DiscoverDW | Amharic - Newsፍልስጤማውያን ወደ ፈራረሱ መኖሪያ ቤቶቻቸው መመለስ ጀመሩ
ፍልስጤማውያን ወደ ፈራረሱ መኖሪያ ቤቶቻቸው መመለስ ጀመሩ

ፍልስጤማውያን ወደ ፈራረሱ መኖሪያ ቤቶቻቸው መመለስ ጀመሩ

Update: 2025-10-11
Share

Description

እስራኤል እና ሐማስ የደረሱበት የተኩስ አቁም ተግባራዊ መሆን ሲጀምር ዛሬ ቅዳሜ በአስር ሺሕዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ወደ ፈራረሱ መኖሪያ ቤቶቻቸው መመለስ ጀመሩ። ከሜድትራኒያን የባሕር ዳርቻ በሚገኘው አውራ ጎዳና በርካታ ሰዎች በእግራቸው ወደ ሰሜናዊ ጋዛ ሲተሙ መታየታቸውን ሬውተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።



በጋዛ ሠርጥ ትልቋ የፍልስጤማውያን መኖሪያ የሆነችው የጋዛ ከተማ እስከ ትላንት አርብ ድረስ የእስራኤል ጦር ሠራዊት የሚወስደው ወታደራዊ እርምጃ ዒላማ ከነበሩ መካከል ነች። የጋዛ ሲቪል ሰዎች መከላከያ ቃል አቀባይ ማሕሙድ ባሳል 200,00 ገደማ ፍልስጤማውያን የተኩስ አቁሙ ተግባራዊ ከሆነ ወዲህ ወደ ሰሜናዊ ጋዛ መመለሳቸውን ገልጸዋል።



በጋዛ ከተማ ሼይክ ራድዋን የተባለ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ኢስማኢል ዛይዳ “ፈጣሪ ይመስገን ቤቴ እንደቆመ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። “ነገር ግን አካባቢው ወድሟል። የጎረቤቶቼ ቤቶች ፈራርሰዋል። አጠቃላይ መንደሩ የለም” ሲሉ ከተፈናቀሉበት ሲመለሱ የጠበቃቸውን አስረድተዋል።



ማሐዲ ሳቅላ የተባሉ ሌላ ፍልስጤማዊ እስራኤል እና ሐማስ የተኩስ አቁም ላይ መድረሳቸው እንደተሰማ ቤተሰቦቻቸው ወደ ጋዛ ከተማ ለመመለስ እንደወሰኑ ገልጸዋል። “ምንም ቤት የለም። ወድመዋል” ያሉት ማሐዲ “ነገር ግን ፍርስራሹም ላይ ቢሆን ቤታችን ወደነበረበት በመመለሳችን ደስ ብሎናል። ያ ታላቅ ደስታ ነው። ለሁለት ዓመታት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ እየተፈናቀልን ሥቃይ ነበር” ብለዋል።



የጋዛ ትልቋ ሁለተኛ ከተማ በነበረችው በደቡባዊ ኻን ዩኒስ የእስራኤል ጦር ከተወሰኑ አካባቢዎች ከወጣ በኋላ ፍልስጤማውያን ሲመለሱ መኖሪያ ቤቶቻቸው በነበሩባቸው ቦታዎች ውድመት እና ፍርስራሽ እንደጠበቃቸው አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።



የዜና ወኪሉ ያነጋገራቸው ፋጢማ ራድዋን “ምንም የተረፈ ነገር የለም፤ ጥቂት ልብሶች፣ እንጨት እና ድስት ብቻ” ሲሉ አስረድተዋል።



አሕመድ አል ባሪም የተባሉ ሌላ የኻን ዩኒስ ነዋሪ ከመኖሪያ ቤታቸው ፍርስራሽ ውስጥ ያገኙት ምግብ ለማብሰል ማገዶ የሚሆናቸው እንጨት ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል። “ወደ አካባቢያችን ሔደን ነበር። ሙሉ በሙሉ ወድሟል። ከዚያ በኋላ ወዴት እንደምንሔድ አናውቅም” ሲሉ ተናግረዋል።



አሕመድ አል ባሪም “የቤት ዕቃዎችን ወይም ልብሶችን ወይም ምንም ነገር ማግኘት አልቻልንም። የክረምት ልብስ እንኳ ምንም የቀረ ነገር የለም” ብለዋል።



ፍልስጤማውያን ወደ ወደሙ መኖሪያ ቤቶቻቸው መመለስ የጀመሩት በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ሥምምነት ሁለተኛ ቀኑን ሲይዝ ነው። በተኩስ አቁም ሥምምነቱ መሠረት ሐማስ በሕይወት ያሉ 20 እስራኤላውያን ታጋቾች እስከ ሰኞ ዕኩለ ቀን መልቀቅ አለበት።



የአሜሪካው ፕሬዝዳን ዶናልድ ትራምፕ ሐማስ እስራኤላውያን ታጋቾችን እያሰባሰበ እንደሚገኝ እና የተኩስ አቁም ሥምምነቱ እንደሚጸና ገልጸዋል።



እስራኤል ባለፉት ሁለት ዓመታት ከጋዛ ተይዘው ክስ ሳይመሰረትባቸው እስር ቤት የሚገኙ 1,700 ሰዎች እና ተፈርዶባቸው እስር ቤት የሚገኙ 250 ፍልስጤማውያን ትለቃለች።



በአሜሪካ “የሰላም ዕቅድ” ተግባራዊ በሆነው የተኩስ አቁም መሠረት ግብጽ በጋዛ ጉዳይ ላይ የሚመክር ዓለም አቀፍ ጉባኤ የማዘጋጀት ውጥን አላት። ከቀይ ባሕር ዳርቻ በምትገኘው ሻርም አል ሼይክ የሚካሔደውን ጉባኤ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እና የግብጽ አቻቸው አብደል ፋታኅ አል-ሲሲ እንደሚመሩት የግብጽ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር በድር አብደል አቲ ዛሬ ቅዳሜ አስታውቀዋል።



ጉባኤው የሚካሔድበት ቀን ይፋ ባይደረግም በርካታ የአውሮፓ እና የአረብ ሀገራት መሪዎች እንዲገኙ ተጋብዘዋል። የግብጽ ፕሬዝደንት ፣ የጀርመን መራኄ መንግሥት ፍሬድሪሽ ሜርስ የጋዛ ሥምምነት ሲፈረም እንዲገኙ መጋበዛቸውን የጀርመን ዜና አገልግሎት ዘግበዋል። የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እስራኤልን ከጎበኙ በኋላ ሥምምነቱ ሲፈረም ወደ ግብጽ የማቅናት ፍላጎት እንዳላቸው ፍንጭ ሰጥተዋል።

Comments 
In Channel
loading
00:00
00:00
x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

ፍልስጤማውያን ወደ ፈራረሱ መኖሪያ ቤቶቻቸው መመለስ ጀመሩ

ፍልስጤማውያን ወደ ፈራረሱ መኖሪያ ቤቶቻቸው መመለስ ጀመሩ

Eshete Bekele