DiscoverDW | Amharic - Newsየካሜሩን ፖለቲካዊ ቀውስ
የካሜሩን ፖለቲካዊ ቀውስ

የካሜሩን ፖለቲካዊ ቀውስ

Update: 2025-10-27
Share

Description

የካሜሩን ሕገመንግሥታዊ ምክር ቤት አዛውንቱ ፓል ቢያ በሀገሪቱ በተካሄደው ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ማሸነፋቸውን ዛሬ ይፋ አድርጓል። የምርጫው ውጤት ከመነገሩ አስቀድሞ በተቀሰቀሰው ውጥረት የተቃዋሚዎቹ ደጋፊዎች ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ተጋጭተው ቢያንስ የአራት ሰዎች ሕይወት ማለፉ፤ በርካታ የፀጥታ ኃይሎችም መጎዳታቸውም ተዘግቧል።



የካሜሮኑ አዛውንት መሪ



ከዓለማችን አዛውንት የሀገር መሪዎች አንዱ ናቸው የካሜሮኑ ፖል ቢያ። 92 ዓመት ደፍነዋል። ከጎርጎሪዮሳዊው 1981 ዓ,ም ጀምሮ የካሜሮን ፕሬዝደንት እሳቸው ናቸው። የሥልጣን ዘመናቸው ሲሰላ 43 ዓመት መሆኑ ነው። አብዛኛውን ጊዜያቸውን ስዊዘርላንድ የሚያሳልፉት ቢያ የካሜሮንን የዕለት ተዕለት የአስተዳደር ሥራ በታማኞቻቸው እንደሚዘውሩት ይነገራል።



ዛሬ የሀገሪቱ ሕገመንግሥታዊ ምክር ቤት ለቀጣይ ተጨማሪ ዓመታት በሥልጣን የሚያሰነብታቸውን የስምንተኛ ጊዜ ዘመን አጎናጽፋቸዋል።



እንደሕገመንግሥታዊ ምክር ቤቱ መግለጫ ጥቅምት 2 ቀን 2018 ዓ,ም በካሜሮን በተካሄደው ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ቢያ የመራጩን 53,7 በመቶ ድምፅ አግኝተዋል። ዋነኛ ተፎካካሪያቸው የነበሩት ቺሮማ ባካሪ ደግሞ 35,2 በመቶ ድምፅ በማግኘት በሁለተኛ ደረጃ አጠናቀዋል።





የሕዝብ ቁጣ ያስነሳው የምርጫ ውጤት



30 ሚሊየን ገደማ የሚሆን ሕዝብ ባላት ካሜሮን የፖለቲካ ውጥረቱ ገና ምርጫው ከመካሄዱ አስቀድሞ ነው የጀመረው። መንስኤው ከግማሽ በላይ ዕድሜያቸውን በሥልጣን ላይ የከረሙት ፕሬዝደንት ፖል ቢያ ለስምንተኛ ጊዜ ለምርጫ ውድድር እቀርባለሁ ብለው መነሳታቸው ሲሆን፤ ድርጊታቸው የሀገሪቱን ወጣቶች እና የተቃውሞ ፖለቲከኞችን አስቆጣ።



ቢያ ግን የምርጫ ቅስቀሳቸውን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሳይቀር ቀጠሉ፤ ባለፈው መስከረም ወርም በገሀድ እየወጡ በሥልጣን መንበሩ ለመስንበት የካሜሮን ሕዝብ ተጨማሪ ዕድል እንዲሰጣቸው ቀሰቀሱ። ተቺዎቻቸው ቢያ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን ያሰራጩት የቅስቀሳ መልእክት በድሮ ፎቶዎቻቸውን የታጀበ ነው ይላሉ። በምርጫው ዋነኛ ተፎካካሪያቸው የሆኑት የቀድሞው ሚኒስትር ቺሮማ ባካሪ ተቀባይነት እንዳያገኙ ያደርጋሉ፤ ውጤቱን ለማዛባትም የመንግሥትን አቅም ተጠቅመዋል በሚል ይከሷቸዋል።



ዛሬ የተሰማውን የምርጫ ውጤቱ ውድቅ ያደረጉት ባካሪ የካሜሮን ዜጎች ድምጻቸውን ለማስከበር እንዲነሱ ጥሪ አቅድርገዋል። እንዲያም ሆኖ ገና የምርጫው ውጤት ይፋ ሳይደረግ ጀምሮ እንዳይጭበረበር የሰጉ የካሜሮን ወጣቶች ድምፃቸው እንዲከበር አደባባይ መውጣታቸውን አራት የተቃውሞ ሰልፈኞች የሞቱባት የወደብ ከተማዋ ዱዋላ ነዋሪ ያስረዳል።



«አየህ፤ ወጣቱ የተሰረቀበትን ድምፁን ለማስመለስ ነው የወጣው። በእነሱ ሃሳብ እስማማለሁ። ታቺሮማ ባካሪ ማሸነፉን በግልፅ አይተናል፤ ነገር ግን መንግሥት ያንን ይክዳል።»



ሌላዋ ተቃውሞ የተጠናከረባት የዱዋላ ከተማ ነዋሪ እበበኩሏ ካሜሮን ውስጥ ያለው ማኅበራዊና ኤኮኖሚያዊ ሁኔታ ሕዝቡን አስከፍቷል ነው የምትለው።



«እውነት ለመናገር ሕዝቡ ደስተኛ አይደለም። እናም ትክክል ናቸው። ምክንያቱም ለ40 ዓመታት ስንሰቃይ ኖረናል። ነገሮች በጥሩ ሁኔታ እየሄዱ አይደለም። ልጆች እየተሰቃዩ ነው። የተማሩ ወጣቶች ሥራ የላቸውም። ካሜሮን ውስጥ ምግብ እንኳ እየበላን አይደለም። ህክምናም አናገኝም። ሰልችቶናል።»





የደረሰ ጉዳት



በዚች ከተማ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ከጸጥታ ኃይሎች ጋር መፋጠጣቸውን ተከትሎ የአራት ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፤ በርካታ የጸጥታ ኃይሎችም ተጎድተዋል። ከመቶ በላይ የሚሆኑ ዜጎችም ታስረዋል።



ፖል ቢያ ካሜሩን ከቅኝ ገዢዎቿ ከተላቀቀች ወዲህ ሥልጣን ከያዙ የሀገሪቱ ዜጎች ሁለተኛው ፕሬዝደንት ናቸው። ቢያ ሀገሪቱን በጠንካራና ጨቋኝ ክንድ እንደሚመሩና ተቃዋሚዎቻቸው ላይም ከፍተኛ ጫና ያደርጋሉ በሚል ይወቀሳሉ። ሥልጣን ላይ የመቆየታቸው ምስጢር ደግሞ ማኅበራዊ ቀውስን ማባባስ፤ ኤኮኖሚዊ ፍትህ አለመኖር እና የተገንጣዮች አመጽ መቀጣጠል ነው።



የአፍሪቃ ውስጥ የሚመሳሰል ታሪክ ያላቸው የጊኒው አቻቸው ቶኦዶር ኦቢያንግ ንጌዌማ ምባሶንጎ ናቸው በዕድሜ የሚቀርቧቸው፤ 83 ዓመት። እሳቸውም ለሀገራቸው ሁለተኛው ፕሬዝደንት ናቸው። ጅቡቲም የፕሬዝደንትን ዕድሜ የሚገድበውን ሕግ ሰርዛለች። የአፍሪቃ ፖለቲከኞችና የሥልጣን ቆይታቸው አነጋጋሪ እየሆነ ነው።



በጀርመን፤ በፈረንሳይ እና እንግሊዝ ቅኝ የተገዛችና በፈረንሳይኛ እና እንግሊዝኛ ተናጋሪዎች ጎራ የተከፋፈለችው ፖል ቢያ ከጎልማሳነታቸው እስኪያረጁ የገዟት ካሜሮን አሁን መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆማለች።



ሸዋዬ ለገሠ



ፀሐይ ጫኔ

Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

የካሜሩን ፖለቲካዊ ቀውስ

የካሜሩን ፖለቲካዊ ቀውስ

ሸዋዬ ለገሠ Shewaye Legesse