DiscoverDW | Amharic - Newsሱዳን ኤልፋሽር ከተማ «ከ2,000 በላይ ያልታጠቁ ሰዎች» ተገደሉ
ሱዳን ኤልፋሽር ከተማ «ከ2,000 በላይ ያልታጠቁ ሰዎች» ተገደሉ

ሱዳን ኤልፋሽር ከተማ «ከ2,000 በላይ ያልታጠቁ ሰዎች» ተገደሉ

Update: 2025-10-28
Share

Description

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ሚሊሻዎች (RSF) በምዕራባዊ የአገሪቱ ክፍል የምትገኘው የኤልፋሸር ከተማን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠራቸውን ዐሳውቀዋል ። የዜና ምንጮች እንደሚሉት፦ ጎሳ ላይ ያነጣጠር ጥቃት ዛሬ በከተማዪቱ ዐይሏል ።



በምሥራቅ ሱዳን 260.000 ግድም ያልታጠቁ ሰዎች አጣብቂኝ ውስጥ የሚገኙባት የኤልፋሽር ከተማን የተቆጣጠሩ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ሚሊሻዎች (RSF) መጠነ ሰፊ ግድያ መፈጸማቸው ተገለጠ ። በኤልፋሽር ከተማ ከበባ ውስጥ ከሚገኙት ነዋሪዎች መካከል ግማሽ ያህሉ ሕጻናት ናቸው ተብሏል ።



«ከ2,000» በላይ ያልታጠቁ ሰዎች ግድያ



የሱዳን ጦር ሠራዊት ደጋፊ የሆኑ ኃይላት እንደሚሉት ከሆነ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አባላት «ከ2,000» በላይ ያልታጠቁ ሰዎችን ገድለዋል ። አብዛኞቹ በጥይት ተደብድበው የተገደሉ ሰዎች ሕጻናት እና ሴቶች እንደሆኑም ተዘግቧል ። በሺህዎች የሚቆጠሩት ያልታጠቁ ሰዎች የተገደሉት ትናንት ጥቅምት 17 እና በዋዜማው እሑድ ዕለት እንደሆነም የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዛሬ ዘግቧል ። ከትናንትና ከእሑድ በፊትም ሥጋት እና ግድያው እንደነበር ደግሞ የሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ፎረሞች ኃላፊ ማሪያ ፔተር ተናግረዋል ።



«ኤል ፋሸር በRSF ተከብባ ከቆየች ከሁለት ዓመታት በላይ ሁኗል ። በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ነገሮች እንደገና ተባብሰዋል ። ቀደም ሲል ብርቱ ረሐብ ነበረ ። ከከተማዪቱ ለመውጣት የሚፈልጉ ተስፋ የቆረጡ ሰዎች ነበሩ ። እናም አሁን ጊዜው በቀረበ ቁጥር፣ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ምናልባትም በቅርቡ ወደ ከተማዪቱ እንደሚገባ ግልጽ ነው ። ያ ሁኔታውን ​​ይበልጥ ያባብሰዋል ። አንዳንድ ከከተማዪቱ ለመሸሽ የፈለጉ ሰዎች በጥይት ተመትተዋል ። በትክክል ከኋላቸው በጥይት ተመትተዋል ። ብዙዎች ታስረዋል ።»



ከቻድ በኩል በ200 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በዳርፉር ግዛት ውስጥ በምትገኘው ኤልፋሽር ከተማ በረሐብ ለተጎዱ ነዋሪዎቿ የሚላስ የሚቀመስ ከገባ ወራት ተቆጥሯል ። ከተማዪቱ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ሚሊሻዎች ለወራት ተከብባ ነዋሪዎቿም ከውጪው ዓለም ተነጥለው ቆይተው ነበር ።



የሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ተመድን አሳስቦታል



የሁኔታው መባባስ እጅግ ያሳሰባቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ ትናንት ሰኞ የማስጠንቀቂያ ደወል አሰምተዋል ። ነዋሪዎቿ በጠኔ እና በረሐብ በተጎዱባት ከተማ ሁኔታዎች «እጅግ በአሳሳቢ ሁኔታ እየተቀየሩ» መሄዳቸውን በመግለጥም አስጠንቅቀዋል ። ማሪያ ፔተርም ሥጋቱን ይጋራሉ ።



«ልክ ሌሎች ከተሞች ሲያዙ እንደነበረው ነው ሥጋታችን ። ዳርፉር ውስጥ በምትገኘው ኤል ዤኔና ከተማ ውስጥም ከሁለት ዓመት በፊት እንዲህ ያለ መሰል እጅግ አሳዛኝ ድርጊት ነበር ። በጅምላ መደፈር፣ በጅምላ በጥይት መደብደብ እና የረሐብ አደጋ ። እናም ለዚህ ነው ለምሳሌ ሠራዊቱ ከተማዋን ይዞ መቆየት የተሳነው ። ምክንያቱም ወታደሮቹ እንደማንኛውም ሰው እየተራቡ ነበር ። በሆነ ጊዜ ምግብ ካላገኘን ከተማዋን መከላከል አንችልም በማለት ከሁለት ሳምንት በፊት የጊዜ ገደብ አስቀምጠው ነበር ። በደቂቃዎች ልዩነት ውስጥ የሚደርሰን መልእክት እንደሚያመለክተው በከተማዪቱ በእየ ሰአቱ ሦስት ሕጻናት እየሞቱ እንደሆነ ነው ።»



አሁን የኤል ፋሽር ከተማ መያዝ ዳርፉር ውስጥ የሚገኙት አምስቱም ግዛቶች ዋና ከተሞች በአጠቃላይ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ቁጥጥር ስር መግባታቸውን ያረጋገጠ መሆኑን የፈረንሣይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል ። የሱዳን ጦር ሠራዊት በሰሜን፤ ምሥራቅ እና መአከላዊ ሱዳን እንዲወሰንም አስገድዶታል ። ያም ማለት ጦሩ ከሱዳን አጠቃላይ ግዛቶች አንድ ሦስተኛውን አጥቷል ማለት ነው ። «ይህ ሁኔታም» አሉ የተመድ ዋና ጸሐፊ፦ «ግጭቱ በከፋ ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን አመላካች ነው ።»



ዳርፉር፦ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይላት ግስጋሴ



የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ራሳቸውን ያደራጁት ጃንዳዊድ ከሚባሉት የአረብ ዝርያ ካላቸው ፈረሰኞች በመውጣት ነው ። እነዚህ ኃይላት ከሚሊኒየሙ መባቻ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ ነው ብቅ ያሉት ። አነሳሳቸውም በምዕራብ ዳርፉር የሚገኘውን የሱዳን ነፃ አውጪ ጦር (SLA) እና የፍትህ እና የእኩልነት ንቅናቄ (JEM)ን የመሳሰሉ ጥቁር አፍሪቃውያን አማፂያን ከምዕራብ ዳርፉር ወግቶ ማስወጣትን ዓላማቸው በማድረግ ነበር ። ያኔም ቢሆን ታዲያ፦ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ሚሊሻዎቹ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጭምር ከፍተኛ በደሎችን መፈጸማቸው የሚታወስ ነው ።



ማንተጋፍቶት ስለሺ/ኬርስተን ክኒፕ



ሸዋዬ ለገሠ

Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

ሱዳን ኤልፋሽር ከተማ «ከ2,000 በላይ ያልታጠቁ ሰዎች» ተገደሉ

ሱዳን ኤልፋሽር ከተማ «ከ2,000 በላይ ያልታጠቁ ሰዎች» ተገደሉ

ማንተጋፍቶት ስለሺ ሥዩም Mantegaftot Sileshi