ሀገራዊ ፖሊሲዎች ሲወጡ ወጣቶች ያላቸው ድርሻ
Description
መቀመጫውን ናይሮቢ ኬንያ ያደረገውና ለትርፍ ያልተቋቋመው የአፍሪካ የማኅበራዊ እና የአስተዳደር ጥናት ትብብር የተባለው ድርጅት ኢትዮጵያን ጨምሮ በአሥር የአፍሪካ አገሮች የሚከናወን ወጣቶች ላይ ያተኮረ አንድ ጥናት ጀምሯል። ወጣቶች በሚወጡ ሀገራዊ ፖሊሲዎች ምን ያህል ባለቤትነት እና ድርሻ ያላቸው ናቸው? የሚለውን የሚዳስሰው ይህ ጥናት ወጣት የአካል ጉዳተኞች፣ ወጣት ተፈናቃዮች እና ፍልሰተኞች ፍላጎቶቻቸው በሚወጡ ፖሊሲዎች እና የሥራ አቅጣጫዎች ላይ እንዴት መካተት እንዳለባቸው፣ ችግሮቻቸው ምን እንደሆኑ ሊያመላክት የሚችል የተባለለት የሁለት ዓመት ተኩል ጥናት ነው ያስጀመረው። ጥናቱ ከሚደረግባችው ሃገራት አንዷ ኢትዮጵያ ስትሆን የዚሁ ሥራ መክፈቻ አውደ ጥናት ከሳምንታት በፊት አዲስ አበባ ውስጥ ተከናውኗል። ስለ ጥናቱ መነሻ፣ አስፈላጊነት እና የሚጠበቀው ውጤት የጥናት ቡድኑ የኢትዮጵያ ባልደረባ የሆኑ ሁለት ወጣቶችን ጠይቀናል።
ጥናቱ ወጣቶችን በተጨባጭ የሚያሳትፍ ነው
የአፍሪካ ማኅበራዊና አስተዳደር ጥናትና ምርምር አጋርነት የተባለው ናይሮቢ ውስጥ ሆኖ በዋናነት ምርምር ላይ የሚሠራው ድርጅት አሁን በአሥር የአፍሪካ ሃገራት ያስጀመረው ጥናት ወይም ምርምር ተመራማሪዎችን፣ ፖሊሲ አውጭዎችን እና የወጣቶች መሪዎችን በማሰባሰብ ለወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ እና መቋቋም አዲስ አጀንዳ ለመፍጠር ያስችላል ተብሎለታል። አፍሪካ «በአሁኑ ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች በተለይም የተገለሉ ማኅበረሰቦች ማለትም ስደተኞች፣ የተፈናቀሉ ግለሰቦች፣ አካል ጉዳተኞች፣ የገጠር ወጣት ሴቶች እና መደበኛ ባልሆነ ዘርፍ የተሰማሩ ሰዎች፣ ከሥራ እድሎች የተገለሉ ወጣቶች ባሉበት የወጣቶች የሥራ እጦት ቀዉስ ውስጥ ትገኛለች» የሚለው የድርጅቱ የጥናት መግለጫ ሰነድ ይህ መገለል የሰው ሀብት አቅም እንዲቀንስ፣ ማኅበራዊ አለመረጋጋት እና የኢኮኖሚ አቅም ማጣት እንዲከሰት ምክንያት መሆኑን ይጠቁማል።
የአምላክ ሥራ በጋሻው ኢትዮጵያ ላይ የሚደረገው የጥናት ቡድን አባል ወይም ባልደረባ ናት። የሚያከናውኑት ምርምር ወጣቶች መረጃ ሰጪ ብቻ ሳይሆኑ ጉልህ ተሳትፎ የሚያደርጉበት መሆኑን ለዶቼ ቬለ ትገልጻለች።
«ወጣቶች ሥራ አለማግኘታቸውን የሚዳስስ እና ለምን ይህ እንደሆነ የገደበውን ነገር ፖሊሲ ሊሆን ይችላል፣ መዋቅር ሊሆን ይችላል ያንን ለማጥናት ነው።»
የጥናት ቡድኑ አባል የአምላክ ሥራ እንደምትለው ወጣት ሆነው በልዩ ልዩ ችግር ውስጥ የሚገኙት ሰዎች ብዙ ጊዜ በሚወጡ ፖሊሲዎች ላይ የተገለሉ ናቸው።
«ከጥናቱ የምናገኘው ውጤት ፖሊሲ ላይ ጫና እንዲያደርግ፣ ለወጣቶች የተሻለ የሥራ ዕድል እንዲፈጥር እንዲሁም ከዚህ በፊት ያልታዩት የወጣት ክፍሎች ፖሊሲ ሲወጣ አይታዩም፣ ልዩ ሕግ አይወጣላቸውም።»
ጥናቱ የሚያተኩርባቸው ጉድለቶች ወይም ችግሮች ምንድን ናቸው?
ኢትዮጵያን ጨምሮ በኬንያ፣ በዩጋንዳ፣ በርዋንዳ፣ በናይጄሪያ፣ በጋና፣ በቶጎ፣ በቤኒን፣ በሴኔጋል እና በኮትዲቮር እንደየ ሃገራቱ ነባራዊ ሁኔታ ግን በተመሳሳይ የምርምር ስልት የሚደረገው ይህ ጥናት ዓላማው «የወጣቶችን ድምጽ ማጉላት፣ የአኗኗር ልምዳቸውን ግንዛቤ ማሳደግ እና የተከበረ ኑሮን የሚያመቻቹ መፍትሔዎችን በጋራ መንደፍ» ላይ ያተኮረ ነው። መረጃዎችን ከመሰብሰብ ባለፈ ወጣቶች ለውጥን እንዲመሩ በማብቃት ላይም ያተኩራል ተብሏል። ሌላኛዋ የኢትዮጵያ የጥናቱ ቡድን ባልደረባ የሆነችው ቤዛዊት ዕድሉ የድርጅቱ የጥናት መነሻዎች ከዚህ በፊት ያልተካተቱ ሁለት የተለዩ ክፍተቶችን ለመሙላት መሆኑን ትገልጻለች።
የሁለት ዓመት ተኩል የጥናት ጊዜ የተያዘለት ይህ ምርምር በጎርጊዮሳዊው ዓመት በ2027 መጨረሻ አካባቢ ይጠናቀቃል ተብሏል። ወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል የሚፈልገው ምንድን ነው ለሚለው የተሟላ ምላሽ መስጠት ከሚጠበቁ ውጤቶች አንዱ መሆኑንም ቤዛዊት ዕድሉ ጠቅሳለች። ይህ ሰፊ የጥናት ሥራ ወጣቶችን አሳትፎ ችግሮቻቸውን በመለየት የፖሊሲ ግብዓት እንዲሆኑ ከማገዝ ባለፈ በጥናቱ ላይ የሚሳተፉ ወጣት የምርምር ባለሙያዎችንም የማበረትታትና የማብቃት ተጨማሪ ዓላማም አለው። ያምላክ ሥራ በጋሻው እንደምትለው በዓለም አቀፍ መስፈርት ወጣት ተመራማሪ የሚባሉት ዕድሜያቸው ከ15- 35 ያሉትን የሚያቅፍ ነው። በዚህ ጥናት ተባባሪ ተብለው የተቀጠሩት ታዲያ ከጥናት ሥራቸው ባለፈ እነሱም የሚበረታቱበት ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ በሚከናወነው የመጀመርያ አውደ ጥናት ምን ምን የወጣት ችግሮች ተለዩ?
ኢትዮጵያ ውስጥ የሚከናወነው ጥናት አዲስ አበባ ውስጥ ወጣቶችን የሚመለከት ዘርፍ ላይ የሚሠሩ የመንግሥት ተቋማት ተወካዮች፣ ተማሪዎች፣ ወጣት ነጋዴዎች፣ ተፈናቃዮች እና ሌሎችም በተገኙበት ተጀምሯል። በዚህ ወቅት ጥናቱን ለማዳበር የሚረዱ ምን ግብአቶች ተገኙ የሚለውን የጠየቅናቸው ያምላክ ሥራ እና ቤዛዊት ተከታዩን ማብራሪያ ሰጥተታል።
«ለምሳሌ ዩኒቨርሲቲዎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ነን ቢሉም እንደዚያ አይደለም። መፀዳጃ ቤት የተሟላ አይደለም በጥናቱ ይህንን በጥልቀት እንዳስሰዋለን። ብዙ የ12ኛ ክፍል ተማሪ እያለፈ አይደለም። ስለዚህ የእነሱ የወደፊት ዕጣ ምንድን ነው? የሚለውንም ጥያቄ ውስጥ [የጥናቱ] አስገብተነዋል።»
ሰሎሞን ሙጬ
ሸዋዬ ለገሠ























