የጥቅምት 17 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
Description
አርሰናል በአንዲት ብቸኛ ግብ መሪነቱን ከማስጠበቅም በላይ ከተከታዬ በአምስት ነጥብ መራቅ ችሏል ። ለተወሰኑ ጊዜያት የደረጃ ሰንጠረዡን ሲመራ የቆየው ሊቨርሉል የቁልቁለት ሽምጡን ተያይዞታል ። ባዬርን ሙይንሽን በበላይነት እየገሰገሰ ነው ። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ የዓለም መድረኮች ድል ቀንቷቸዋል ። የቅዱስ ጊየርጊስ ስፖርት ማኅበር የቦርድ አባልት ምርጫ ማጨቃጨቁ ተዘግቧል ።
በሴቶችም በወንዶችም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እጩ ናቸው
አትሌት ትእግስት አሠፋ ከሴቶች እንዲሁም አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ ከወንዶች ከስታዲየም ውጪ የዓመቱ ምርጥ አትሌት እጩ ውስጥ መካተታቸውን የዓለም አትሌቲክስ ይፋ አድርጓል ። በበይነ መረብ ድምፅ አሰጣጡ የፊታችን እሁድ እንደሚጠናቀቅ የዓለም አትሌቲክስ ዐሳውቋል ። በሴቶች እና በወንዶች ምድብ ከኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ባሻገር አምስት አምስት በድምሩ ዐሥር እጩዎች ይገኙበታል ።
በሴቶች ከትእግስት አሰፋ ጋር የሚፎካከሩት እጩዎቹ፦ ትውልደ ኢትዮጵያዊት የሆላንድ ሯጭ ሲፋን ሐሰን፣ ኬኒያዊያቱ ፔሬዝ ጄፕቺርቺር፤ አንገስ ንጌቲች፤ እንዲሁም ስፔናዪቱ ማሪያ ፔሪዝ ናቸው ። በወንዶች ደግሞ፦ የብራዚሉ ካዮ ቦንፊም፣ ካናዳዊው ኤቫን ዱንፊ፣ የኬኒያው ሠባስቲያን ሳዌ እንዲሁም የታንዛኒያው አትሌት አልፎንስ ሲምቡ ከኢትዮጵያዊው ዮሚፍ ጋር ይፎካከራሉ ። የድምፅ አሰጣጡ በዓለም አትሌቲክስ የፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ኤክስ የቀድሞው ትዊተር ላይ እንደሚከናወንም ተገልጧል ።
በዓለም መድረክ የአትሌቲክስ ፉክክሮች ኢትዮጵያውያን አሸንፈዋል
እሁድ ጥቅምት 16 ቀን፣ 2018 ዓ.ም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በተከናወኑ የአትሌቲክስ ፉክክሮች ኢትዮጵያውያን አሸንፈዋል ። በቫሌንሽያ ግማሽ ማራቶን የወንዶች ውድድር ኢትዮጵያዊው አትሌት ዮሚፍ ቀጀልቻ 58:02 በመሮጥ አሸናፊ ሁኗል ። የቡሩንዲው ሮድሪግ ክዊዜራ እንዲሁም ኬኒያዊው ብሪያን ኪቦር ከዮሚፍ በ37 ሰከንዶች ተቀድመው ሁለተኛ እና ሦስስተኛ ወጥተዋል ።
በሴቶች ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ፎትየን ተስፋይ በ 65:05 በማጠናቀቅ 2ኛ ደረጃ ወጥታለች ። በዚህ ውድድር፦ ኬኒያዊቷ አንገስ ጄቤት ንጌቲች (1:03:08 ) በመሮጥ አንደኛ ወጥታለች።
ጀርመን ፍራንክፉርት ከተማ ውስጥ እናንት በተከናወነው 42ኛው የፍራንክፈርት ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሴቶችም በወንዶችም አሸንፈዋል ። በወንዶች ፉክክር፦ ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ደረጃ ተከታትለው በድል አጠናቅቀዋል ። በውድድሩ አትሌት በላይ አስፋው (2:06:16 ) በመሮጥ አሸናፊ ሆኗል ። አትሌት ተሬሳ ቤኩማ፣ አትሌት ሹራ ቂጣታ፣ ይስማው ይታየው፣ ያሲን ሐጂ እና ጌታቸው ማስረሻ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከሁለተኛ እስከ ስድስተኛ ደረጃ አግኝተዋል ።
በሴቶች ፉክክር፦ ቡዜ ድሪባ ቀጀላ ( 2:19:34 ) አንደኛ ወጥታለች ። ኬኒያዊያት አትሌቶች ማግዳሊን ማሳይ፣ ሻሮን ቼሊሞ እና ካትሪን ቼሮቲች ሁለተኛ እና አራተኛ ደረጃ ይዘዋል ። ኢትዮጵያዊያቱ ምሕረት ገመዳ፣ ዐይንአዲስ ተሾመ እንዲሁም ዳኛቸው አያልም ኬንያዊያቱን ተከታታትለው እስከ ሰባተኛ ደረጃ በማግኘት አጠናቅቀዋል ።
በአየርላንድ ደብሊን ማራቶን አትሌት ኤቢሴ አዱኛ (2:26 .28) አሸንፋለች ። አትሌት ቀና ግርማ ሁለተኛ ስትወጣ አትሌት አፀደ ባይሳ (2:27:12 ) ሦስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቅቃለች ። በወንዶች አትሌት ማናዞት ሥዩም (2:09:09 ) ሁለተኛ ደረጃ አግኝቷል ። የጥቅምት 10 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
በሊዝበን ግማሽ ማራቶንም በሴቶች አትሌት ጫልቱ ዳዲ በወንዶች አትሌት ሚኪያስ ባረጋ ሁለቱም በተመሳሳይ ሁለተኛ ደረጃ ይዘው አጠናቅቀዋል ። በቻይና ሻንግሀይ የ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ውድድር ደግሞ፦ አትሌት አስማረች አንሊ (31፡10) አንደኛ ወጥታለች ። በፖርቹጋል የሊዝበን ማራቶን የሴቶች ፉክክር አትሌት አበበች አፈወርቅ (2:29 .00) በመግባት አሸናፊ ሁናለች ። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት አስማሬ በየነ (2:29:09 ) በሁለተኛ ደረጃ አጠናቅቃለች ። በወንዶች ፉክክር አትሌት ጋዲሳ ብርሀኑ ሁለተኛ ልመንህ ጌታቸው ሦስተኛ አግኝተዋል ።
አርሰናል ሽቅብ ሊቨርፑል ቁልቁል ሽምጥ ጀምረዋል
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፦ መሪው አርሰናል ዳግም ድል ቀንቶታል ። ትናንት በ39ኛው ደቂቃ ላይ ክሪስታል ፓላስ ላይ በኤቤሪች ኤዜ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ድል የተቀዳጀው አርሰናል ነጥቡን 22 አድርሷል ። በርመስ በ18 ሁለተኛ፤ ቶትንሀም እና ሠንደርላንድ በ17 እስከ አራተኛ ደረጃ በተከታታይ ሰፍረዋል ። በአስቶን ቪላ የ1 ለ0 ሽንፈት ያስተናገደው ማንቸስተር ሲቲ እና ብራይተንን 4 ለ2 ያበራየው ማንቸስተር ዩናይትድ በተመሳሳይ 16 ነጥብ ሆኖም በግብ ክፍያ አምስተኛ እና ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ። ሊቨርፑል እና አስቶን ቪላ በ15 ነጥብ ሰባተኛ እና ስምንተኛ ላይ ናቸው ። በተለይ ሊቨርፑል በብሬንትፎርድ ሜዳ 3 ለ2 ዳግም ሽንፈት መከናነቡ የቡድኑን የቁልቁለት ጉዞ አፋጥኖታል ።
በጀርመን ቡንደስሊጋ፦ መሪው ባዬር ሙይንሽን ቦሩሲያ ሞይንሽንግላድባኅን 3 ለ0 በሜዳው ኩም አድርጎት ነጥቡን 24 አድርሷል ። ተከታዩ ኤር ቤ ላይፕትሲሽ በ19 ነጥብ፤ ትናንት ማይንትስን 2 ለ1 ያሸነፈው ሽቱትጋርት በ18 ሁለተኛ እና ሦስተኛ ናቸው ። ኤር ቤ ላይፕትሲሽ አውግስቡርግን በሜዳው የግብ ጎተራ አድርጎት 6 ለ0 አንኮታኩቶታል ። ቅዳሜ ዕለት ኮሎኝን 1 ለ0 ድያሸነፈው ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ17 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይንገታገታል። የጥቅምት 3 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
የቅዱስ ጊየርጊስ ስፖርት ማኅበር ጠቅላላ ጉባኤ ለምን አጨቃጨቀ?
የቅዱስ ጊየርጊስ ስፖርት ማኅበር ጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባውን እሁድ ጥቅምት 16 ቀን፣ 2018 ዓ.ም በቀድሞ ግሎባል ሆቴል በአሁኑ ኢትየጵያ ሆቴል ቁጥር 2 አካሂዷል ። የስፖርት ማኅበሩ «በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ» ያለው ስብሰባ ጭቅጭቅ እና ንትርክ የነበረበት አንዳንዶችም ስብሰባውን ረግጠው የወጡበት መሆኑ ተዘግቧል ። በስብሰባው የታደመው የስፖርት ጋዜጠኛ ዖምና ታደለ፦ «ባለፉት አምስት ዓመታት ማኅበሩ 161 ሚሊዮን ብር እዳ ውስጥ» ይገኛል መባሉን ገልጧል ። ይህም በቡድኑ ላይ ተጽእኖ እንደሚያሳድር ተገልጧል ። የቅዱስ ጊየርጊስ ስፖርት ማኅበር ለመጪው አራት ዓመታት ስፖርት ማኅበሩን የሚመሩ የቦርድ አባላት በደጋፊዎች መመረጣቸውን ይፋ አድርጓል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሠ























