የአየር ለውጥ ጉባኤ
Description
ኢትዮጵያ እንደጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2027 የሚካሄደውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ለውጥ ጉባኤ እንድታዘጋጅ ይሁንታ አግኝታለች። ኢትዮጵያ ጉባኤውን እንድታዘጋጅ ይሁንታ ማግኘቷ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን የበለጠ ለማጎልበትና ያሉትን የሕግ ይሁን የአመለካከት ችግሮችን ለመቅረፍ ትልቅ ዕድል ሊሰጥ እንደሚችል አንድ የአካባቢ ጥበቃ ባለሞያ ለዶይቸቨለ ተናግረዋል።
በእንግሊዝኛ ምህጻሩ COP ወይም «ኮንፈረንስ ኦፍ ፓርቲስ» የሚል ስያሜ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ጸባይ ለውጥን አስመልክቶ የሚመክር የድርጅቱ ታላቅ ጉባኤ እንደሆነ ይታወቃል። እንደ ጎርጎረሳውያኑ አቆጣጠር በ1992 የተጀመረው ጉባኤ በተለያዩ ሐገሮች ተካሂዶ የአየር ለውጥን የሚመለከቱ የተለያዩ ጉዳዮች ተመክሮበታል፤ ውሳኔዎችም ተላልፎበታል።
መልካም ዜና ነው
የዘንድሮው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ጸባይ ለውጥ ጉባኤ በብራዚል ቤሌም ከተማ እየተካሄደ ያለ ሲሆን ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2027 የሚካሄደውን ጉባኤ በአዲስ አበባ እንድታካሂድ ተመርጣለች። ኢትዮጵያ ይህን ዕድል ማግኘቷ የጉባኤውን አጀንዳዎች በመቅረጽ፣ በጉባኤው ሊተላለፉ የሚገባቸው ውሳኔዎችን ከራሷና ከአፍሪካ ሐገራት ብሔራዊ ጥቅሞች ለመቃኘትና በአየር ለውጥ ተጽኖ መከላከልን በተመለከተ እየሰራችው ያለውን ስራዎችን ለዓለም ለማስተዋወቅ ታላቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተገልጿል።
አቶ መልካሙ ኦጎ «ቁም ለአካባቢ» የተባለው በአካባቢ ጥበቃ የሚንቀሳቀስ ድርጅት መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። የውሳኔውን ዜና በመልካም ጎኑ እንደተቀበሉት ነግረውናል።
« ይሄ ዜና በዚህ ዘርፍ ለተሰማሩና ከጉዳዩ ጋር ግኑኝነት ያላቸው ሥራዎችን ለሚሰሩ ትልቅ ዜና ነው። ከዛም አልፎ እንደ ሐገርም ልንኮራበት የሚገባ ነው ብዬ ነው የማሰብው።»
«ቁም ለአካባቢ» የተባለው ድርጅት በሐገሪቱ ያልተለመዱ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን ያከናውናል።
በተለያዩ የሐገሪቱ ክፍሎች አየር በካይ የሆኑ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ወደ ሕግ በማቅረብ ከድርጊታቸውን እንዲቆጠቡ፤ በአየር ብክለቱ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ነዋሪዎች ደግሞ ተገቢውን ካሳ እንዲከፍሉ የማድረግ ሥራ።
ሥራውን እንደ የቅንጦት የማየት አባዜ
በዚህ መስክ በሕብረተሰቡ ዘንድ ያለው ምልከታ አመርቂ አለመሆኑንን ይናገራሉ።ሥራውን የቅንጦት አድርጎ የመመልከት አዝማሚያ እንዳለ በማከል።
ለሕብረተሰብ ጥቅም ሲባል የሚካሄዱየአካባቢ ጥበቃ የፍርድቤት ሙግቶች የሕግ ማዕቀፍ ልል መሆን፣ የአስፈጻሚ አካላት በቂ ግንዛቤ አለመኖር፤ በዚህ ጉዳይ ላይ የዳበረ አሰራር አለመኖር የአካባቢ ጥበቃ ሥራውን አስቸጋሪ እንዳደረገው አቶ መልካሙ ያክላሉ።
ኢትዮጵያ እንዲህ አይነት በአየር ጸባይ ለውጥ የሚመክር ጉባኤ ለማዘጋጀት ዕድል ማግኘቷ በሐገሪቱ ለሚደረጉ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን ለማጎልበት የሚረዱ ልምዶችን ለማግነት እንደሚረዳ ባለሙያው ይናገራሉ።
« ይህ ጉባኤ ኢትዮጵያ ውስጥ መደረጉ ምንድነው የሚጠቅመው ከተባለ ይሄ አሁን እየሰራነው ያለነውና በአለም የዳበረ ስለሆነ በዚህ ዘርፍ የዳበረ ዕውቀት ያላቸው ሰዎች በደንብ ስለምንገናኝ፤ ለጉዳዩ ትኩረት ስለሚሰጥ፤ ም ሐሳባችንን በማጋራት ከነሱም ግብአት የምንወስድበት ነው የሚሆነው።»
በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አምባሳደር ልዑል ሰገድ ታደሰ በጉባኤው ባደረጉት ንግግር «በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ዕምነታችሁን ስለጣላችሁ እናመሰግናለን» ብለዋል። ኢትዮጵያ አፍሪቃን ወክላ የኮፕ ጉባኤ ለማዘጋጀት ከምዕራብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ናይጄሪያ ብርቱ ውድድር ገጥሟት የነበረ ሲሆን የጉባኤተኛውን አብላጫ ድጋፍ ማግኘት ችላለች።
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ታምራት ዲንሳ























