአየር ጥቃት መፈጸሟን አስታውቀች።
Description
እስራኤል በደቡባዊ ጋዛ የአየር ጥቃት መፈጸሟን አስታውቀች።ጥቃቱ ሐማስ የተኩስ አቁም ስምምነቱን በመጣስ በእስራኤል ጦር ላይ ለፈጸመው ጥቃት ምላሽ ነው ብሏል። በጎርጎሮሳውያኑ ጥቅምት 10 ቀን 2025 በአሜሪካው ፕረዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አማካኝነት የተኩስ አቁም ስምምነት ከተካሄደ በኋላ ሁለቱም ወገኖች አንዱ ሌላኛውን በተኩስ አቁም ስምምነቱን በመጣስ እየተወቃቀሱ ነው።የእስራኤል ጦር ያሰራጨውን መግለጫ ጠቅሶ የጀርመን ዜና አገልግሎት እንደዘገበው እስራኤል ዛሬ በደቡብ ጋዛ ራፋሕ አካባቢ የሐማስ ወታደራዊ ይዞታዎች ባለቻቸው ኢላማዎች ላይ የአየር ጥቃት ፈጽማለች። ጥቃቱ ሐማስ የተኩስ አቁም ስምምነቱን በመጣስ በእስራኤል ጦር ላይ ለፈጸመው ጥቃት ምላሽ መሆኑን በማከል። በጥቃቱ ስለደረሰ ጉዳት ግን ያለው ነገር የለም።የእስራኤል ጦር አክሎም ሐማስ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ላይ «ከፍተኛ ጥሰት ፈጽሟል» ሲል ሀማስን ወቅሷል። አሜሪካ በበኩሏ ሐማስ በገዛ ወገኖቹ ፍልስጤማውያን ስቪሎች ላይ ጥቃት ለመፈጸም ዕቅድ አለው ስትል አስጠንቅቃለች።ሐማስ ግን ይህን ውንጀላ ውድቅ አድርጎታል። ሐማስ ባሰራጨው መግለጫ በመላው ጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ላይ የተዘረዘሩትን ውሎች በሙሉ እንዲከበሩና እንዲተገበሩ ቁርጠኛ መሆኑን አክሏል።ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ጦራቸው በጋዛ «አሸባሪ» ባሉት ሐማስ ላይ ጠንካራ እርምጃ እንዲወስድ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ዛሬ ባሰራጨው መግለጫ አስታውቋል። ጠቅላይ ሚኒስትርቤንጃሚን ኔታንያሁ ይህን ትዕዛዝ ያስተላለፉት ከሐገሪቱ ወታደራዊና የጸጥታ አካላት ባለስልጣኖች ከመከሩ በኋላ መሆኑን መግለጫው አክሏል። የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫም ሐማስ የተኩስ አቁም ስምምነቱን በመጣስ በእስራኤል ወታደሮች ላይ ትንኮሳ ከፈጸመ «ከባድ ዋጋ ይከፍላል» ሲል አስጠንቅቋል።
በሌላ ዜና እስራኤል በዛሬው ዕለት የ 15 ፍልስጤማውያን አስከሬን ወደ ጋዛ መልሳለች።እስከአሁን የተመለሰ የፍልስጤማውያን አስከሬን ቁጥር 150 መድረሱን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር መግለጹን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።