ጠ/ሚ ዐብይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ 7ተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለሥልጣን በዶቼቬለ ዘጋቢያዎች ላይ የጣለው ጊዜያዊ እገዳ
Description
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ፣ የኢትዮጵያ ርዕሰ-ብሔር ታዬ አጽቀስላሴ ለኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ጉባኤ ባደረጉት ንግግር ላይ የምክር ቤት አባላት ላነሷቸው ጥያቄዎች መልስና ማብራሪያ የሰጡት በዚህ ሳምንት ማክሰኞ ነበር ። ዐቢይ ማብራሪያ ከሰጡባቸው ጉዳዮች መካከል 7ተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ፣ የኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄ፣ከኤርትራ ጋር የተነሳው ውዝግብ የሀገሪቱ የውጭ እዳና የኤኮኖሚ ዕደገት ይገኙበታል። በዚሁ ገለጻቸው ዐቢይ "ኢትዮጵያ በዘንድሮው ዓመት ያላምንም ጥርጥር ባለሁለት አሃዝ እድገት ታስመዘግባለች።" ሲሉም ተናግረው ነበር
ዐቢይ ለምክር ቤት አባላት በሰጡት መልስና ገለጻ ላይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከተሰጡት አስተያየቶች ፣ ጽንፍ የያዙትና ዘለፋ የሚያመዝንባቸውን ወደጎን በመተው የተሻሉ የሚባሉትን ስንመለከት ፣ አዳሙ ውበቱ በፌስቡክ «ተስፋ ጥሩ ነው» ሲሉ አጭር አስተያየት ሰጥተዋል ።ፋልታሞ አስቴር መልካም ተመኝተዋል «መልካም ሀገራዊ አቅም ይሁንልን!» ሲሉ ማን ያሻግራት በሚል የፌስቡክ ስም የተሰጠ አስተያየት ግን «የኑሮ ውድነት እየጠበሰው ነው፣ በህልም ነው? ሲል ይጠይቃል።
ነጻነት ቡርቃ በፌስቡክ «ምን ይሳናችኋል ባለ አራት አሃዝ ማድረግ ትችላላችሁ Check የሚያደርግ ወይም የሚያጣራ በሌለበት ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። መርዕድ መቼነህ ግን« ትችላለች እንችላላለን ችለንም አሳይተናል።ጉዞ ወደ ፊት ብቻ »ብለዋል።
 ሲሳይ ተሰማ «በሕልምሽ ነው» ሲል ዮፍታኄ ኤልያስ ቶስካ «በእግዚአብሔር በመተማመን ነው» በማለት ለሲሳይ መልስ የሚመስምል አስተያየት ሰጥተዋል። ዳግም ዳታ የተባሉት የፌስቡክ ደንበኛ «በእናትህ አንተ ወደ ምትኖርበት ኢትዮጵያ ውሰደኝ» ሲሉ ተሳልቀዋል። 
«ፈቃድና አስቻይ ሁኔታዎች ባሉበት ክልል ሁሉ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫይደረጋል» ሲል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባለፈው ግንቦት መጨረሻ ላይ አስታውቋል። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዚህሳምንት ለምክር ቤት አባላት በሰጡት ገለፃም ፣ምርጫውን ለማከናወን መንግስት በቂ አቅምና ዝግጁነት እንዳለው፣ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ እስካሁን በኢትዮጵያ ከተካሄዱ ምርጫዎች ሁሉ የተሻለ እንደሚሆን ተናግረዋል።
ዳሞት ታደለ በፌስቡክ «ምርጫ? «ዜጎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅስው መኖር ባልቻሉበት ሁኔታ የት ላይ ልታረገው ነው ያስብከው? ሲሉ ጠይቀዋል። አቡ ፈውዙን ሂክ «የኛን ሀገር ምርጫ ፍትሀዊ ይሆናል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው» ሲሉ «ተሚ ወፊሌ ኢትዮጵያ ዉስጥ በምርጫ አሸንፎ ፣የመራ ፓርቲ ስለሌለ ገንዘብ በምርጫ ሰበብ ባይባከንስ? ብለዋል።
ዐቢይ ግን፣ በማክሰኞው የምክር ቤት ገለጻቸው «ምርጫው ዴሞክራሲያዊና ብዘሃ ድምጾች ያሉት እንዲሆን ፣በሃላፊነት እንሰራለን። እኛ እንደ ፓርቲም፤ እንደ መንግስትም ዝግጁ ነን። ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ከወዲሁ መዘጋጀት አለባቸው።» ሲሉ አሳስበዋል።
ባለፈው ሐሙስ ነበር የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለሥልጣን ከኢትዮጵያ ለዶቼቬለ የሚዘግቡ 9 ባልደረቦችን ፈቃድ ማገዱን ያሳወቀው። ዶቼቬለ ከመቀሌ፣ ባሕርዳር፣ ደሴ፣ አዲስ አበባ፣ ሐዋሳ፣ ድሬዳዋና አሶሳ ለዶቼቬለ በሚዘግቡ ወኪሎቹ አማካይነት መረጃዎችን በማሰባሰብ ገለልተኛ፣ ሚዛናዊና ትክክለኛ ዘገባዎችን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያሰራጫል። ይሁንና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ባለፈው ሳምንት ሐሙስ በላከው ደብዳቤዉ ዶቼ ቬለና ወኪሎቹን የኢትዮጵያን ሕግና ደንብ ጥሰዋል፣ ሙያዊ ሥነ-ምግባርን አያከብሩም በማለት ወቅሶ ነው የዶቸ ቬለ ዘጋቢዎችን የሥራ ፈቃድ ለጊዜዉ ማገዱን ያሳወቀው ። ዶቼቬለ ለኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን በሰጠው መልስ 9 ዘጋቢዎቹን ማገዱን በመቃወም ፤ ባለሥልጣናቱ በዘጋቢዎቹ ላይ የተጣለውን እገዳ በአስቸኳይ እንዲያነሱ ጥሪ አቅረቧል ።
የዶቼቬለ ዋና ስራ አስኪያጅ ባርባራ ሜሲንግ ባወጡት መግለጫ ዶቼ ቬለ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ነጻ መረጃ ለማግኘት የሚተማመኑበት ጣቢያ መሆኑን ጠቁመዉ  የታገዱት ባልደረቦች ካለምንም ገደብ በአስቸኳይ ተመልሰው ስራቸውን መቀጠል ይችላሉ ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።  ይሁንና ዶቼቬለ ላቀረበው የእገዳው ይነሳ ጥሪ ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን እስካሁን በይፋ የተሰጠ መልስ የለም።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለሥልጣን በኢትዮጵያ የዶቼ ቬለ ዘጋቢዎች ላይ ስለጣለው ጊዜያዊ እገዳ በፌስቡክ ከተሰጡት አስተያቶች አንዱ « የባህር ዳር የትግራይ (መቀሌ) የአዲስአበባ። ወኪሎች ወይም ሪፖርተሮች ስለታገዱ የሀገራችንን የህዝባችንን ያሉበትን ሁኔታ እነዳናውቅ ተደረገ ማለት ነው። (አ ፈ ና) ማለት ይሄ ነው። የህዝብ ድምፅ በታፈነ ቁጥር አመፅ ይበረታል» ይላል።
«በትግራይ ጦርነት ጊዜ እናንተን ብቻ ነበር የምን ጠብቀው። የሁሉም ሚዲያ ሰለጦርነት በሚያራግብበት ጊዜ እናንተ ግን ሰው ሆናችው ተገኝታችሁልን ነበር። በውነት ዉለታችሁንን እግዜር ይመልሰው አሁንም ቢሆን እንዲቋረጥብን አንፈልግም።» የሚለው ደግሞ የሄለን ማዞሪያ አስተያየት ነው
ሴፉስ ሲ «ለምን ዶቼቬለ ጋዜጠኛዎቹን ለጊዜው ከኬንያ ናይሮቢ ሆነው እንዲዘግቡ ማድረግ አልቻለም ነጋሽ? ሲሉ ጠይቀዋል። በላይ ሀብቱ ደግሞ «በርቱ ተበራቱ» ብለውናል
ሳላድሂን አዩብ «መንግስት የ DW አማርኛ ቋንቋ ጋዜጠኞች ኢትዮጵያ ውሰጥ ተዘዋውረው ዜናዎችን እና ሪፖርቶችን እንዳይሰሩ ማገዱ የስርአቱን አፋኝነት ያጋለጠ ማሳያ ነው።» ሲሉ ስዩም ገብረ መስቀል« በአግባቡና በሕጉ መሠረት የማትሰሩ ከሆነ መባረራቸው የግድ ፤ምክንያቱም ሁሉም ነገር ሚኖረው ሀገር ስኖር ብቻ ነዉ።» ብለዋል። የያዕቆብ ወታንጎ አስተያየት «አውነት የሚያወራውን ሰው፣ ሰው አይወድም፤ እውናት ስለምትዘግቡ ነው፤ እኛ ግን FB እንከታተላለን ይላል።
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ 
 

























