የጸጥታ እና የፖለቲካ ጥያቄዎች መልስ ካላገኙ ቀጣዩ ምርጫ ምርጫ ሊሆን አይችልም፤ ኦፌኮ
Description
በኢትዮጵያ የፀጥታ እና የፖለቲካ ጥያቄዎች መልስ ካላገኙ ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ምርጫ ሊሆን አይችልም ሲሉ የኦፌኮ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ተናገሩ ። ፕሮፌሰር መረራ ለዶቼ ቬለ በተለይ እንዳሉት በተለይ በኦሮሚያ ክልል ያለው የፀጥታ ሁኔታ አሳሳቢ በመሆኑ ከክልሉ መንግስት ጋር መነጋጋር የግድ አስፈላጊ ኾኖ ተገኝቷል። ከትናንት በስትያ ማክሰኞ ኅዳር ዘጠኝ ቀን ሁለቱ ዋነኛ የኦሮሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለአሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት የእንነጋገር ይፋዊ ደብዳቤ ቢልኩም የክልሉ መንግስት ወዲያው መልስ አልሰጠም ።
የኦሮሚያ ክልል ስላለበት አሁናዊ አጠቃላይ ኹኔታ ከክልሉ መንግስት ጋር ለመነጋገር እንዳስገደዳቸው ፕሮፌሰር መረራ ለዶቼ ቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል። አብዛኛው የክልሉ አካባቢ በፀጥታ ችግር ውስጥ በወደቀበት ኹኔታ ቸል ብለን ማየት አልቻልንምም ይላሉ።
«ዋና ጉዳይ ፤ የኛ ችግር አብዛኛው ኦሮሚያ በሚባል ደረጃ ሰፊ ችግር ውስጥ ገብቷል። እና ስለዚህ ዝም ብለን እያየን ፣ ሕዝቡ ወጥቶ መግባት ካቃተው ፣ በየቦታው ከሕግ ውጭ ግድያዎች እየበዙ እየሰፉ ሲሄዱ እያየን ይህን ህዝብ እንወክላለን ብለን ዝም ብለን ደግሞ ዝም ብለን መቀመጡ አስቸጋሪ ስለሆነ ነው።»
ኅዳር ዘጠኝ ቀን፣ 2018 ዓ/ም የተጻፈው እና ለኦሮሚያ ክልል መንግስት ፕሬዚደንት ሺመልስ አብዲሳ መላኩን የሚያመለክተው እና በኦፌኮ ይፋዊ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ተለጥፎ የተመለከትነው ደብዳቤ እንደሚለው፦ «አቶ ዳዉድ ኢብሳ የኦነግ ሊቀመንበር እንዲሁም ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና የኦፌኮ ሊቀመንበር በኦሮሚያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር ቀጠሮ እንዲሰጠን እንጠይቃለን» ይላል።
የደብዳቤውን መላክ የኦነግ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ለሚ ገመቹ ለዶቼ ቬለ አረጋግጠዋል።
«በአጠቃላይ የደብዳቤው ይዘት ሁሉም የሚያውቀው ነገር ነው። አሁን ያለንበት እና ባለነው ነባራዊ ኹኔታ ይበጃል ብለን ሁለታችን ተነጋግረን የደረስንበት እና አሁን ካልተነጋገርን መች ነው? ለዛ ነው ለምክክሩ ቀጠሮ እንዲያዝልን የጠየቅነው።»
ከሁለቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተጻፈው ደብዳቤ ዛሬ ሦስተኛ ቀኑን ቢያስቆጥርም ከክልሉ ፕሬዚዳንት ሺመልስ አብዲሳ ቢሮ ፈጣን መልስ እንዳልተሰጠ ነው የኦነግ የኮሙኒኬሽን ኃላፊው የተናገሩት ።
«እስካሁን ገና ነው ያገኘነው መልስ የለም።»
ከዋነኞቹ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተጻፈውን ደብዳቤ በተመለከተየኦሮሚያ ክልል መንግስት ምላሽን ለማካተት ለክልሉ የፕሪዚዳንት ጽ/ቤት እና የኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎች የእጅ ስልክ ላይ በተደጋጋሚ ብንደውልም ስልካቸው ባለመነሳቱ ለዛሬ ሳይሳካልን ቀርቷል።
የኦፌኮ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እንደሚሉት በክልሉ ያለውን አጠቃላይ የጸጥታ እና የፖለቲካ ችግሮች በመነጋገር ለማስተካከል የክልሉ መንግስት ሚና የጎላ እንደሆነ ነው።
«ኳሱ በዚያኛው ሜዳ ነው ያለው ። እኛ ግን ከመገዳደል ፖለቲካ ወደ መደራደር ፖለቲካ አስፈላጊ ነው ብለን የምናምን ፓርቲዎች ነን ። በተለያዩ መንገዶችም እናነሳ ነበር ። አሁንም ደግሞ ያለው ሁኔታ እየባሰበት ስለመጣ መነጋገሩ አስፈላጊ ነው ብለን አምነንበታል።»
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና ኦፌኮ ከስድስተኛው ሃገራዊ ምርጫ ውጭ መሆናቸው ይታወሳል። በወቅቱ ሁለቱም ፓርቲዎች ከምርጫው ለመገለላቸው የየፓርቲዎቹን አመራር እና አባላት እስራትን ጨምሮ ለምርጫው አስቻይ ኹኔታዎች እንዳይኖሩ በማድረግ በምርጫውእንዳንሳተፍ መገፋት ደርሶብናል ሲሉ በመንግስት እና ገዢው ፓርቲ ላይ የሰላ ትችት እና ክስ ሲያቀርቡ ነበር።
ሰባተኛው ሃገራዊ ምርጫ በተመለከተ የፓርቲያቸውን ዝግጅት በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ የሰጡት ፕሮፌሰር መረራ ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ ያቀረቧቸው ጥያቄዎች መልስ ማግኘት እንደሚገባቸው ነው ያሳሰቡት።
«ሰባት ነጥቦች በተለያየ ጊዜ በተለይ የጥታ እና የፖለቲካ ምህኅዳርጥያቄዎች ካልተፈቱ የሚመጣው ምርጫ ምርጫ ምርጫ ሊሆን አይችልም። ከፖለቲካ ቴአትር ባለፈ ምርጫ ሊሆን አይችልም። ይህን መንግስትም የኢትዮጵያ ሕዝብም ፣ የዓለማቀፍ ማኅበረሰብም ፣ ሁሉም እንዲያውቅ አድርገናል።»
ኦፌኮ በ7ኛው የሃገራዊ ምርጫ ተሳትፎን በተመለከተም ለመናገር አሁን ያለው ሁኔታ አመቺ እንዳልሆነም ነው ፕሮፌሰሩ የተናገሩት ።
«ምርጫ ትገባላችሁ አትገቡም ፣ ምርጫ ውስጥ ትሳተፋላችሁ አትሳተፉም የሚለው አሁን የኢትዮጵያ ኹኔታ ባለበት ትርጉም የለውም። ፣ ምርጫው መሰረታዊ የሀገሪቱን የፖለቲካ እና የፀጥታ ችግር ይፈታል ወይስ አይፈታም ነው ፤ ዋናው መነጋገር ያለብን በዚህ ላይ ነው።»ኦፌኮ የሚገኝበት 10 የፖለቲካ ፓርቲዎች ባለፈው ኅዳር ሦስት ቀን፣ 2018 ባወጡት ባለ ሰባት ነጥብ የጋራ መግለጫ ቀጣዩ ሀገር አቀፍ ምርጫ ነጻ እና ፍትሃዊ እንዲሆን ያስችላል ያሏቸውን ቅድመ ኹኔታዎች ማስቀመጣቸው ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሳምንታት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ቀጣዩን ምርጫን በተመለከተ ሲናገሩ «ምርጫ ለማድረግ እንኳን ዘንድሮ በባለፈው ምርጫ አካሂደናል እኮ እየተዋጋን» በማለት ምርጫው አይቀሬ መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል።
ታምራት ዲንሳ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
























