በጥቅምት ወር ስለጡት ካንሰር እንነጋገር
Description
የጥቅምት ወር በየዓመቱ በመላው ዓለም ስለጡት ካንሰር ሰዎች ግንዛቤ እንዲያገኙ መረጃዎች የሚሰራጩበት ወር ነው። የዘንድሮው መሪ ቃል ከጡት ካንሰር ጋር በተገናኘ ሰዎች የተለያየ ተሞክሮ እንደሚኖራቸው፤ በጊዜው የሚደረግ ምርመራና ክትትል ማድረግም እንደሚገባ ያሳስባል።
የጡት ካንሰር ይዞታ በመላው ዓለም
የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው በመላው ዓለም በሴቶች ላይ በብዛት ከሚከሰቱ የካንሰር ዓይነቶች የጡት ካንሰር ቀዳሚው ነው። ከሁለት ዓመት በፊት የጡት ካንሰር 2,3 ሚሊየን በሚሆኑ ሴቶች ላይ በምርመራ መገኘቱንም መዝግቧል። በተመሳሳይ በዚሁ ጊዜ በጡት ካንሰር ምክንያት ለሞት የተዳረጉት 670 ሺህ መሆናቸውንም ገልጿል። እንግዲህ ይህ ቁጥር ብቻ አይደለም፤ ሰዎች በተለይም ለየቤተሰባቸው እናቶች፤ እህቶች እንዲሁም ሴት ልጆች ናቸው።
እንዲያ ማለት ግን በህክምና ምርመራ የጡት ካንሰር የተገኘበት ሁሉ ሕይወቱን ያጣል ማለት አይደለም። የዘርፉ የህክምና ባለሙያዎች ደጋግመው እንደሚናገሩት ሰዎች በየግላቸው አካላቸውን በመዳበስ ሲፈትሹ በጡታቸው ላይ ለውጥ እንደተመለከቱ ወደ ሀኪም ቤት የሚሄዱት ሊያጋጥም የሚችለውን አደጋና ስጋት የመከላከል ብሎም የመቆጣጠር ዕድሉን ያገኛሉ። በተለያዩ አጋጣሚዎች ስለካንሰርና ህክምናው ያነጋገርናቸው ዶክተሮች እንደገለጹልን በህክምናው ሂደት ለእነሱም ለታካሚዎቹም ፈተና የሚሆነው የአብዛኞቹ ህመሙ ስር ከሰደደ፤ አንዳንዴም መጨረሻ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ለህክምና የሚመጡት መብዛታቸውን ነው። ይህ የታማሚውን እና የቤተሰብ ወዳጆቹን ብቻ ሳይሆን በሙያቸው ለመርዳት የተሰማሩትን የዘርፉን የህክምና ባለሙያዎችም ስጋት ውስጥ የሚከት አጋጣሚ እንደሆነም ይናገራሉ።
የዓለም የጤና ድርጅት የጡት ካንሰርን አስመልክቶ ይፋ ያደረገው መረጃ ባለፉት አምስት ዓመታት በካንሰር ተይዘው የዳኑ ሰዎች ቁጥር ገቢያቸው ከፍተኛ በሆነ ሃገራት ከ90 በመቶ ከፍ ማለቱን ያሳያል። በተቃራኒው መካከለኛ ገቢ ባላቸው እንደ ሕንድ በመሳሰሉ ሃገራት ወደ 60 በመቶ ዝቅ ያለ ሲሆን በደቡብ አፍሪቃ ደግሞ ይባስ ወደ 40 በመቶ የወረደ ነው። ለዚህ ልዩነት ዋነኛው ምክንያት ደግሞ የህመሙ ቀድሞ መታወቅ፤ በተገቢው ጊዜ የሚደረገው ምርመራ እና ውጤታማ የሆነ ህክምና ማግኘት መሆኑንም ገልጿል። ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሃገራት በካንሰር ምክንያት የሚከሰተውን የሕይወት መቀጠፍ ምጣኔ ለመቀነስም ስለካንሰር ሰዎች በየጊዜው መረጃ እንዲያገኙ ማድረግ እና የህክምናውን ሁኔታም ማሻሻልና ተደራሽ ማድረግ አማራጭ እንደሚያስፈልግም አመልክቷል።
የጡት ካንሰር በኢትዮጵያ
ለመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ የጡት ካንሰርን በተመለከተ ሁኔታው ምን ይመስላል? ስንል የዘወትር ተባባሪያችን የሆኑትን በአዳማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ከፍተኛ የካንሰር ህክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ቢንያም ተፈራን ጠየቅን። ዶክተር ቢንያም በየጊዜው ከአድማጮች ለሚመጡልን ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት ያለመታከት ከሚተባበሩን የህክምና ባለሙያዎችን አንዱ በመሆናቸው ምስጋናችንን አስቀደምን። እሳቸው እንደገለጹት ለህክምና ዘግይቶ መድን ጨምሮ ኅብረተሰቡ ስለካንሰር ያለው ግንዛቤ አሉታዎ ተጽዕኖ አስከትሏል። ይህም ብቻም አይደለም በህክምናው ሙያ ዘርፍ የካንሰር ህመም ልየታ ለማድረግ የሚችል በሙያው የሰለጠነ በቂ የሰው ኃይል አለመኖሩ፤ ታካሚዎችን በተመለከተም የካንሰር ህክምና ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ አቅም በማጣትም የሚያቋርጡ መኖራቸው ተደማምሮ እንደኢትዮጵያ ባሉ ደሀና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሃገራት በጡት ካንሰር ምክንያት የሚሞቱትን ቁጥር እንደጨመረውም አስረድተዋል። የካንሰር ከፍተኛ የህክምና ባለሙያው እንደሚሉት ኢትዮጵያ ውስጥ የካንሰር ታማሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ ከፍ ብሏል።
ወደ ህክምና ዘግይቶ መሄድ ያለው ጣጣ
የህክምና አማራጮችን በአግባቡ መጠቀምን በተመለከተ፤ በተለይ በከተማና ህክምናው በሚገኝባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ወገኖች ያሉ አማራጮችን በጊዜ አለመጠቀማቸው ችግሩን ሳያባብሰው እንዳልቀረ ይገመታል።
ዶክተር ቢንያም እንዳሉትም በአደጉት ሃገራት አስቀድሞ በሚደረጉ ክትትልና ምርመራዎች አማካኝነት ችግሩ መኖሩ ሲታወቅ ህክምናውን በመስጠት ሰዎች ከጡት ካንሰር እየዳኑ ረዥም ዓመት መኖር እንደሚችሉ እየታየ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ይላሉ የዘርፉ የህክምና ባለሙያ፤ ታማሚዎች ወደህክምና ዘግይተው ስለሚመጡ ከዚህ ይለያል።
እዚህ ጀርመን ሀገር ከ40 ዓመት በላይ የሆናቸው ሴቶች በጤና ኢንሹራንስ አማካኝነት ከየቤታቸው ማሞ ግራም በተሰኘው መመርመሪያ የጡት ካንሰር ምርመራ እንዲደረግላቸው ይጠራሉ። ይህ በየሁለት ዓመቱ ሳያሰልስ የሚደረግ ነው። ዶክተር ቢንያም ኢትዮጵያ ውስጥ እሳቸውና በዚህ የህክምና ዘርፍ የተሰማሩ ሀኪሞች እስካሁን እየሠሩበት ስለሚገኘው የጡት ካንሰር መርመሪያዎች ገልጸውልናል።
ካንሰር መነሻው በትክክል አይታወቅም ነው ያሉት ዶክተር ቢንያም ስለዚህ ሁሉም ሴቶች በየወሩ ከሚያደርጉት ከግል ፍተሻ ጀምሮ፤ በዓመት አንድ ጊዜ ደግሞ ወደ ሀኪም ቤት ሄደው መመርመር እንደሚኖርባቸው መክረዋል። ከዚህም ሌላ ለካንሰር ተጋላጭነትን የሚጨምሩ ለምሳሌ ከመጠን ያለፈ ውፍረት፤ አመጋገብን ማስተካከል፤ ቅባታማ ምግቦችን፤ በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችን መቀነስ፤ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ፤ ጭንቀትን መቀነስና ተያያዥ ጥንቃቄዎችን መክረዋል። የካንሰር ከፍተኛ ሀኪሙ በህክምና ሂደት የሚገጥሟቸውን አስቸጋሪ ሁኔታዎችም ገልጸውልናል። ለብዙዎች ትምህርት ይሆናልና በሌላ ጊዜ እንመለስበታለን። ለሰጡን ማብራሪያ ዶክተር ቢንያም ተፈራን በማመስገን፤ እንሰናበት።
ሸዋዬ ለገሠ
ታምራት ዲንሳ