ኢትዮጵያ ውስጥ የተጠለሉ ስደተኞች የረሃብ አደጋ ተጋርጦባቸዋል ተባለ
Description
የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ መርሐ ግብር (WFP) አሳሳቢ ባለው የገንዘብ እጥረት ምክንያት የምግብ አቅርቦትን በመቀነሱ ኢትዮጵያ ውስጥ የተጠለሉ ስደተኞች "የረሃብ አደጋ ተጋርጦባቸዋል" ሲል ገለፀ።
ድርጅቱ በዚህ ወር በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ 27 ካምፖች ውስጥ ለሚገኙ 780,000 ስደተኞች ያቀርብ የነበረውን 60 በመቶ የሰብአዊ የምግብ ድጋፍ ወይም ራሽን ወደ 40 በመቶ ለመቀነስ መገደዱን ገልጿል።
በሚቀጥሉት ስድስት ወራት የሰብአዊ ስራዎችን ለማስቀጠል አስቸኳይ 230 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ያስፈልገኛል ያለው ድርጅቱ፣ ይህ ድጋፍ በአፋጣኝ ካልተገኘ "በሚቀጥሉት ወራት በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች በሙሉ የሚሰጠውን የምግብ እርዳታ ሙሉ በሙሉ ለማቆም ሊገደድ እንደሚችል" አስታውቋል።
ችግሩ መፍትሔ ካላገኘ "የስደተኞችን ሕይወት አደጋ ላይ ይጥላል"
የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ መርሐ ግብር አሳሳቢ የገንዘብ እጥረት ውስጥ በመሆኑ በኢትዮጵያ ለተጠለሉ የተለያዩ ሀገራት ስደተኞች የሚያቀርበውን የምግብ አቅርቦት መቀነሱንና በዚህም ሳቢያ "የረሃብ አደጋ ተጋርጦባቸዋል" ሲል አስታውቋል።
እያንዳንዱ ተረጂ አሁን በቀን ከ1,000 ካሎሪ በታች የሆነ የምግብ እርዳታ ይቀበላል ያለው ድርጅቱ አሁን ባለው ሀብት ከጎረቤት ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ግጭት ሸሽተው ወደ ኢትዮጵያ የመጡ 70,000 አዲስ ስደተኞች ብቻ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ሙሉ የምግብ ድጋፍ የሚያገኙ ይሆናል ብሏል።
የድርጅቱ የኢትዮጵያ ተወካይ ዝላታን ሚሊሲች “በተቻለ መጠን ለብዙ ስደተኞች የምግብ እርዳታ ለማግኘት እየሞከርን ነው፣ ነገር ግን ተጨማሪ ገንዘብ ካልተገኘ ሁኔታው የምንረዳቸውን ሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ ይጥላል" ብለዋል። እየተቀነሰ ያለው የእርዳታ መጠን ከልጆች ጉሮሮ ላይ መሆኑን ገልፀውም አስጠንቅቀዋል።
ኃላፊው ለዶቼ ቬለ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ "ሁላችንም እንደምናውቀው የዓለም የሰብአዊ የገንዘብ ድጋፍ ሁኔታ በዚህ ዓመት በትክክል የማይገመት እና ያልተረጋጋ፣ በርግጥም ኢትዮጵያን ጨምሮ ብዙ ሀገራትን ለችግር ያጋለጠ ነው"ብለዋል። እንዲያም ሆኖ ጉድለቱን ለማስተካከል ብርቱ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ጠቅሰዋል።
"አሁን ግን የገንዘብ ድጋፋችን እያሽቆለቆለ የሚገኝበት ሁኔታ ላይ ደርሰናል። እናም በቅርቡ አዲስ የገንዘብ ድጋፍ እንደምናገኝ ምንም አይነት የተለየ ምልክት የለንም። የገንዘብ ድጋፉ ባለፉት በርካታ ዓመታት እንዳደረግነው በተለይም ይህን ዓመት ጨምሮ በአንዳንድ ችግሮች ለተጎዱ ሕፃናት [ርዳታችንን] እንድንቀጥል አይፈቅድልንም።" ብለዋል።
በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ሥራዎችን ለማስቀጠል 230 ሚሊየን ዶላር ያስፈልጋል
የዓለም የምግብ መርሐ ግብር ያወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ "በሚቀጥሉት ስድስት ወራት የሰብአዊ ስራዎችን ለማስቀጠል 230 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በአስቸኳይ እንደሚያስፈገው ይጠቅሳል። ሆኖም አፋጣኝ አዲስ የገንዘብ ድጋፍ የማይገኝ ከሆነ በሚቀጥሉት ወራት "በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች በሙሉ የሚሰጠውን የምግብ እርዳታ ሙሉ በሙሉ ለማቆም ሊገደድ ይችላልም" ብሏል።
በምግብ እጥረት ለተጎዱ ሕጻናት እና እናቶች የሚቀርበው የድርጅቱ ልዩ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትም "በአደገኛ ሁኔታ እያሽቆለቆለ መሆኑን" ጭምር በመግለጽ።
ይህም ድርጅቱ የተመጣጠነ የምግብ እጥረት ላለባቸው ሕፃናት እና ነፍሰ ጡር ሴቶች እንዲሁም ጡት ለሚያጠቡ እናቶች የሚያደርገው ወሳኝ ድጋፍ እንዲያበቃ ያደርጋል ተብሏል።
"በእርግጥ ክምችታችን ሙሉ በሙሉ ካበቃ፣ በአሁኑ ወቅት ለመርዳት እየሞከርን ካለው 870,000 ሰዎች መካከል 90 በመቶ ያህሉን ለስደተኞች የምንሰጠውን እርዳታ ማቆም ሊኖርብን ይችላል።"
የስደተኞች ተቀባይ የሆነችው ኢትዮጵያ ምን አለች
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር የሚገኘው የዓለም ምግብ መርሐ ግብር ያለውን ውስን የሰብአዊ ምግብ አቅርቦት ለማስፋፋት እየሰራ መሆኑን ጠቅሶ ችግሩ መፍትሔ ካላገኘ ግን ለአዳዲስ የፍልሰት ሰለባዎች፣ የድርቅ ወይም ሌሎች የአየር ንብረት አደጋዎች ሊያስከትሉ ለሚችሉት አዳዲስ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት የሚደረገውን ዝግጅት የሚጎዳ ነው ተብሏል።
ሰምኑን በተካሄደው 76ኛው የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬከተር ጠይባ ሀሰን የችግሩን አሳሳቢነት አዲስ አበባን ጨምሮ በ8 ክልሎች የሚገኙ ስደተኞችን ለችግር የሚዳርግ መሆኑን ገልፀዋል።
"ዘንድሮ - 2025 በጣም አስቸጋሪ [ዓመት] ነው። የሰብአዊ ፍላጎቶች በፍጥነት እያደጉ ባሉበት በዚህ ወቅት የአለም አቀፍ የገንዘብ ድጋፍ ወደ አሳሳቢ ደረጃ ሲወርድ አይተናል። በሀብቶች እና ፍላጎቶች መካከል ያለው አለመጣጣም በየቀኑ እየጨመረ ነው። ያየናቸው [የድጋፍ] ቅነሳዎች ዘላቂ መፍትሔዎችን ለማምጣት ለውጦችን ከመገደቡ ባለፈ ባለፉት ዓመታት የተገኙትን ጠቃሚ ግኝቶች እንዳይቀለብስ ያሰጋል።"
የአማራ ክልል ቀውስ የሰብአዊ ቀውሱን አባብሷል
በድንገተኛ አደጋዎች ለተጎዱ ሰዎች ሕይወትን በማዳን እና የምግብ ርዳታን በመጠቀም ከግጭት፣ ከአደጋ እና ከአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖ የሚያገግሙ ሰዎችን የሰላም፣ የመረጋጋት እና የመሻሻል መንገድ ለመገንባት በዓለም ትልቁ የሰብአዊ ድርጅት የሆነው የተባበሩት መንግሥታት የምግብ መርሐ ግብር ከገንዘብ እጥረት በተጨማሪ በተለይ በአማራ ክልል እየተከሰተ ያለው ቀውስ የሰብዓዊ እንቅስቃሴውን ማስተጓጎሉን ቀጥሏል ሲል ድርጅቱ አስታውቋል።
ሰለሞን ሙጬ
እሸቴ በቀለ