የ10 ተቃዋሚ ፓርቲዎች መግለጫ
Description
«ምቹ ሁኔታ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ፤ ምርጫን ለማካሄድ የሚያደርጋቸው ጥረቶች ሁሉ ትርጉም አልባ ናቸው» ሲሉ 10 የፖለቲካ ፓርቲዎች ባወጡት የጋራ መግለጫ አሳሰቡ። ፓርቲዎቹ የምርጫ ምቹ ሁኔታን መፍጠር አማራጭ ሳይሆን ቅድመ ሁኔታ መሆኑን አበክረን እናሳስባለን ብለዋል።
« ምቹ ሁኔታን መፍጠር አማራጭ ሳይሆን ቅድመ ሁኔታ ነው»
በጣምራ መግለጫውን ያወጡት ፓርቲዎች ሕብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የመላው ሲዳማ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ አንድነት፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ ፣ የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄና ዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ለሉአላዊነት ናቸው።
ፓርቲዎቹ ባወጡት 7 ነጥቦችን ያካተተ መግለጫ በሐገሪቱየምርጫ ምቹ ሁኔታን መፍጠርአማራጭ ሳይሆን ቅድመ ሁኔታ መሆኑን አበክረን እናሳስባለን ብለዋል። መግለጫውን ካወጡት ፓርቲዎች የኢሕአፓ ፕረዚደንት አቶ አብርሐም ሐይማኖት በመግለጫው ከተካተቱ ነጥቦች የተወሰኑትን እንዲህ ያብራራሉ።
«በተለያዩ አካባቢዎች ጦርነቶች አሉ። እነዚህ ጦርነቶች በሚቆሙበት ሁኔታ ላይ መወያየትና መደራደር ያስፈልጋል። የህሊና እስረኞች፤ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሊፈቱ ይገባል።»
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አመሃ ዳኘው በበኩላቸው በሐገሪቱ ያለው የሰላም ሁኔታ ለምርጫው ዕንቅፋት እንደሆነ አስረድቷል።
«የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ይከበር»
አስሩ ፓርቲዎች ከምርጫው በፊት ይቅደሙ ካሏቸው ነጥቦች ሌላኛው የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ነው። የፖለቲካ ምህዳሩም አስቸጋሪ መሆኑን በማከል። አቶ አብርሃም ሃይማኖት፤
« የሚድያ ነጻነት ሊኖር ይገባል። ሚድያዎች በነጻነት ሊዘግቡ ይገባል። ለምሳሌ ምርጫ እየተቃረበ የዶይቼቨለ በአገር ውስጥ መታገድ አንዱ ምሳሌ ነው ለዚህ ምርጫ ሳንካ እና ሌሎችም ብዙ ሚድያዎች እንደ ዶይቼቨለ ታግደዋል፤ ጠንካራ የሕዝብ ድምጽ የሆኑት። አንዳንዱ ደግሞ ወይ ሥራችሁን አቁሙ ወይ ሚድያችሁ ይዘጋል ተብለው በፍርሃት ላይ ነው ያሉትና ፖሊሲዎቻችን በነጻነት የምናቀርብበት ሚድያ የለንም።»
ማሻሻያ ባይደረግስ?
በአስሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫው በፊት መሻሻል አለባቸው ተብለው የተዘረዘሩ 7 ነጥቦችከምርጫው በፊት ተፈጻሚ የመሆን ዕድላችው ምን ያህል ነው? ካልተፈጸሙስ? ተብሎ ከዶይቼቨለ ለቀረበ ጥያቄ አቶ አብርሃም ሃይማኖት ሲመልሱ በመንግስት በኩል ቅንነት ካለ ሊፈጸሙ እንደሚችሉ ገልጸው ካልተፈጸሙስ ለሚለው ደግሞ፤
« ባይሆኑ ተወያይተን የምወስዳቸው ጠንካራ እርምጃዎች ይኖራሉ። ዝርዝር ሄኔታውን በቅርቡ ይፋ የምናደርግ ይሆናል።»
መግለጫው የጸጥታ ሃይሎችን ጨምሮ የመንግስት መዋቅር ገለልተኛ መሆን እንዳለበት ጠቅሶ እነዚህ የተዘረዘሩ ሁኔታዎች ሳይሟሉ የሚደረግ ማንኛውም ምርጫ የሕዝብን ፍላጎት ከመግለፅ ይልቅ የይስሙላ ዴሞክራሲ ማሳያ እንደሚሆን እናምናለን ብሏል።
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በጋራ ባወጡት መግለጫ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ ከመንግስትም ሆነ ከምርጫ ቦርድ የተሰጠ ምላሽ የለም።
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ታምራት ዲንሳ























