ማሕደረ ዜና፣ የASEAN ጉባኤ፣ የትራምፕ ጉብኝትና የሲኖ-አሜሪካ ድርድር
Description
የደቡብ ምሥራቅ እስያ መንግሥታት ማሕበር (AEAN) ጉባኤ ትናንት ኩዋላ ላፑር-ማሌዢያ ዉስጥ ተጀምሯል።በየጊዜዉ እንደሚደረገዉ ሁሉ ጉባኤዉ ከ11ዱ የማሕበሩ አባል ሐገራት መሪዎች በተጨማሪ ከደቡብ አፍሪቃ እስከ ኒዉዚላንድ፣ ከጃፓን እስከ ብራዚል የሚገኙ ሐገራት መሪዎች ተጋብዘዉበታል።ኮኮቡ ግን የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ናቸዉ።ጉባኤተኞችንም፣ተጋባዦችንም ሌላዉንም ዓለም በቀረጥ ጭማሪ «ዱላ» የሚዠልጡት ዶናልድ ትራምፕ በየደረሱበት የስብሰባ-ጉባኤ ልዩ እንግዳ የመሆናቸዉ ምክንያትና ጉልበት በርግጥ ያነጋግራል።የአስያን ጉባኤ መነሻ፣የትራምፕ ኮኮብነት ማጣቃሻ፣ ምክንያቱ መድረሻችን ነዉ። ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።
ASEAN በግጭትና ሠላም፣ በዉዝግብና ዕድገት መሐል
ታይላንድና ካምቦዲያ ሁለቱም የደቡብ ምሥራቅ እስያ መንግሥታት ማሕበር (ASEAN) አባላት ናቸዉ።ሁለቱ መንግሥታት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሲዋጉ ነበር።ፊሊፒንስ የማሕበሩ አባል ናት።የእስያዋ ልዕለ ኃያል፣ የዓለም ሁለተኛ ሐብታም ቻይና የማሕበሩ ቀጥታ አባል ባትሆንም የዉይይት አጋር በሚል ማዕረግ ከማሕበሩ ጋር ጥብቅ ግንኙነት አላት።የማኒላና የቤጂንግ መሪዎች በደሴቶችና በባሕር ክልል ይገባኛል ሰበብ ይወዛገባሉ፣ አንዳዴ ይጋጫሉ።
ምያንማር የASEAN አባል ናት።በወታደራዊ ሁንታ የምትገዛ ሐገር ናት።ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾች በተደጋጋሚ እንዳሉት በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የያዘዉ ወታደራዊ ሁንታ፣ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ የሮሒንጂያ ሙስሊሞችን ገድሏል።ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉትን አባርሯል።ባንድ በኩል በሮሒንጃያዎች ላይ የተዋለዉን ግፍ፣ በሌላ በኩል መፈንቅለ መንግሥቱን ከሚቃወሙ አማፂያን ጋር ይዋጋል።
አማፂያኑ እንደ ፖለቲካ፣ ርዕዮተ ዓለም ዝንባሌያቸዉ የማሕበሩ አባል በሆኑ ሐገራት ይደገፋሉ።ያምሆኖ ማሕበሩ የሚያስተናብራቸዉ አብዛኞቹ ሐገራት ግጭት-ጦርነት እንዳይባባስ የሚያደርጉት ጥረት፣ በምጣኔ-ሐብቱ መስክም ብዙዎች እንደሚሉት የተሻለ ዕድገት እያሳዩ ነዉ።
የአንዋር ኢብራሒም መልዕክትና የጉባኤዉ ልዩ እንግዳ መርሕ ግጭት
ትናንት የተጀመረዉ የ47ኛዉ ጉባኤ አስተናጋጅ የማሌዢያዉ ጠቅላይ ሚንስትር አንዋር ኢብራሒም እዳሉትም ማሕበራቸዉ ከግጭት ይልቅ ድርድርን፣ ከክፍፍል ይልቅ መግባባትን አጠናክሮ ይቀጥላል።
«ከኃይል ይልቅ ድርድርን፣ ከመከፋፈል ይልቅ ሚዛናዊነትን፣ ከፍጥጫ ይብስ ትብብርን ማስረፅ እንደሚያስፈልግ መቀስቀሳችንን እንቀጥላለን።የዓለም ሠላምና ፀጥታ እንዲፀና፣የጋራ ትብብር እንዲጠናከር ና ዓለም አቀፍ ሕግ እንዲከበር ያለንን አቋማችንን እናረጋግጣለን።»
የማሌዢያዉ ጠቅላይ ሚንስትር መልዕክትካንጀት-ይሁን ካንገት በርግጥ ማረጋገጪያ የለም።ያሉትን ያሉት ግን ከትብብር ይልቅ ኃያልነትን፣ ከጋራ ጥቅም ይልቅ ተናጠልነትን፣ ከድርድር በፊት ቅጣትን-የሚመርጡ ወይም ሚያራምዱትን፣ የ«አሜሪካ ትቅደም» መርሕን የሚያቀነቅኑት ዶናልድ ትራምፕን ከየትኛዉም እግዳ በላይ ለማስተናገድ ኢብራሒም ጠብ እርግፍ በሚሉበት መሐል ነዉ።
ዶንልድ ትራም እሳቤ፣ የአሜሪካ ክብር
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈዉ መስከረም እንዳሉት አሜሪካን ዳግም ታላቅ የማድረግ ምኞት፣ መርሕ ይሁን ዕቅዳቸዉ በስምንት ወራት ዉስጥ ተሳክቶላቸዋል።አሜሪካ ዳግም «ተከብራለች» አሉ ትራምፕ።
«በዓለም መድረክ አሜሪካ ከዚሕ ቀደም ተከብራ በማታዉቀዉ ደረጃ ዳግም ተከብራለች።ከ2 ዓመት፣ ከ3 ዓመት፣ ከ4ዓመት ወይም ከአንድ ዓመት በፊት እንኳን የመላዉ ዓለም መሳቂያ ነበርን።»
እርግጥ ነዉ የቀድሞዉ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆ ባንይደን በጥቂት ጉባኤና አጋጣሚዎች ላይ ማንጎላጀት፣ መዘባረቃቸዉ ዓለምን ላፍታ ፈገግ ማሰኘቱ አይካድም።የሰዉዬዉ ሥሕተት ግን ከእድሜና፣ ከጤና እጦት ጫና ባለፈ አሜሪካን መሳቂያ የሚያደርግ አልነበረም።
ከመጀመሪያዉ የዓለም ጦርነት ፍፃሜ ወዲሕ አሜሪካ ተፈርታም ይሁን ተወድዳ ያልተከበረችበት ዘመን የለም።
የዓለም መሪዎች የሚሽቆጠቆጡት ለትራም ወይስ ለአሜሪካ
ይሁንና ፕሬዝደንት ትራምፕ ሥልጣን ከያዙ ወዲሕ የአዉሮጳ ይሁን፣ የአፍሪቃ፣ የእስያ ይባል የደቡብ አሜሪካ መሪዎች ለትራምፕ ማሸርገዳቸዉ ለአሜሪካ እንደተሰጠ ክብር አይተዉት ከሆነ በርግጥ ትራምፕ አልተሳሳቱም።
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬኑን ፕሬዝደንት ቮልድሚር ዜለንስኪን ሲቆጡ ወይም የሩሲያዉን ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲንን ለማነጋገር ሲዘጋጁ የአዉሮጳ መሪዎች ዋሽግተን ድረስ ተጉዘዉ የትራምፕን «መመሪያ» አከል መልዕክት በንቃት ሲደምዙ ከቴሌቪዥን ካሜራ ፊት እንኳን አልተደበቁም።
ዶናልድ ትራምፕ በቴል አቪቭ አደባባይ ከእስራኤል መሪዎች በላይ ሲደነቁ፣ እየሩሳሌም አዳራሽ ዉስጥ የእስራኤል መሪዎችና ፖለቲከኞች ቁጭ ብድግ እያሉ ሲያጨበጭብሏቸዉ፣ ሻርም አልሼክ ዉስጥ የዓረብ፣ የሙስሊም የአዉሮጳ መሪዎች ለመለማመጥ ሲሻሙባቸዉ በቴሌቪዥን መስኮት አይተናል።
ሥለዚሕ ለትራምፕ የዓለም መሪዎችን አጎበደዱ እንጂ ወትሮም የምትከበረዉ አሜሪካ አዲስ ክብር አላገኘችም።ደግሞም መሪዎች ወይም ፖለቲከኞች እንጂ ሕዝብ በፊትም አሜሪካንን አልናቀም ዛሬም ለትራምፕ አላጎበደደም።
«መሪዎቻችን ስለሚፈሩ» የኩላ ላፑሩ ተቃዉሞ ሠልፈኛ
በተቃራኒዉ ከሰባት ሚሊዮን የሚበልጥ የሐገራቸዉ ሕዝብ በአደባባይ ሠልፍ ተቃዉሟቸዋል።ትናንት ዕሁድ ኩዋላ ላምፑር ከግባታቸዉ በፊትና ሲገቡም ሕዝብ ባደባባይ ሠልፍ ተቃዉሟቸዋል።የሰልፈኞቹ የተቃዉሞ ዋና ዋና ክንያቶች ሁለት ናቸዉ።የጋዛዉ እልቂት አንድ፣ የቀረጥ ወይም ታሪፍ ጭማሪ ሁለት።ሰልፉን ካስተባበሩት አንዱ የቀድሞዉ የማሌዢያ ምክር ቤት አባል ማይክል ጄያኩመር ዴቫራጅ ደግሞ «መሪዎቻችን ሥለሚፈሩ» ብለዉ የምክንያቱን ምክንያት አፈረጡት።
«መሪዎቻችን የቀረጥ (ታሪፍ) ማዕቀብ ይጣልብናል ብለዉ ይፈራሉ።ሥለዚሕ እኛ ታሪፉ እንዲቀንስ (ትራምፕን) እንለምናቸዋልን።በኛ ላይ ከታይላንድና ከኢንዶኔዥያ የበለጠ ታሪፍ ከተጣለ ማሌዢያ ትጎዳለች።»
ዶናልድ ትራምፕ ባለፈዉ መስከረም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር አስቆምኳቸዉ ካሏቸዉ 7 ጦርነቶች (የጋዛ ሲጨመር 8 ሆኗል) አንዱ የካምቦዲያና የታይላንድ ዉጊያ ነበር።
የኩዋላ ላፑር የሰላም ዉል-የትራምፕ መልዕክት
ሁለቱ ASEAN ማሕበር አባላት የገጠሙትን ጦርነት እንዲያቆሙ የተለያዩ ሐገራት ዲፕሎማቶች ግፊት አድርገዋል።ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕም ሁለቱ መንግሥታት ዉጊያዉን ካላቆሙ በቀረጥ ጭማሪ እንደሚቀጧቸዉ አስጠንቅቀዉ ነበር።
የሁለቱ መንግሥታት ዲፕሎማቾችና የጦር አዛዦች በተከታታይ ያደረጉትን ድርድር ያስተናገዱ፣ ያግባቡና ሸመገልናዉን የመሩት የማሌዢያ ባለሥልጣናት ናቸዉ።ዉጊያዉ ከቆመም ሳምንታት አለፉት።የተኩስ አቁም ሥምምነቱ ግን ለልዩ እንግዳዉ «ገፀ-በረከት» እንዲሆን እስከ ትናንት ድረስ ቆይቶ ትናንት ትራምፕ በተገኙበት ተፈረመ።
«አሁን እንግዲሕ እኒሕ የተከበሩ ሰዎች የኩዋላ ላንፑር የሰል ዉል የምንለዉን ሥምምነት ሊፈርሙ ነዉ።ጥሩ ስም ነዉ።ሁለቱም ሐገራት ሁሉንም ግጭቶች ለማቆምና ጥሩ የጉርብትና ግንኙነትን ለመገንባት ተስማምተዋል።ይሕ ደግሞ ቀደም ሲል ተጀምሯል።»
የASEAN አባል ያልሆኑ መንግስታት መሪዎች
ትናንት በተጀመረዉ የASEAN ጉባኤ ላይ ከዩናይትድ ስቴትስ በተጨማሪ የማሕበሩ አባላት ያልሆኑ የአዉስትሬሊያ፣ የብራዚል፣ የቻይና፣ የጃፓን፣ የሕንድ፣ የደቡብ ኮሪያ፣የደቡብ አፍሪቃ፣ የካናዳ፣ የኒዉዚላንድና የሌሎች ሐገራት መሪዎች ወይም ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተገኝተዋል።
መሪዎቹ ወይም ባለሥልጣናቱ ከጉባኤዉ ጎን ለጎን የሚያደርጉት የሁለትዮሽና የጋራ ዉይይት የጋራ ግንኙነታቸዉን ለማጠናከር ምናልባትም የዓለምን ፀጥታና የምጣኔ ሐብት ግንኙነትን ለማሻሻል ይጠቀሙበታል ተብሎ ይጠበቃል።
የአሜሪካና የቻይና የንግድ ጦርነት
በከፍተኛ ጉጉት የሚጠበቀዉና በጥንቃቄ ይደረጋል ተብሎ የሚታሰበዉ ግን በዩናይትድ ስቴትስና በቻይና መሪዎች መካከል ሊደረግ የታቀደዉ ድርድር ነዉ።የዓለም አንደኛና ሁለተኛ ሐብታም ሐገራት የሚያደርጉት የሸቀጥ ንግድ ልዉዉጥ በዓመት ወደ 6 መቶ ቢሊዮን ዶላር ይገመታል።ዩናይትድ ስቴትስ ወደ ቻይና ከምትልከዉ ሸቀጦች ይልቅ ከቻይና የምታሥገባዉ ይበልጣል።ከ1980ዎቹ ማብቂያ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ጀምሮ እየናረ የመጣዉ የንግድ ተባለጥ የቀድሞዉን ቱጃር ነጋዴ ዶናልድ ትራምፕን ማብሰልሰል የጀመረዉ ከ190ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ነዉ።
ትራምፕ በመጀመሪያዉ ዘመነ-ሥልጣናቸዉ በ2018 ከቻይና ወደ አሜሪካ በሚገቡ የተወሰኑ የቻይና ሸቀጦች ላይ የቀረጥ (ታሪፍ) ጭማሪ ሲያደርጉ የሁለቱ ሐገራት የንግድ ጦርነት ተጫሪ።
ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ሥልጣን ሲይዙ፣ ትራምፕ የጣሉትን የቀረጥ ጭማሪ አልሰረዙም።ይሁንና ተጨማሪ ቀረጥ ባለመጣላቸዉ ጦርነቱ ቀዝቀዝ ብሎ ዶናልድ ትራምፕ ዳግም ሥልጣን ሲይዙ በቻይና ሸቀጦች ላይ እስከ 145 በመቶ የሚደርስ ቀረጥ በመጣላቸዉ ጦርነቱ ናረ።የቻይና አፀፋም ቀጠለ።
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በ2018 «የንግድ ጦርነት ቀላል ነዉ።ደግሞም እናሸንፋለን» ብለዉ ነበር።
«ቻይና በትራምፕ ዱላ አሜሪካንን መታች»
የቻይና አፀፋ ግን እየከፋ መጣ። እንዲያዉም ከተንቀሳቃሽ ሥልክ እስከ ኤሌክትሪክ መኪኖች ለሚገኙ ለብዙ የቴክኖሎጂ ዉጤቶች የሚያገለግለዉ ማዕድን (ሬር ኧርዝ) ሞልተ የተረፋት ቻይና ማዕድኑ ወደ ዉጪ እንዳይወጣ እንደምትቆጣጠር ዘንድሮ ማስፋራት ይዛለች።
ቤጂንጎች ሲያመሩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ «የንግድ ጦርነት ቀላል ነዉ አልኩ እንጂ---ከቻይና ጋር ማለቴ አልነበረም» ማለታቸዉ ተዘገበ።ዘ-ኤኮኖሚስት የተሰኘዉ መፅሔት ደግሞ በቀደም «ቻይና በትራምፕ ዱላ አሜሪካናንን ደበደበች» አለ።የሁለቱ ሐገራት የንግድና የኤኮኖሚ ባለሥልጣናት ሰሞኑን ለ5ኛ ዙር እየተደ,ራደሩ ነዉ።የቻይና ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ጉዮ ጂያኩን ዛሬ እንዳሉት ዉይይቱ የሰከነና መግባባት የታየበት ነዉ።
«ሁለቱ ርዕሳነ ብሔራት ባደረጉት መግባባት መሠረት የሚመሩት የሁለቱ ወገኖች (ባለሥልጣናት) ሁለቱን ወገኖች በሚያሳስቡ በዋና ዋና የኤኮኖሚ የንግድ ጉዳዮች ላይ የተረጋጋ፣ ጥልቅና ገንቢ ዉይይት አድርገዋል።አንዳቸዉ ለሌላቸዉ አሳሳቢ ጉዳዮች መልስ ለመስጠት በሚረዱ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ተግባብተዋልም።ሁለቱ ወገኖች ዝርዝር ጉዳዮችን ይበልጥ ለመለየት በየሐገራቸዉ ለማፀደቅ ተስማምተዋልም።»
አፅዳቂዎቹ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕና ሊቀመንበር ሺ ጂኒንግ ናቸዉ።ሁለቱ መሪዎች የፊታችን ሐሙስ ደቡብ ኮሪያ ዉስጥ ለመነጋገር ቀጠሮ አላቸዉ።
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሰ























