የታኅሣሥ 6 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
Description
በስፔን ላሊጋ የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ ዣቪ አሎንሶ ላይ ጫናው በርትቷል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ታሪክ በ16 ጨዋታዎች ሁለት ነጥብ ብቻ ይዞ አደገኛ ቁልቁለት ውስጥ የሚገኘው ዎልቨርሀምፕተን ዎንደረርስ በመሪው አርሰናል የማታ ማታ ተሸንፏል ። ሔሪ ኬን ያገኛት ፍፁም ቅጣት ምት የቡንደስሊጋ መሪው ባዬርን ሙይንሽንን በገዛ ሜዳው ከመሸነፍ ታሪካዊ ጉድ አትርፎታል ። የጀርመን የሴቶች የእጅ ኳስ ቡድን በዐለም ዋንጫ ግጥሚያ ለጥቂት ዋንጫ ሳያነሳ ቀርቷል ። ዩናይትድ ስቴትስ በቅርቡ በሚከናወነው የዓለም አገር አቋራጭ ፉክክር ለመወዳደር ያመለከተው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን ቪዛ መከልከሉ ተሰምቷል ። ኢትዮጵያዊት እና ኤርትራዊት ብስክሌተኞች ጀርመን በሚገኝ ቡድን ውስጥ በቀጣዩ የጎርጎሪዮሱ ዓመት ለመሰለፍ ፈርመዋል ።
አትሌቲክስ የአሜሪካ ቪዛ ማግኘት ከብዷል
ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከ26 ቀናት በኋላ ለሚከናወነው 46ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ያመለከተው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን ቪዛ መከልከሉ ተሰምቷል ። ዩናይትድ ስቴትስ ወደ አገሯ ለመግባት የሚያመለክቱ የውጭ አገራት ሰዎች ላይ በፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ጥብቅ የቪዛ ቁጥጥር ጀምራለች ። በተለይ ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ ለኢትዮጵያውያን ትሰጥ የነበረውን ጊዜያዊ የሕግ ከለላ (TPS) ካቋረጠች በኋላ ቁጥጥሩ ጥብቅ ሁኗል ።
ለኢትዮጵያውያን ከለላው መነሳቱ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ከተነገረ በኋላ ቁጥጥሩ ይበልጥ ጠብቋል ። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እና የቡድኑ አባላት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ለመጓዝ ያቀረቡት የቪዛ ማመልከቻ ውድቅ መደረጉ ተዘግቧል ። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከውድድሩ አዘጋጆች ጋር በመነጋገር ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለው እንደሆነ ገልጧል ። የስፖርት ጋዜጠኛ ዖምና ታደለ የፌዴሬሽኑ ኃላፊዎችን አነጋግሯል ። ለመሆኑ የአትሌቶቹ የጉዞ እጣ ምን ይመስላል?
ዩናይትድ ስቴትስ የሚቀጥለው የዓለም ዋንጫን ከሚያዘጋጁ ሦስት አገራት መካከል አንዷ ናት ። ከአፍሪቃ ደግሞ በእርግጠኝነት ዘጠኝ ምናልባትም የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ከተሳካላት ዐሥር አገራት በዓለም ዋንጫው ይሳተፋሉ ። እናስ የአፍሪቃውያን እግር ኳስ ተጨዋቾች፣ ቤተሰቦቻቸው እና ደጋፊዎቻቸው የአሜሪካ ቪዛ የማግኘታቸው ነገር ምን ይመስላል፤ ይህ ጥብቅ ቁጥጥር እና ክልከላስ በውድድሩ ላይስ ምን ሊያጠላ ይችላል?
አጣብቂኝ ውስጥ የገባው የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ ዣቪ አሎንሶ
የሪያል ማድሪዱ ዣቪ አሎንሶ ለ236 ጊዜያት በተጨዋችነት ወዳገለገለበት ሪያል ማድሪድ በአሰልጣኝ ከተመለሰ ገና ስድስት ወሩ ነው ። ከአሰልጣኝነቱ ሊነሳ እንደሚችል ግን ከወዲሁ ጫናው በርትቷል ። በተለይ በሻምፒዮንስ ሊግ በማንቸስተር ሲቲ የደረሰበት ሽንፈት ሪያል ማድሪድ ምርጥ ስምንት ቡድን ሁኖ የመጨረሱ ነገርን አጣራጣሪ አድርጓል ። ሪያል ማድሪድ ትናንት አልቫሬዝን 2 ለ1 ቢያሸንፍም፤ በዚህ የጨዋታ ዘመን ስድስት ሽንፈቶችን አስተናግዷል ። የዣቪ አሎንሶ እጣ ፈንታ አነጋጋሪ ሁኗል ። ላሊጋውን በ43 ነጥብ የሚመራው ባርሴሎና ቅዳሜ ዕለት ዘና ብሎ ዖሳሱናን 2 ለ0 ድል ማድረጉ ከሪያል ማድሪድ ጋር የነጥብ ልዩነታቸውን ወደ አራት ከፍ አድርጎታል ።
ሪያል ማድሪድ ባለፈው የጨዋታ ዘመን ከደረሰበት የሁለት ጊዜያት ሽንፈት አንጻር የዘንድሮው በሦስት እጥፍ ስድስት መድረሱ ነው አሰልጣኙ ላይ ጫናውን ያበረታው ። የሪያል ማድሪድ «ለ» ቡድንን የሚያሰለጥነው የቡድኑ የቀድሞ የኋላ ተመላላሽ ተከላካይ አርቤሎዋ ዣቪ አሎንሶን ሊተካ ይገባል የሚሉ ድምፆች ይሰማሉ ። ዣቪ አሎንሶ የአርቤሎዋን ብቃት በማወደስ ወደፊት ዋናውን ቡድን የመረከብ አቅም እንዳለው ጠቅሷል ። ሆኖም ሪያል ማድሪድ በላሊጋው ከመሪው ባርሴሎና ጋር ያለው ልዩነት እስካልሰፋ ድረስ በቡድኑ መቆየት እንደሚሻ ገልጧል ። ባለፈው ሰኔ ሪያል ማድሪድን በአሰልጣኝነት ከተረከበ ጀምሮ በዘጠኝ ጨዋታዎች ሦስቱን ብቻ በማሸነፉ ዣቪ አሎንሶ ላይ ጫናው እንደበረታ ነው ።
ዎልቨርሀምፕተን በቀውስ የቁልቁለት ጎዳና
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ታሪክ ዎልቨርሀምፕተን ዎንደረርስ በ16 ጨዋታዎች ሁለት ነጥብ ብቻ ይዞ አደገኛ ቁልቁለት ውስጥ ይገኛል ። ከወራጅ ቀጣና ውጪ ካሉ ቡድኖችም በ15 ነጠብ ልዩነት ቁልቁል ርቋል ። 35 ግቦችን አስተናግዶ የግብ ጎተራም ተሰኝቷል ። ዘንድሮ ከፕሬሚየር ሊጉ የመሰናበቱ ነገርም ሳይታለም የተፈታ ነው፥ አንዳች ተአምር ካልተፈጠረ በስተቀር ። ቅዳሜ እለት በመሪው አርሰናል 2 ለ1 ተሸንፎ ተስፋውን አጨልሟል ። በእርግጥ ዎልቨርሀምፕተን እስከ 90 ደቂቃው ድረስ ከአርሰናል ጋር አንድ እኩል ቆይተው የአርሰናል ደጋፊዎችን አስጨንቀው ነበር ። የማታ ማታ ግን ቡካዮ ሳካ ያሻማትን ኳስ ከጋብሪየል የሱስ ለማስጣል የሞከረው የኋላ ተከላካይ የርሶን ሞስኬራ በገዛ መረቡ ላይ በጭንቅላት አስቆጥሮ አርሰናልን እፎይ አስብሏል፥ ለቡድኑ ግን ሌላ ጭንቀት ጋብዟል ።
ዎልቨርሀምፕተን በአሰልጠኛ ቪቶር ፔራይራ አመራር በ11 ጨዋታዎቸ አንድም ጊዜ ማሸነፍ ተስኖት ነበር አሰልጣኙን ያሰናበተው ። እሳቸውን በተኩት አሰልጣኝ ሮብ ኤድዋርድ ዘመንም ይኸው ትናንት ለአምስተኛ ጊዜ ምንም የተሻሻለ ነገር የለም ። ደጋፊዎች በቻይና ኩባንያ በተያዘው ዎልቨርሀምፕተን ላይ ቁጣቸውን እያንፀባረቁ ነው ። አሰልጣኙ የደጋፊዎችን ስሜት እንደሚረዱ ገልጠው ተጨዋቾቻቸውን እንዲደግፉ ተማፅነዋል፥ በዛው ልክ ደግሞ ደጋፊዎች ከተጨዋቾች የበለጠ ይፈልጋሉ ሲሉም አክለዋል ። ከሽያጭ የተረፉት ተጨዋቾች ግን ያን ፍላጎት የሚያሟሉ አይመስሉም ።
ቡድኑ ከዐሥር ዐመታት የፕሬሚየር ሊግ ቆይታ በኋላ የመሰናበቱ ነገር ገና በጊዜ ቁርጡ የለየለት መሰሏል ። ለዚህ ሁሉ ምስቅልቅሉ ሰበቡም ምርጥ ተጨዋቾቹን ለተለያዩ ቡድኖች ሸጦ ባገኘው ገንዘብ እነሱን የሚተኩ ተጨዋቾችን ያለማስመጣቱ ነው ። ማቲው ኩናን ለማንቸስተር ዩናይትድ፣ የግራ ተከላካይ ሪያን ኤይት ኑሪን ለማንቸስተር ሲቲ ሸጧል ። ኔልሰን ሴሜዶን ለፌሬንባህ፣ ፓብሎ ሳራቢያን ለአል አራቢያ ሰጥቷል ። እነዚህ ቁልፍ ተጨዋቾቹን ግን መተካት አልቻለም ። የኅዳር 29 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ዎልቨርሀምፕተን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1980ዎቹ የገጠመው ምስቅልቅል ውስጥ እያመራ ይመስላል ። የዛሬ ዐርባ ዐመታት ግድም ዎልቨርሀምፕተን በሦስት ዐመታት ልዩነት ከፕሬሚየር ሊጉ ወደ አራተኛ ደቪዚዮን አሽቆልቁሎ ነበር ። አሁንም በፕሬሚየር ሊጉ የተያያዘው የሽምጥ ጉዞው የሚያሳየው ከዛ የተለየ አይመስልም ። ባለፈው ሰኞ በማንቸስተር ዩናይትድ 4 ለ 1 ድባቅ ከተመታ በኋላ፤ ከትናንት በስትያ በብርቱ ቢታገልም በአርሰናል የ2 ለ1 ሽንፈት አስተናግዷል ። ዎልቨርሀምፕተንን ከፕሬሚየር ሊጉ ከወዲሁ ደህና ሰንብት ማለቱ ሳይቀል አይቀርም ።
ሊቨርፑል አሰልጣኝ አርኔ ስሎትና ሞሐመድ ሣላኅ ተስማሙ?
ሊቨርፑል ከአሰልጣኝ አርኔ ስሎት ጋር የተነጋገረው ሞሐመድ ሣላህን አሰልፎ ድል ተቀዳጅቷል ። ግብጻዊው አጥቂ ሞሐመድ ሣላኅ ብራይተንን 2 ለ0 ባሸነፉበት ጨዋታ ግብ የሚሆን ኳስ አመቻችቷል ። በሊቨርፑል ታሪክም ግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማመቻቸት ቀዳሚ መሆን ችሏል ። ጨዋታው እንደተጠናቀቀ ቤተሰቦቹ ወደሚገኙበት የደጋፊዎች አቅጣጫ በማቅናት እጁን በማውለብለብ ተሰናብቷል ። የትናንቱ ግጥሚያ ከሊቨርፑል ጋር የመጨረሻው ነበር፤ ለግብጽ ብሔራዊ ቡድኑ ተሰልፎ ለመጫወት ከማምራቱ በፊት ። አሰልጣኝ አርኔ ስሎት ከአፍሪቃ ዋንጫ በኋላ ግብጻዊው አጥቂን «እንኳን ደህና መጣህ »ብለው ይቀበሉት እንደሆን ተጠይቀው « እንዴታ» ብለዋል ። የሰሞኑ የሞሐመድ ሣላኅ እና የአሰልጣኙ ውዝግብ ለጊዜው በዚሁ የተፈታ ይመስላል ።
ሊቨርፑል በቅዳሜው ድሉ ነጥቡን ወደ 26 ደረጃውን ወደ ስድስት ከፍ አድርጓል ። ከመሪው አርሰናል ጋር የዐሥር ነጥብ ልዩነት አላቸው ። ማንቸስተር ሲቲ በ34፣ አስቶን ቪላ በ33 እንዲሁም ቸልሲ በ28 ነጥብ እስከ አራተኛ ደረጃ ይከታተላሉ ። ቅዳሜ ዕለትቸልሲ ኤቨርተንን 2 ለ0 ትናንት ማንቸስተር ሲቲ ክሪስታል ፓላስን በገዛ ሜዳው 3 ለ0 አሸንፈዋል ። ዛሬ ማታ ማንቸስተር ዩናይትድ በሜዳው ኦልድ ትራፎርድ እና በደጋፊዎቹ ፊት በርመስን ያስተናግዳል።
ባዬርን ሙይንሽን በቡንደስሊጋው ከጉድ ተርፏል
ሔሪ ኬን በፍፁም ቅጣት ምት ያስቆጠራት ግብ የቡንደስሊጋ መሪው ባዬርን ሙይንሽንን በገዛ ሜዳው ከመሸነፍ ታሪካዊ ጉድ አድኖታል ። ከ19 ዐመታት ወዲህ ባዬርን በገዛ ሜዳው ለዚያውም ወራጅ ቀጣናው ግርጌ በሚገኘው ማይንትስ ሊሸነፍ ነበር ። በ87ኛው ደቂቃ ላይ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ከመረብ በማሳረፍ ግን ሔሪ ኬን ባዬርንን ታድጓል ። ነጥቡንም 38 አድርሷል ። ማይንትስ ከ14 ጨዋታ በኋላ በ7 ነጥቡ ብቻ ተወስኖ የመጨረሻ 18ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። 29 ነጥብ ያላቸው ላይፕትሲሽ እና ቦሩስያ ዶርትሙንድ በግብ ክፍያ ብቻ ተበላልጠው ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ።የኅዳር 15 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ጀርመን በእጅ ኳስ የዐለም ዋንጫ
የጀርመን ብሔራዊ ቡድን በእጅ ኳስ የዐለም ዋንጫ የሴቶች ግጥሚያ ለጥቂት ዋንጫ ሳያነሳ ቀረ ። ብርቱ ፉክክከር በታየበት የትናንቱ ግጥሚያ የኖርዌይ ቡድን አሸንፊ ዋንጫውን አንስቷል ። ለጥቂት 23 ለ21 የተሸነፈው የጀርመን ቡድን የብር ሜዳሊያ ተሸልሟል ። የሦስተኛ ደረጃውን ፈረንሳይ የጋራ አስተናጋጇ ኔዘርላንድን 33 ለ31 አሰሸንፋ አግኝታለች፥ ነሐስ ሜዳሊያም አጥልቃለች ።
የኤርትራ አገር አቀፍ የብስክሌት ውድድር የሁለት ጊዜያት አሸናፊ ሞናሊዛ ዓርአያ ለጀርመኑ ካኒየን//ስራም Canyon//SRAM-zondacrypto Generation) የብስክሌት ቡድን ለሁለት ዓመት መፈረሟ ትናንት ይፋ ሆነ ። የ21 ዓመቷ ወጣት ብስክሌት ጋላቢ ትውልዷ ደቡባዊ ኤርትራ አዲ አኸሎ ውስጥ ነው ። የካኒየን//ስራም ቡድን ኃላፊ ጎሲያ ጃሲንካ፦ ወጣቷ የቡድናቸው አባል በመሆኗ እጅግ መደሰታቸውን ገልጠዋል ። ኃላፊዋ ሞናሊዛን ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኟት ርዋንዳ ኪጋሊ ከተማ ውስጥ በነበረው ተስፋ የሚጣልባቸው ሴት ብስክሌተኞች እና የዓለም ፉክክር ላይ መሆኑን ገልጠዋል ።
የኢትዮጵያና የኤርትራ ብስክሌት ጋላቢዎች በጀርመን ቡድን
ሞናሊዛ በቱር ደ ፍሯንስ የብስክሌት ግልቢያ ፉክክር ላይ የመጀመሪያው አፍሪቃዊ ብስክሌተኛ በመሆን ብቃቱን ያሳየው ሌላኛው ኤርትራዊ ጋላቢ ዳንኤል ተክለ-ሃይማኖት አርዓያዋ እንደሆነ ተናግራለች ። ወጣት ሞናሊዛ ለየካኒየን//ስራም ቡድን በሚቀጥለው የጎርጎሪዮሱ አዲስ ዓመት ተሰልፋ የምትፎካከር የመጀመሪያዋ ኤርትራዊ ብስክሌት ጋላቢ ናት ።
ከሞናሊዛ ቀደም ብሎ የ18 ዓመቷ ኢትዮጵያዊት ብስክሌት ጋላቢ ጽጌ ካህሣይ ኪሮስ ለጀርመኑ ካኒየን//ስራም ቡድን የሦስት ዓመት ውል መፈረሟ ይታወቃል ። ወጣቷ ለጀርመኑ ቡድን የፈረመችው ባለፈው መስከረም ወር መጀመሪያ ላይ ርዋንዳ ውስጥ በተከናወነው ተስፋ የሚጣልባቸው ሴት ብስክሌተኞች እና የዓለም ፉክክር ላይ ባሳየችው ብቃት መሆኑ ታውቋል ።
በወቅቱ ኪጋሊ ውስጥ በነበረው የአዳጊ ጋላቢዎች ፉክክር ሰባተኛ ደረጃ ማግኘቷ የሚታወስ ነው ። ጽጌ ለጀርመኑ ካኒየን//ስራም ቡድን (የፈረመችው ለሦስት ዓመታት ነው ። ወጣት ጽጌ ካህሣይን ወደፊት የስፖርት ክፍላችን እንግዳ ለማድረግ እንሞክራለን ። ካኒየን//ስራም እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2025 በቡድኑ ውስጥ ያካተታቸውሴት ብስክሌት ጋላቢዎች ከአውስትራሊያ እና ከዩናይትድ ስቴትስ ውጪ በአጠቃላይ ከ11 የአውሮጳ አአገራት የተውጣጡ ናቸው ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሠ
























