የዩናይትድ ስቴትስና ቻይና  ስምምነት «እመርታ»
Description
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ከቻይና አቻቸው ሺ ጂፒንግ ጋር በቀረጥ እና ምድር ላይ እጅግ ውስን በሆኑ ማለትም (ሬር ኧርዝ) ማዕድናት ላይ አመርቂ ስምምነት ማድረጋቸውን ገለጡ ። ደቡብ ኮሪያ ቡሳን ውስጥ የተደረገውን ስምምነት ፕሬዚደንቱ «ጥሩ እመርታ የታየበት» ሲሉ አወድሰዋል ። በስምምነቱ መሰረት ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ቻይና ላይ ጥለውት የነበረዉን ከፍተኛ ቀረጥ ሊከልሱ መሆናቸውንም ሮይተርስ የዜና ምንጭ ዛሬ ዘግቧል።
አበበ ሁለቱ አገራት በ«አራት ጉዳዮች ላይ» መስማማታቸውን አብራርቷል ። አንደኛው እና ዋነኛው «በቻይናእና በሌሎች አገራት ላይ አወዛጋቢ የነበረው የቀረጥ ጉዳይ» መሆኑን ጠቅሷል ።
ቻይና በበኩሏ እንደ ቦሎቄ፣ አኩሪ አተር፤ ማሽላ የመሳሰሉ የግብርና ምርቶችን ከዩናይትድ ስቴት ገዝታ ወደ አገሯ ለማስገባት መስማማቷ ተዘግቧል ። ከስምምነቶቹ መካከል ፤ ቻይና ፌንቴኒል የሚባለው የኅመም ማስታገሻ ግን ደግሞ እጅግ ሱስ አስያዥ ንጥር ላይ ቁጥጥር ማድረግ እንዳለባትም ተስማምተዋል ተብሏል ።
ቻይና ብራዚል፣ ሩስያ፣ ሕንድ እና ደቡብ አፍሪቃ በጋራ በመሆን አምስቱ አገራት የመሰረቱት «ብሪክስ» የተባለው ቡድን ዋና አባል መስራች ናት ። ከዚህ አንጻር ቻይና ከዩናይትድ ስቴትስ እና ከብሪክስ ጋር ያላትን ጥቅም አጣጥማ ለማስኬድ ምናልባትም ተግዳሮት ሊገጥማት እንደሚችል አበበ ጠቁሟል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አበበ ፈለቀ
ሸዋዬ ለገሠ

























