ኢዜማ፤ የብልፅግና ፓርቲ ያደርጋል ያለውን የግዳጅ የአባላት ምልመላን አወገዘ
Description
የብልፅግና ፓርቲ የግዳጅ የፓርቲ አባላት ምልመላ ነፃ እና ፍትሃዊ የፖለቲካ ውድድርን የሚያጠብ እና ዜጎችን ስጋት ላይ የሚጥል ነው ፤ ሲል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፤ ኢዜማ ገለፀ። ፓርቲው አያይዞምየገዢው ፓርቲ ርምጃ የዜጎችን በነፃ የመደራጀት መብት የሚገፍ ነው ብሏል።
የመንግሥት ሠራተኞችን በግዴታ የብልጽግና ፓርቲ አባል የማድረግ ተግባር በአስቸኳይ ይቁም በሚል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ በዚህ ሳምንት ያወጣውን መግለጫ በተመለከተ ዶቼቬለ ያነጋገራቸው የፓርቲው ምክትል መሪ አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን እንደገለፁት ኢትዮጵያ በምትገዛበት የፌደራሉ መንግሥትም ሆነ በተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ዜጎች ባመኑበት የፖለቲካ አስተሳሰብ በነፃ የመደራጀት መብት አላቸው። ይሄ መብታቸው በነፃነት ያለገደብ እና የለአስገዳጅነት የሚፈጽሙት እንጅ ለተለዬ የፖለቲካ ዓላማ መሆን የለባትም ብለዋል። ይህ ችግር በኢትዮጵያ ስር የሰደደ እና ዘመናትን የተሻገረ ነው ያሉት ምክትል መሪው፤ ዜጎች የፓርቲውን አቋም ተቀብለው አባል ቢሆኑ መብታቸው በመሆኑ ይህንን ፓርቲው እንደሚቀበል አመልክተዋል። ነገር ግን በግዳጅ የፓርቲው አባላት ማድረግ ዜጎችን ስጋት ላይ የሚጥል እና ፓርቲው የሚያስበውን ነፃ እና ፍትሃዊ የፖለቲካ ውድድር የሚያጠብ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
ችግሩን በዳሰሳ ጥናት እና በአንዳንድ አቤቱታዎች ፓርቲው ማረጋገጡን የገለፁት ኃላፊው፤ ይህ መሰሉ አባላትን በአስገዳጅ የመመልመል ሁኔታ የዜጎችን መብት የሚጋፋ እና የዲሞክራሲ ምህዳሩን የሚያጠብ ብቻ ሳይሆን፤ «እንደ ሀገር ከመጣንበት ብዙ ርቀት ወደ ኋላ የሚመልስ» ነውም ብለዋል።
ገዥው ፓርቲ ከሀገሪቱ ዜጎች አንድ አስረኛ የሚሆኑ አባላት አሉኝ ይላል የሚሉት አቶ ዮሐንስ ይህ የገዢው ፓርቲ ጠቅልሎ የመያዝ ሁኔታ በመጭው ምርጫ ላይ ተፅዕኖ እንዳለው ገልፀዋል። ከዚህ ባሻገር ሥራ አጥ ወጣቶችን ሴቶች እና አካል ጉዳተኞችን ተጎጂ ያደርጋልም ብለዋል።
መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሠራተኞችን ያለፍላጎታቸውበተለያዩ ተጽዕኖዎች አባል እንዲሆኑ ጫና እያሣደረ መሆኑን በገለፀበት የሰሞኑ የኢዜማ መግለጫ፤ በገዢው ፓርቲ ቅቡልነት ላይም ጥያቄ አንስቷል። ድርጊቱ የመንግሥት ኃላፊነት የተሠጣቸው የፓርቲው አመራሮች ሥልጣንን ያለአግባብ እንደሚጠቀሙ ያሳያል ብሏል። ጉዳዩንም የመገናኛ ብዙኀን ለማኅበረሰቡ እንዲያጋልጡ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እንዲያወግዙት፣ የሲቪክ ማኅበራት ደግሞ በጉዳዩን ላይ ግንዛቤ እንዲፈጥሩ ሲል ሰሞኑን ባሰራጨው መግለጫ ጥሪ አቅርቧል።
ኢዜማ ጠንከር ያለ ተቃውሞ በመንግሥት ላይ አያቀርብም በሚል ይተቻል ሲል ዶቼ ቬለ ላቀረበላቸው ጥያቄም፤ ፓርቲው ፅንፍ ሳይዝ በጥናት ላይ የተመሰረተ አካሄድ አለው ብለዋል። ትችቱ የፓርቲውን አካሄድ ካለመረዳት የመጣ ነው ያሉት የፓርቲው ምክትል መሪ፣ «ሁሉን ነገር ጠቅልለን አናመሰግንም ሁሉን ነገር ጠቅልለን አንወቅስም» የሚል ምላሽም ሰጥተዋል።
በጉዳዩ ላይ ከብልፅግና ፓርቲ ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ፀሐይ ጫኔ
ሽዋዬ ለገሠ






















