በካርቱም ከተማ የተፈጸመው የድሮን ጥቃት እና የተናፈቀው የተኩስ አቁም
Description
የፈጥኖ ደራሽ ኃይል በካርቱም ከተማ ላይ የድሮን ጥቃት መፈጸሙ
የሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም፣ አትባራ እና ኦምዱርማን ላይ ዛሬ አርብ በድሮኖች ጥቃት መፈጸሙን የዐይን እማኞች እና ወታደራዊ መኮንኖች አስታውቀዋል። ጥቃቶቹ የተፈጸሙት አሜሪካን ጨምሮ አራት ሀገራት ብሔራዊ ጦር እና በፈጥኖ ደራሹ ኃይል ለሰብአዊነት ተኩስ እንዲያቆሙ ግፊት እያደረጉ በሚገኝበት ወቅት ነው።
አሜሪካን ጨምሮ አራት ሀገሮች የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ሰብአዊ የተኩስ አቁም ላይ እንዲደርሱ ግፊት እያደረጉ በሚገኙበት ወቅት ካርቱም ላይ ዛሬ ድሮኖች መተኮሳቸውን የዐይን እማኞች እና የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን አረጋግጠዋል። የሱዳን ጦር በሚቆጣጠራቸው የከተማይቱ በርካታ ክፍሎች ፍንዳታዎች መሰማታቸውን የጀርመን ዜና አገልግሎት ዘግበዋል።
ከካርቱም በተጨማሪ አትባራ እና ኦምዱርማን የተባሉት ሁለትየሱዳን ከተሞች በፈጥኖ ደራሽ ኃይል ድሮኖች ዒላማ እንደነበሩ አንድ ከፍተኛ የጦር መኮንን ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል። በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን የገለጹት የጦር መኮንኑ በመሐመድ ሐምዳን ደጋሎ የሚመራው ታጣቂ ቡድን የተኮሳቸውን ድሮኖች የሱዳን ብሔራዊ ጦር እንዳከሸፈ ተናግረዋል።
የፈጥኖ ደራሹ ኃይል ለተኩስ አቁም መስማማቱን ማሳወቁ
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የድሮኖች ጥቃት የተፈጸመው አር ኤስ ኤፍ ለሰብአዊ ተኩስ አቁም መስማማቱን ካስታወቀ አንድ ቀን በኋላ ነው። የቡድኑ ቃል አቃባይ አል-ፋቴህ ቁራሺ ባሺር አሜሪካ እና አጋር አሸማጋይ ሃገራት ያቀረቡትን የስምምነት ሃሳብ ቡድኑ መቀበሉን ገልጸው ነበር።
«ለሱዳን ሕዝብ ምኞት እና ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች አሜሪካ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ሳዑዲ አረቢያ እና ግብጽ ያቀረቡት የሰብአዊነት ተኩስ አቁም ለመሳተፍ መስማማቱንያረጋግጣል። ይህ ሥምምነት የጦርነቱ አስከፊ የሰብአዊ መዘዝን ለመፍታት እና በሰብአዊ ተኩስአቁም ድንጋጌዎችን በማጠናቀቅ የሲቪሎችን ጥበቃ ለማሻሻል ያለመ ሲሆን ይህም ለሁሉም የሱዳን ሕዝቦች አስቸኳይ የሰብአዊ ርዳታ እንዲደርስ ያስችላል።»
በመሐመድ ሐምዳን ደጋሎ የሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ለሰብአዊነት ተኩስ የማቆም ሥምምነቱን በአፋጣኝ ተግባራዊ ለማድረግ፣ ግጭት የሚቆምበት ስልት እና የሱዳን የፖለቲካ ሒደት የሚመራባቸው ቁልፍ መርኆዎች ረገድ ውይይት ለመጀመር መዘጋጀቱን አስታውቋል።
የተፈናቃዮች ተስፋ
አሜሪካ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ግብጽ እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶችን ያካተተው የአሸማጋይ ሀገራት ቡድን የፈጥኖ ደራሹን ኃይል ወደ ስምምነት እንዳመጣው ይታመናል። አር ኤስ ኤፍ ትላንት ሃሙስ ስምምነቱን መቀበሉን ይፋ ሲያደርግ በተለይ የመሳሪያ ድምጽ ዝም እንዲል ለሚናፍቀው የሱዳን ሕዝብ ተስፋሰጥቶ ነበር። በጦርነቱ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በመጠለያ የሚገኙት ፋጢማ ዑስማን እንዳሉት ስምምነቱ ቀድሞ በመጣ ነበር ።
«ሁላችንም አንድ ቤተሰብ ነን። ከውጭ ሊዋጋን የመጣ የለም አይደል? ይህ ሥምምነት በፊት ከመኖሪያ ቤቶቻችን ሳንፈናቀል መምጣት ነበረበት። እናንተ የእኔ ልጆች እኔ የተናገርኩትን ወደ ጎን ብላችሁ ሔዳችሁ አጣሩ። የምታዩትን አትወዱትም። ወደ ኤል ፋሺር ስትሔዱ የምታዩትን አትወዱትም። ይሁንና በመስማማታቸው ፈጣሪ ይመስገን። እንዲስማሙ እንፈልጋለን። ሀገራችን ሱዳን ቤት አልባ፣ የተበታተነች እና ችግሮች የበዙባት እንድትሆን አንፈልግም። »
ይሁንና በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ይደገፋል የሚባለው የመሐመድ ሐምዳን ደጋሎ ታጣቂ ቡድን ቃሉን ለማክበሩ በርካታ ታዛቢዎች ጥርጣሬ አላቸው። የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ በበኩላቸው በአራቱ ሀገሮች የቀረበውን ምክረ ሐሳብ የሱዳን ብሔራዊ ጦር በበጎ እንደሚቀበል ተናግረዋል። ይሁንና በተኩስ አቁም ምክረ ሐሳቡ የሱዳን ብሔራዊ ጦር የሚስማማው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከተቆጣጠራቸው ሲቪል አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ለቅቆ ሲወጣ እና ከዚህ ቀደም በቀረቡ የሰላም ምክረ ሐሳቦች መሠረት የጦር መሣሪያ ሲያስረክብ ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል።
የብሔራዊ ጦሩ አቋም
የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀ መንበር እና የብሔራዊ ጦሩ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሉቴናንት ጄነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን በተንቀሳቃሽ የዕዝ ማዕከላቸው ትላንት ለከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ያደረጉት ንግግርም የሱዳን ቀውስ እንዲህ በቀላሉ እንደማይቋጭ ጥቆማ የሰጠ ነው።
«ከጨቋኝ አገሮችና ከትዕቢት ኃይሎች ያገኘችውን ድጋፍ ሁላችንም ተመልክተናል። ይህ ዘመቻ ይሰበራል፤ የሱዳን ሕዝብም ያሸንፋል። ሕይወታቸውን ለሰጡ ሰማዕታት ሁሉ እንበቀላለን። በኤል-ፋሺር፣ አል ጀኒና፣ በአል ጀዚራ እና በሁሉም ቦታ በአማጺያኑ በተጠቁ ቦታዎች ሁሉ የተገደሉ እና የተሰቃዩ ሁሉ እንበቀላለን። »
የተኩስ አቁም ለማድረግ ትናንት ፈቃዱን ሰጥቶ የነበረው የፈጥኖ ደራሹ ኃይል አሁን ፊታቸውን ወደ ምስራቅ ካርቱም እና እና በነዳጅ ዘይት ወደበለፀገው ኮርዶፋን ግዛት ያዞረ መስሏል።
ቡድኑ በምዕራብ ዳርፉር የምትገኘውን እና የብሔራዊ ጦሩ የመጨረሻ ይዞታ የነበረችውን የአልፋሽር ከተማ ሲቆጣጠር በሺዎች በሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የጅምላ ግድያ ፈጽሟል የሚል ብርቱ ክስ ሲቀርብበት ቆይቷል።
መዲና ካርቱም በድጋሚ በብሔራዊ ጦሩ እጅ ከገባች ወዲህ አንጻራዊ መረጋጋት ብታሳይም የፈጥኖ ደራሹ ኃይል የድሮን ዒላማ ከመሆን አላመለጠችም። አር ኤስ ኤፍ ከጎርጎርሳዉያኑ 2023 ጀምሮ በከተማዋ የወታደራዊ እና የሲቪል መሰረተ ልማቶችን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶች ሲፈጽም መቆየቱን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘገባ ያመለክታል።
ታምራት ዲንሳ
እሸቴ በቀለ






















