«ኢትዮጵያ ለቀይ ባሕር ስትል ኤርትራን የመውረር ፍላጎት የላትም» - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
Description
«ኢትዮጵያ ለቀይ ባሕር ስትል ኤርትራን የመውረር ፍላጎት የላትም» - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
"ኢትዮጵያ ለቀይ ባሕር ስትል ኤርትራን የመውረር ፍላጎት የላትም" ሲሉ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ሐሙስ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ስያብራሩ "የቀይ ባሕር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የሕልውና ጉዳይ ነው" ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ትግራይ፣ መላው ኢትዮጵያ ጦርነት አይፈልግም፤ አይፈጠርም ብየም ተስፋ አደርጋለሁ" ያሉት ጠላይ ሚኒስትሩ "በድርድር በሰላም ጉዳያችን ለመፍታት" እንፈልጋለን ሲሉ ከመንግሥታቸው ጋር ለሚዋጉት ኃይሎች ጥሪ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከ18 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ስለ ሀገሪቱ ሰላምና ድህንነት፣ ፀጥታ፣ የገጠማት ቀውስ፣ ግጭትና የሚደርሰው ጉዳት፣ የባሕር በር ጥያቄ፣ የኢኮኖሚ እና የልማት ጉዳዮች ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 11 ቀን 2017 ዓ . ም ሰፊ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል። "የባሕር በር ጥያቄን ማንሳት ነውርነቱ አብቅቷል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዚህ ወቅት ለኢትዮጵያ የባሕር በር "አያስፈልግም የሚል የለም" ሲሉ ጥያቄው ተገቢ ስለመሆኑ በብዙዎች ዕምነት መያዙንና ይህም "ትልቅ ድል" መሆኑን አብራርተዋል። "ውኃ የማይቋጥር" ያሉት ብዙ ክስ መኖሩንም በዚሁ ጊዜ ጠቅሰዋል።
"ኢትዮጵያ ላይ ማንም ሀገር ወረራ ሊፈጽም እና ከጀመርነው ሕልም ሊያስቆመን ይችላል የሚል ሥጋት የለብንም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ማንም ደፍሮ አይሞክረንም" ሲሉም ተደምጠዋል። "ምላሹ ከፍተኛ ስለሚሆን" ምንም አይነት ትንኮሶ መኖር የለበትም የሚለውንም አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።
"ኢትዮጵያ ለቀይ ባሕር ስትል ኤርትራን የመውረር ፍላጎት የላትም"
ያነጋገርናቸው አንድ የፖለቲካ ተንታኝም ሁለቱ ሀገራት በምንም ኹኔታ ወደ ጦርነት ሊገቡ እንደማይገባ አመልክተዋል። ያ ከሆነ የብዙ አካላት እጅ ገብቶበት የከፋ ውድመትና ቀውስ እንደሚከሰት በማሳሰብ ጭምር። "በሁለቱ ሀገራት መካከል ሊፈጠር የሚችለው ግጭትም የሚያጠፋው የሰው ሕይወት፣ የሚያጠፋው ንብረት መጠን በጣም አስጨናቂ እና መገመት የሚያስቸግር ነው የሚሆነው" የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት ወዴት እያመራ ነው?
መንግሥትን ከሚዋጉት ጋር ስለሚደረግ ድርድር እና ውይይት
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "ከኦነጎችም፣ አማራ ክልል አካባቢ ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎችም ጋር ድርድር ነበር" ብለዋል። "በድርድር፣ በሰላም ጉዳዮችን ለመፍታት መንግሥት ሁልጊዜም እጁ የተዘረጋ ነው" ሲሉም አሁንም ቢሆን ለዚሁ ስኬት ተፋላሚዎቹ እንዲመጡ ሲሉ ጥሪ አድርገዋል። "መከላከያ በአማራ እና በኦሮሚያ ተበትኗል፣ ተወጥሯል እና ጊዜው አሁን ነው [ለማጥቃት] ብለው የሚያስቡ ግለሰቦች እንዳሉ እንሰማለን። ምክሬ አይመስለኝም፣ አያዋጣም፣ ተውት ነው"
በምክር ቤቱ ከተቃዋሚው አብን አባል የቀረበው የሰላ ትችት
ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል ኢትዮጵያ ለከፋ የፀጥታ እና የሰላም ቀውስ፣ ለእርስ በርስ ጦርነትና ግጭት መዳረጓ፣ ስልታዊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መኖራቸው፣ የተቃውሞ ድምጾች እመቃ መኖሩ፣ ብሔራዊ የደህንነት አደጋ ያዘለ ከፍተኛ ድህነት መኖሩንና መንግሥት ለተፈፀሙ ግዙፍ ወንጀሎች እውቅና የማይሰጠው ለምንድን ነው? የሚለው የተቃዋሚው ፓርቲ አብን አባል የሰነዘሩት ብርቱ ትችት ያዘለ ጥያቄ ይገኝበታል። "ነባር የመጠፋፋት ባሕል እና ፍረጃ" የግጭት ምክንያቶች መሆናቸውን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሰላ ትችት ላቀረቡባቸው የምክር ቤት አባል "መንግሥትን ሲተቹ አማራ ክልል ያለውን ሌላውን ችግር ፈጣሪ ኃይል ለምን አላዩም" ሲሉ መልሰዋል። በኢትዮጵያ መንግሥትና በኤርትራ ውዝግብ ላይ የፖለቲካ ተንታኝ አስተያየት
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሷቸው ሌሎች ዋና ዋና ጉዳዮች
የፕሪቶሪያን ስምምነት በተመለከተ በተማላ መልኩ ያልተፈፀሙ ያላቸው የትጥቅ ማስፈታት፣ መልሶ የማዋሃድ እና ተፈናቃዮችን የማስመለስ ሥራዎች መኖራቸውን ጠቅሰው ትግራይ ክልል ውስጥ "የሰብአዊነት ጉዳይ እና ፖለቲካ ተቀላቅሏል" ብለዋል። የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እስከ ቀጣዩ ምርጫ ለአንድ ዓመት እንደሚራዘም እና የአመራር ለውጥ እንደሚኖርም አመልክተዋል። የሀገሪቱ የዚህ ዓመት ዕድገቱ 8.4 በመቶ እንዲሆን ስለመታቀዱ ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በኢኮኖሚው ዘርፍ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ "ታይተው የማይታወቁ" ያሏቸው ውጤቶች ስለመመዝገባቸውም ተናግረዋል። የሕዳሴ ግድብን በሚመለከት "ቢበዛ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት በጋራ ሪባን እንቆርጣለን" በማለት ግድቡ በቅርቡ እንደሚመረቅ እና በቀጣይ መሰል ግዙፍ የማዳበሪያ ፋብሪካ የመትከል ሀገራዊ ትልም ስለመኖሩም በዛሬው ማብራሪያቸው ገልፀዋል።
ሰለሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ























