የኃይል መቋረጥ የፈተናቸው የኮሬ ዞን ነዋሪዎች
Description
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልልኮሬ ዞን ነዋሪዎችእንደሚሉት በዞኑ በሙሉ እና በከፊል እየተቋረጠ የሚገኘው የአሌክትሪክ ሀይል የዕለት ተዕለት ኗሯቸውን አስቸጋሪ እያደረገባቸው ይገኛል ፡፡ በዞኑ ኬሌ ፣ ጂጆላ ፣ ኬሬዳ እና ዳኖ ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎች “ የሀይል መጥፋት ከአቅማችን በላይ ሆኗል “ ሲሉ ቅሬታቸውን ለዶቼ ቨለ ተናግረዋል ፡፡ በተለይም የሀይል መቋረጥና መጥፋት የህክምና አገልግሎትን ጨምሮ መሠረታዊ በሚባሉ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ሥራ እያስተጓጎለ እንደሚገኝ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል ፡፡
ወደ የወፍጮ ድንጋይ ዘመን እንመለስ ወይ ?
ወይዘሮ ማሚቱ ኦልግሳ በኮሬ ዞን የኬሌ ከተማ ነዋሪ ናቸው ፡፡ ካባለፈው የሰኔ ወር መግቢያ አንስቶ ለኬሌ ከተማ የሚቀርበው ኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት እየተቆራረጠ እንደሚገኝ የሚናገሩት ወይዘሮዋ “ መብራት በዚህ ሳምንት ከመጣ በቀጣዩ ሳምንቱን ሙሉ ይጠፋል ፡፡ በዚህም የተነሳ ልጆቼን አብስዬ ለመመገብ አልቻልኩም ፡፡ በተለይ አኔን በመሳሰሉ እናቶች ላይ ከፍተኛ ጫና ነው የፈጠረብን ፡፡ አሁን ምን እናድርግ ? ማንስ ይስማን ? ወይስ ወደ ቀድሞው የወፍጮ ድንጋይ ዘመን እንመለስ ወይ “ ሲሉ ጠይቀዋል ፡፡
የኮሬ ዞን መስተዳደር ምላሽ
የዞኑ ነዋሪዎች ቅሬታን አስመልክቶ ዶቼ ቨለ ያነጋገራቸው የኮሬ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታረቀኝ በቀለ ቅሬታው ትክክለኛ መሆኑና አረጋግጠው በአካባቢው የታጠቁ ቡድኖች በሚያደርጉት እንቅስቃሴ በፈጠረው የፀጥታ ሥጋት የኤሌክትሪክ መስመሮችን ለመጠገን አዳጋች ማድረጉን ተናግረዋል ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአካባቢው በሚገኙ የአገር መከላከያና የፌዴራል ፖሊስ ድጋፍ መስመሮችን የመጠገን እና ያረጁ ምሶሶዎችን የመቀየር ሥራ መጀመሩን ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል ፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሀይል አቅርቦቱን ወደ ቦታው ለመመለስ በቅንጅት እየተሠራ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል ፡፡
ዘላቂ መፍትሄ
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪ ሀይል አገልግሎት የቡሌ የአርባምንጭ ሪጅን በበኩሉ በዞኑ ለተፈጠረው የሀይል እጦት የፀጥታ ሥጋት አንዱ ምክንያት ቢሆንም ሌላ ተጨማሪና መሠረታዊ ምክንያት መኖሩን አስታውቋል ፡፡ ለዞኑ ሀይል እየቀረበ የሚገኘው ከጉጆ ዞን ቡሌ ሆራ ከሚገኘው የሀይል ማከፋፈያ ጣቢያ ለብዙ ከተሞች የሚያገለግልና ከፍተኛ ጫና ያለበት መሆኑ ለሀይል መቋረጥ ሌላው ተግዳሮት እንደሆነ ሪጅኑ ጠቅሷል ፡፡ አሁን ላይ የኃይል መዋዠቅና መጥፋትን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ሥራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ነው በአገልግሎቱ የአርባ ምንጭ ሪጅን የአማሮ ኮሬ አገልግሎት ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን መሐመድ የገለጹት ፡፡
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ታጣቂዎች በሚያደርሱት የደፈጣ ጥቃት የህዝብና የጭነት መጓጓዣን ጨምሮ በተለያዩ የአገልግሎት አቅርቦት ላይ ጫና አሳድሮ ይገኛል ፡፡ በዞኑ ታጣቂዎች በየጊዜው በሚያደርሷቸው ጥቃቶች በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ እንደሚገኝ ይታወቃል ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ኂሩት መለሰ
ታምራት ዲንሳ