የጤና ባለሙያዎች “የሙያ ማህበራት እያገዙን” አይደለም አሉ
Description
የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች ተመጣጣኝ ደሞዝና ጥቅማጥቅም እንዲያገኙ በመጠየቅ ለጀመሩት የመገናኛ ዘዴዎች ዘመቻ የጤና ባለሙያዎች ማሕበራት «እያገዙን አይደሉም» በማለት ወቀሱ።ባለፈዉ ሚያዝያ 3 ቀን፣ 2017 የተጀመረው የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የጥያቄ ዘመቻ እስከፊታችን ግንቦት 3 ድረስ ይቀጥላል ተብሏል።ዘመቻዉን ከሚያደርጉት አንዳዶቹ እንደሚሉት ጫና፣ ዛቻና እንግልት ደርሶባቸዋል። ከመስሪያ ቤት እንዲዛወሩ የተደረጉም አሉ።እስካሁን ድረስ ከማሕበራት ድጋፍ አለማግኘታቸዉንም ገልጠዋልም።የጤና ባለሙያዎቹ ጥያቄዎቻችው እስከ ግንቦት 3/2017 ዓ ም ካለተመለሠ የሥራ ማቆም አድማ እንደሚምቱ አስጠንቅቀዋል፡፡
12 ጥያቄዎቻቸውንም እንዲመለሱላቸው ለጤና ሚኒሰቴር በደብዳቤ ማሰሳወቃቸውን የእንቅስቃሴው ደጋፊዎች ለዶይቼ ቬሌ መናገራቸው ተናግረዋል፡፡፡
በዚህ ሁሉ ሂደት ታዲያ የጤና ባለሙያዎቸ ማህበር እንቅስቃሴው እንዳይደረግ ከመከላከል የዘለለ ያደረገላቸው ድጋፍ እንደሌለ አንድ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኝ የመንግስት ሆስፒታል የሚሰሩ ሀኪም ገልፀዋል፡፡
“... እሰካሁን ከነሱ (ከጤና ማህበራት) መልካም ነገር እየጠበቅን ነው፣ እኛ የምንፈልገው፣ በማህበራት በኩል ወደላይ ቢገፉልን የበለጠ ተሰሚነት ይኖራል ብለን እንረዳለን እስካሁን ድረስ መልካም ነገር አላገኘንም” ብለዋል፡፡
“የሙያ ማሕበራት እንዳሉ አይቆጠሩም” ባለሙያዎች
ባሕር ዳር ክተማ ከሚገኙ በአንዱ በህክምና ሥራ ላይ ያሉ ባለሙያ በበኩላቸው የሙያ ማህበራት አሉ ለማለት እንደማይደፍሩ ጠቁመው፣ ቢኖሩም የጤና ባለሙያውን ችግር አሳመኖ የመፍታት አቅም እንደሌላቸው ነው ያመለከቱት፡፡ መፍትሔው ከየጤና ተቋማቱ ተወካዮችን መርጦ በመላክ ችግሩን በውይይት መፍታት ነው ነው ያሉት፡፡
አስተያየት ሰጪው አሁን እየተደረገ ያለው የማህበራዊ ሚዲያው ዘመቻ መሪ የሊለውና አስተባባሪዎችም ብግልፅ ስለማይታውቁ ንቅናቄው ውጤታማ የሆናል የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል፣ ጥያቄውም ሂደቱን ያልተከተለ፣ችኩልነት የታየበትም ሲሉ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡፡ኢትዮጵያ
“የባለሙያው ኑሮ እንዲሻሻል ጥረት እያደረግሁ ነው” የጤና ባለሙያዎች ማህበር
የኢትዮጰያ ጤና ባለሙያዎቸ ማህበር ፕረዚደንት ዮናታን ዳኛው በጉዳዩ ዙሪያ ተጠይቀው በሰጡት ምላሸ ማህበሩ ሰላማዊ ሰልፍና የሥራ ማቆም አድማ የመጥራት ኃላፊነት ባይኖርበትም የጤና ባለሙያዎቸ ያሉባቸው ችግሮች እንዲፈቱ እየሰራ እንደሆነ ገልጠዋል፡፡
እንደ ፕረዚደንቱ ካለፉት 2 ዓመታት ጀምሮ የባለሙያው ጥያቄ መፍትሔ እንዲያገኝ የጠቅላይ ሚኒሰትሩን ጽ/ቤትን ጨምሮ ለበርካታ ሚኒስቴር መስሪያቤቶችና ቢሮዎች ደብዳቤ ማስገባታቸውን ተናግረዋል፡፡
ድሬዳዋ የሚገኙ አንድ የህከመና ባለሙያ“የመብት ጥያቄ በማንሳቴ ከምሰራበት ሆሰፒታል ወደ ጤና ጣቢያ ወርጀ እንድስራ ተደርጌያለሁ” ሲሉ አመልክተዋል፡፡
ባለሙያው፣ “የዝውውር ደብዳቤው ከመፃፉ በፊት የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ስልክ በመደወል እንቅስቃሴውን እንዳቆም ዛቱብኝ፣ እንደማላቆም ስነግራቸው ከምሰራበት ሆስፒታል ወደ ጤና ጣቢያ እንደተዛወርኩ የሚያመለክት ደበዳቤ ደረሰኝ” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የባለሙያውን አቤቱታ በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጡን ለድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዩሱፍ ሰኢድ የእጅ ስልክ ብንደውልም “ስብሰባ ላይ ነኝ” በማለታቸው ሊሳካ አልቻለም፡፡
የኢትዮጰያ ጤና ባለሙያዎቸ ማህበር በሀኪሙ ላይ ተደረገው ዝውውር ተግቢ ባለመሆኑ ዝውውሩ ተሰርዞ ወደ ቀድሞ የሥራ ገበታቸውእንዲመለሱ ደበዳቤ መፃፉን የማህበሩ ፕረዚደንት ዮናታን ዳኛው ገልጠዋል፡፡
“ንቅናቄውን በኃይል ለማስቆም የሚደረገው ጥረት መፍትሔ አያመጣም” አስተያየት ሰጪዎች
ሆኖም የመብት ጥያቄ ለምን ጠየቃችሁ ብሎ በባለሙያዎቹ ላይ ጫና መፍጠር ነገሩን የባሰ አስቸጋሪ እንደሚያደርገው አንድ የጤና ባለሙያ ያስረዳሉ፡ኮሮና
ጤና ባለሙያዎች ትክክለኛ ጥያቄ ይዘው መነሳታቸውን የሚናገሩት እኚሁ ባለሙያ፣ መብቱን የሚጠይቅ አካል ማዋከብና መዛት፣ እርምጃ መውሰድ ነገሩን የበለጠ ያካርረዋል ነው ያሉት፣ ይልቁንም መንግስት ጥያቄው ትክክል ነው ወይስ አይደለም የሚለውን አይቶ መፍትሄ ማምጣት ነው ተገቢ የሚሆነው ብለዋል፡፡
ባለሙያዎቹ ጥያቄዎቻቸው እስከ ግንቦት 3/2017 ካልተመለሰ የሥራ ማቆም እንደሚያደርጉ ዝተዋል፣ የጤና ሚኒሰቴር የህዝብ ግንኙነትና የጤና ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ተገኔ ረጋሳ ሰሞኑን ለዶቼ ቬሌ እንደገለጡት የባለሙያዎቹ ጥያቄ በየደረጃው እንደሚፈታ አመልክተው፣ ባለሙያዎቹ የሥራ ማቆም አድማ ያደርጋሉ የሚል እምነት ግን እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ነጋሽ መሐመድ
ፀሐይ ጫኔ






















