በታንዛኒያ አወዛጋቢ ምርጫ ከተደረገ በኋላ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ተስፋፋ
Description
ታንዛኒያ ዉስጥ ትላንት ረቡዕ የተካሔደውን ምርጫ በመቃወም ዳር ኤ ሰላም ከተማ ከተደረገ ሰልፍ በኋላ ዛሬ በድጋሚ አደባባይ የወጡ ተቃዋሚዎችን ለመበተን ፖሊስ ጥይት እና አስለቃሽ ጭስ መተኮሱን ሬውተርስ ዘግቧል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች ትናንት የፕሬዝደንት ሳሚያ ሱሉሑ ሐሰን የምረጡኝ ዘመቻ ፖስተሮችን እየቀደዱ ተቃውሟቸውን ከገለጹ በኋላ የታንዛኒያ ፖሊስ በከተማዋ የሰዓት ዕላፊ ገደብ ደንግጎ ነበር።
በዳር ኤ ሰላም ታንኮችን ጨምሮ ከፍተኛ የጸጥታ አስከባሪዎች በአውራ ጎዳናዎች ቢሰማሩም “ሀገራችን እንድትመለስልን እንፈልጋለን” እያሉ የሚዘምሩ በአብዛኛው ወጣቶች የሚበዙባቸው ተቃዋሚዎች ትላንት ተቃውሞ ማሰማታቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። በዳር ኤ ሰላም ኔልሰን ማንዴላ ጎዳና የሚገኝ የፖሊስ ጣቢያ በተቃዋሚዎች እንደተቃጠለ ዘገባው ይጠቁማል።
ከምርጫው በኋላ ተቃውሞ ሲቀሰቀስ በመላ ታንዛኒያ የኢንተርኔት ግንኙነት መቆራረጡን አገልግሎቱን የሚከታተለው ኔትብሎክስ ይፋ አድርጓል። በታንዛኒያ ብሔራዊ የቴሌቭዥን ጣቢያ በኩል በመላ ሀገሪቱ የሰዓት ዕላፊ መጣሉን ያወጁት የፖሊስ አዛዥ ካሚሉስ ዋምቡራ ጦሩ እና የፖሊስ መኮንኖች በዳር ኤ ሰላም ጎዳናዎች ቁጥጥር እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
ቲቶ ማጎቲ የተባሉ የታንዛኒያ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ትላንት ረቡዕ ከምርጫ በኋላ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ አምስት ሰዎች መገደላቸውን ሪፖርት እንደተቀበሉ ለሬውተርስ ተናግረዋል። ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የዲፕሎማቲክ የመረጃ ምንጭ በበኩላቸው በዳር ኤ ሰላም ብቻ ቢያንስ አስር ሰዎች መገደላቸውን የሚጠቁም ጠንካራ ሪፖርት መቀበላቸውን ገልጸዋል።
የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከ-እና ወደ ዳር ኤ ሰላም የሚደረጉ የተወሰኑ ዓለም አቀፍ በረራዎች መቋረጣቸውን፤ በአሩሻ እና በኪሊማንጃሮ ከተሞች የሚገኙ አውሮፕላን ማረፊያዎች መዘጋታቸውን አስታውቋል። የታንዛኒያ መንግሥት ቃል አቀባይ ጌርሰን ምሲግዋ በአሠሪዎቻቸው ከሥራ ቦታቸው እንዲገኙ ከተነገራቸው የመንግሥት ተቀጣሪዎች ውጪ ያሉት ሥራቸውን ከቤታቸው እንዲያከናውኑ መልዕክት አስተላልፈዋል። ተማሪዎችም ከቤታቸው እንዲቆዩ ታዘዋል።
የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ አምስነቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ዳይሬክተር ቲገረ ቻጉታሕ አንድ ሰላማዊ ሰው እና አንድ ፖሊስ መገደላቸው ከተገለጸ በኋላ በታንዛኒያ እየተፈጠረ ያለው ነገር “የበለጠ ሊባባስ” እንደሚችል አስጠንቅቀው ነበር። ቲገረ ቻጉታሕ “ፖሊስ በተቃዋሚዎች ላይ አላስፈላጊ እና ከልክ ያለፈ ኃይል ከመጠቀም እንዲቆጠብ” አሳስበዋል።
በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የታንዛኒያ ካምፔይነር ዋንጅሩ ሙይታሐ “ትልቁ ሥጋታችን ከምርጫው በፊት በታንዛኒያ እየጨመረ የመጣው የሰብአዊ ቀውስ መባባስ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። “አሁን ያለው ሁኔታ በምርጫው ወቅት እና በኋላ እንዲሁ ሊቀጥል እንደሚችል ይታየናል” ያሉት የአምነስቲ ባልደረባ ከጥር 2024 ጀምሮ ተቋማቸው የታንዛኒያ መንግሥት “በገዛ ዜጎቹ ላይ የሚፈጽማቸውን ጥሰቶች በንቃት ሲሰንድ” እንደቆየ ገልጸዋል።
የታንዛኒያ መንግሥት “ዜጎች እና ጋዜጠኞችን ለማፈን ጨቋኝ እና ግልጽ ያልሆኑ ሕግጋትን በተለያየ መንገድ ሲጠቀም ነበር” ያሉት ዋንጅሩ ሙይታሕ “በእንዲህ አይነት የሰብአዊ መብቶች ቀውስ ውስጥ የታፈኑ ድምጾች፣ የተጨቆኑ ተቃዋሚዎች እና ውስን የሕዝብ ተሳትፎ እያየን ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ከሰባት ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ባሏት ዳር ኤ ሰላም እና ሌሎች ከተሞች ተቃውሞ የተቀሰቀሰው በታንዛኒያ አጠቃላይ ምርጫ ሁለት ትልልቅ ፓርቲዎች በመገለላቸው ምክንያት ነው። ዋናው ተቃዋሚ ፓርቲ ቻዴማ የፕሬዝደንት ሳሚያ ሱሉሑ ሐሰን “ንግሥና” ባለው ምርጫ ወቅት ተቃውሞ እንዲደረግ ጥሪ አስተላልፏል። የምርጫ ማሻሻያ እንዲረግ የፓርቲው መሪ ቱንዱ ሊሱ ጥሪ በማቅረባቸው ከታሰሩ እና በሀገር ክህደት ከተከሰሱ በኋላ ቻዴማ ራሱን ከምርጫው አግልሏል።
ጥምረት ለለውጥ እና ግልጽነት (ACT-Wazalendo) የተባለው ፓርቲ ፕሬዝደንታዊ እጩ ሉሐጋ ምፒና በታንዛኒያ ብሔራዊ የምርጫ ኮሚሽን ታግደዋል። በምርጫው ትናንሽ ፓርቲዎችን የሚወክሉ 16 ዕጩዎች ቢሳተፉም ያሸንፋሉ ተብሎ የሚጠበቁት ሳሚያ ሱሑሉን የመገዳደር አቅም እንደሌላቸው ይታመናል። የቻዴማ ፓርቲ ሊቀ መንበር ጆን ኪቶካ ምርጫው ሳሚያ ሱሉሑ ከራሳቸው ጋር የሚወዳደሩበት አድርገው በማቅረብ አጣጥለውታል።
የቻዴማ ፓርቲ ሊቀ-መንበር ጆን ኪቶካ “ገዥው ፓርቲ እና የሚመራው መንግሥት ምርጫ ብለው ይገልጹታል። ነገር ግን አብዛኛው ታንዛኒያዊ እንደዚያ አይመለከተውም” ሲሉ ተናግረዋል። የታንዛኒያ ሕዝብ ምርጫውን “ዴሞክራሲያዊ ሒደት ያለ ለማስመሰል የሚደረግ ትወና አድርገው ይቆጥሩታል። እውነቱም ይህ ነው” ያሉት ጆን ኪቶካ “ምርጫው የሚደረገው በሳሚያ እና በሱሑሉ መካከል ነው” በማለት አጣጥለዋል።
ትላንት የተካሔደው ምርጫ ሳሚያ ሱሑሉ ፕሬዝደንት ከሆኑ ወዲህ የመጀመሪያው ቢሆንም ፓርቲያቸው ቻማ ቻ ማፒንዱዚ ግን ታንዛኒያ በጎርጎሮሳዊው 1961 ከቅኝ ገዥዎች ነጻ ከወጣች ጀምሮ በሥልጣን ላይ ይገኛል። የታንዛኒያ የመጀመሪያ ሴት ፕሬዝደንት ለመሆን የበቁት ሱሑሉ ሥልጣን የያዙት የቀድሞው የሀገሪቱ መሪ ጆን ማጉፉሊ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ ነበር።

























