የዓለም ባንክ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸዉ ሐገራት ለጤና የሚመድቡት ገንዘብ እጅግ አነስተኛ ነዉ አለ
Description
የዓለም ባንክ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸዉ ሐገራት ለጤና የሚመድቡት ገንዘብ እጅግ አነስተኛ ነዉ አለ
እንደ ኢትዮጵያ፣ ማሊና ዩጋንዳን የመሳሰሉ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸዉ ሐገራት መንግሥታት ለጤና ጥበቃ የሚመድቡት ገንዘብ እጅግ በጣም ትንሽ መሆኑን የዓለም ባንክ ያለፈዉ ረቡዕ አስታዉቋል። ድሆቹ ሐገራት መንግስታት ለጤና የሚመድቡት ገንዘብ የዓለም ባንክ መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ለማዳረስ ያስፈልጋል ከሚለዉ ዝቅተኛ ተመን እንኳ በእጅጉ ያነሰ ሲል የዓለም ባንክ በሪፖርቱ ገልጿል። የዓለም ባንክ እንደሚለዉ ባለፈዉ የጎርጎረሳዉያኑ 2024 ኢትዮጵያ፣ ማሊ እና ዩጋንዳን የመሳሰሉት ሐገራት መንግስታት ለጤና ጥበቃ የመደቡት በነብስ ወከፍ በዓመት 17 ዶላር ነዉ። ይሁንና ይህ ገንዘብ ሃገራቱ በጎርጎረሳዉያኑ 2024 ለመሰረታዊ ጤና ጥበቃ ይመድባሉ ብሎ ከገመተዉ በሦስት እጥፍ ያነሰ መሆኑ ተመልክቷል። እንደ ባንኩ ገለፃ ድሆቹ ሐገራት ለየዜጋቸዉ መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ለማዳረስ በርዳታም ያግኙት ከየካዝናቸዉ በዓመት በትንሹ 90 ዶላር መመደብ አለባቸዉ። ለጤና አገልግሎት የሚመደበዉ ገንዘብ በድሆቹ ሐገራት ብቻ ሳይሆን እንደ ህንድ ፓኪስታን ቬትናም የመሳሰሉ፤ በመካከለኛ ዕድገት ላይ በሚገኙ ሐገራት ለጤና ጥበቃ የሚመድቡት ገንዘብ የመቀነስ አዝማሚያ እንደሚታይበት ባንኩ አስታዉቋል። በዚህ ጉዳይ ላይ በዩናይትድ ስቴትስ ፤ አትላንታ የሚገኘዉን የዶቼ ቬለ ዘጋቢ፤ ታሪኩ ኃይሉን፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ የማሊን እና የዩጋንዳን የመሳሰሉ ሃገራት የጤና ተደራሽነትን አስመልክቶ የዓለም ባንክ ያወጣዉን ዘገባ እንዴት ይታያል፤? ሃገራቱ ለጤና ተደራሽነት ሚመድቡት ገንዘብ ማነስ ምክንያቶቹ ምንድን ናቸዉ፤ ተፅኖዉስ ፤ ስንል አነጋግረነዋል።
ታሪኩ ኃይሉ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ























