የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር የሚመሩ ሹማምንት በዋሽንግተን ምን አሉ?
Description
የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር በግንባር ቀደምትነት የሚመሩ ሹማምንት ባለፈው ሣምንት በዋሽንግተን ዲሲ በተካሔደው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) እና የዓለም ባንክ ጣምራ የጸደይ ጉባኤ ሥራ በዝቶባቸው ሰንብቷል። ልዑካኑ ከአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት፣ ከሳዑዲ አረቢያ የልማት ፈንድ፣ ከዓለም አፉ የገንዘብ ድርጅት እና ከዓለም ባንክ ሹማምንት ተገናኝተው ስለ መንግሥታቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር እና አሳካ የሚሏቸውን ውጤቶች አስረድተዋል።
በዓለም ሰሜናዊ ንፍቀ-ክበብ ጸደይ ሲጠባ በየዓመቱ የሚካሔደው ስብሰባ የገንዘብ ሚኒስትሮች፣ የባንክ ገዥዎች፣ የግሉ ዘርፍ ተወካዮች እና ምሁራን ጭምር የሚሳተፉበት ነው። በስብሰባው የዓለም ኢኮኖሚ ይዞታ፣ ሥጋቶች፣ የፋይንስ መረጋጋት እና ድሕነት ቅነሳን የመሳሰሉ ጉዳዮች ይመከርባቸዋል።
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የሀገራትን እና ክፍለ-አኅጉራትን የኢኮኖሚ ዕድገት ትንበያ ይፋ የሚያደርግበት ጭምር ነው። የዘንድሮው ጉባኤ ከሚያዝያ 13-18 ቀን 2017 ሲካሔድ የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ፣ ምክትላቸው ኢዮብ ተካልኝ፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ እና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ ተክለወልድ አጥናፉን ያካተተ የኢትዮጵያ ልዑካን ተሳትፏል።
ኢትዮጵያ “ፈጣን እና ቁርጠኛ የፖሊሲ ማሻሻያዎች” ተግባራዊ ማድረግ እንደሚኖርባት በዓለም ባንክ አቅጣጫ የተሰጣት ከሁለት ዓመታት በፊት መቀመጫቸውን በዋሽንግተን ዲሲ ያደረጉት ሁለቱ ተቋማት የጋራ ጉባኤ ላይ ነበር። ሁለቱ ተቋማት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ወደ ሊብራል ሥርዓት ለማሻገር ተግባራዊ የሚያደርጋቸው መዋቅራዊ ማስተካከያ መርሐ-ግብሮችን የሚደግፉ ናቸው።
የኢትዮጵያ ልዑካን በስብሰባው ጎን ለጎን ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጂዮርጂየቫ እና የተቋሙ ባልደረቦች ተገናኝተው መንግሥታቸው ተግባራዊ ስለሚያደርገው የተራዘመ የብድር አቅርቦት መርሐ-ግብር ተነጋግረዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ የአይኤምኤፍ ሰዎች “በፕሮግራሙ አፈጻጸም እጅግ ደስተኛ ናቸው” ሲሉ ለሬውተርስ ተናግረዋል። በማሻሻያዎቹ የኢትዮጵያ መንግሥት ያሳካቸውን ውጤቶች “አስደሳች አስገራሚ” ብለው የገለጿቸው ኢዮብ በብሔራዊ ባንክ የውጪ ምንዛሪ ክምችት፣ የዋጋ ግሽበትን በመቀነስ እና በወጪ ንግድ ዕድገት ከታቀደው በላይ ውጤት መታየቱን ለሬውተርስ አስረድተዋል።
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባዘጋጀው ውይይት ላይ የተሳተፉት የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ መንግሥታቸው ተግባራዊ የሚያደርገውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ውጤታማነት ሲያስረዱ በማሳያነት ከጠቀሷቸው ጉዳዮች መካከል የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ለውጥ ያመጣው ውጤት ይገኝበታል።
የብሔራዊ ባንክ ገዥ “የማሻሻያው ውጤት ከጠበቅንው በላይ ነው። ለምሳሌ ያክል የውጪ ምንዛሪ አቅርቦት በከፍተኛ መጠን ጨምሯል። የውጪ ንግድ በዚህ ዓመት ቢያንስ በ100 ፐርሰንት ያድጋል። ሐዋላ ቢያንስ በ25 ፐርሰንት ይጨምራል” ሲሉ ተደምጠዋል።
ማሞ የሚመሩት ብሔራዊ ባንክ ጥብቅ ቁጥጥር ያደርግበት ከነበረው የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት እጁን ሲያወጣ ብር ከዶላር አኳያ ያለው የምንዛሪ ተመን በከፍተኛ መጠን ወድቋል። ውሳኔው ገቢራዊ ከመሆኑ በፊት በሐምሌ 2016 በባንኮች 58 ብር ከ50 ሣንቲም ይሸጥ የነበረው የአንድ ዶላር አማካኝ ዕለታዊ የምንዛሪ ተመን ዛሬ ሚያዝያ 22 ቀን 2017 በብሔራዊ ባንክ መረጃ መሠረት ወደ 131 ብር ከ56 ሣንቲም ገደማ ደርሷል።
የብርን የመግዛት አቅም ያዳከመው የግብይት ሥርዓት ለውጥ የሠራተኞችን ደመወዝ እና የኢትዮጵያውያንን ተቀማጭ በኃይል ያኮሰመነ ነው። እንዲያም ሆኖ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ በተለይ ሀገሪቱን ጠፍሮ ለያዘው የውጪ ምንዛሪ እጥረት መፍትሔ እንዳበጀ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በተሰናዳው መድረክ ላይ ተናግረዋል።
“ከማሻሻያው በፊት ከተጋፈጥናቸው ብርቱ ችግሮች አንዱ የውጪ ምንዛሪ ክምችት መመናመን ነበር” ያሉት ማሞ “ከማሻሻያው በኋላ የውጪ ምንዛሪ ክምችታችን በሦስት እጥፍ ጨምሯል። በባንክ ሥርዓቱ ውስጥ ያለው የውጪ ምንዛሪ ክምችት ሁለት እጥፍ አድጓል” ሲሉ ተናግረዋል።
ማሞ በ2017 የበጀት ዓመት ብሔራዊ ባንክ ለገንዘብ ሚኒስቴር ምንም ዐይነት የቀጥታ ብድር ሳይሰጥ ለማጠናቀቅ መታቀዱን አስረድተዋል። ይህ ከተሳካ ማሞ እንዳሉት “ከ12 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ” ይሆናል። የብሔራዊ ባንክ ገዥ በጥር 2016 ተግራዊ መሆን የጀመረው የገንዘብ ፖሊሲ የኢትዮጵያ “ማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋት መሠረታዊ ምንጭ” ባሉት የዋጋ ግሽበት ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንዳመጣ ተናግረዋል።
“በኢትዮጵያ ላለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት የዋጋ ግሽበት 30 በመቶ ገደማ ሆኖ ቆይቷል። ተግባራዊ እያደረግን በምንገኘው ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ምክንያት የዋጋ ግሽበትን ከ30 በመቶ በመጋቢት ወደ 13 በመቶ መቀነስ ችለናል” ያሉት አቶ ማሞ ምኅረቱ በ2018 “የዋጋ ግሽበት 10 በመቶ ይደርሳል የሚል ተስፋ አለን። ይህን ካሳካን በ10 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሆናል” ሲሉ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት መሠረታዊ የፖሊሲ እና የሕግ ለውጦች የሚያካትተውን ማሻሻያ ተግባራዊ እያደረገ የሚገኘው ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና ከዓለም ባንክ በሚያገኛቸው ብድሮች እና ድጎማዎች አማካኝነት ነው። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የተራዘመ የብድር አቅርቦት በተባለ መርሐ-ግብር ብቻ እስከ ጎርጎሮሳዊው 2028 ባሉት ዓመታት ለኢትዮጵያ 3.4 ቢሊዮን ዶላር ያበድራል።
በዚህ ሣምንት ማዕቀፉ ሦስተኛ ግምገማ የመጀመሪያ ደረጃ ሥምምነት ላይ ይደረሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ ለሬውተርስ ተናግረዋል። ሦስተኛው ግምገማ ኢዮብ እንዳሉት በሰኔ ወር በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ከጸደቀ የኢትዮጵያ መንግሥት ከተፈቀደለት ብድር ውስጥ ቀጣይ ክፍያ ይለቀቅለታል። ድርጅቱ ለኢትዮጵያ ከሚያበድረው የገንዘብ መጠን ውስጥ ከመጀመሪያው ግምገማ በኋላ 345 ሚሊዮን ዶላር ገደማ፤ ከሁለተኛው ግምገማ በኋላ 250 ሚሊዮን ዶላር ለዐቢይ መንግሥት ለቋል።
የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በኢኮኖሚ ማሻሻያው ፍሬዎች ደስተኛ ቢሆኑም ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሀገሪቱ አሁንም “የውጪ ምንዛሪ እጥረት” እና “የገቢ ንግድ ገደብ” ካለባቸው በርካታ የአፍሪካ ሀገራት አንዷ መሆኗን አስታውቋል። አይኤምኤፍ የአፍሪካ ሀገራትን የኢኮኖሚ ዕድገት ትንበያ ይፋ ባደረገበት ሠነድ በኢትዮጵያ “ማኅበራዊ ውጥረት” መኖሩን አስቀምጧል። የአፍሪካ ሀገራት የሚኖርባቸውን ሥጋት በዘረዘረበት የሰነዱ ክፍል በኢትዮጵያ “የሰላም ሥምምነት” ቢኖርም “ተጨማሪ ግጭት የመቀስቀሱ ዕድል ከፍ ያለ” እንደሆነ አስታውቋል።
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በጎርጎሮሳዊው 2025 ከሰሐራ በታች የሚገኙ ሀገራት 4 በመቶ ኢትዮጵያ ደግሞ 6.6 በመቶ ያድጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቋል። መቀመጫውን በዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው አበዳሪ ተቋም ሰነድ እንደሚለው በጎርጎሮሳዊው 2025 የኢትዮጵያ መንግሥት ዕዳ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት (GDP) አኳያ ወደ 28.6 በመቶ ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል። በተያዘው ዓመት ከኢትዮጵያ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት የመንግሥት ዕዳ 30.5 በመቶ ድርሻ አለው።
ኢትዮጵያ የምትገኝበት ቀጠና በተለይ በኢኮኖሚ ረገድ ባለፉት ዓመታት ከገጠመው መቀዛቀዝ የማንሠራራት አዝማሚያ ቢያሳይም በርካታ ሀገራት የገንዘብ እጥረት፣ ከፍተኛ የብድር ወለድ እና የዕዳ ተጋላጭነት እንደበረታባቸው አትቷል። በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የአፍሪካ ክፍል ዳይሬክተር አበበ አዕምሮ ሥላሴ የአፍሪካ መንግሥታት ያከናወኗቸው አንገብጋቢ የመሠረተ-ልማት ግንባታዎች አትራፊ ሆነው ገቢያቸውን በግብር መልክ ማሳደግ አለመቻላቸው ለዕዳ ጫና መበርታት ዋንኛው ገፊ ምክንያት እንደሆነ አስረድተዋል።
“የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅምን በማሳደግ፣ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን በማስፋፋት እና በርካታ መንገዶች በመገንባት ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ ቢደረግም የዚህ ሁሉ ኢንቨስትመንት ትርፍ በግብር ገቢ መልክ አልተገኘም” ያሉት አበበ አዕምሮ ሥላሴ “ብድር እና የዕዳ ወለድ ከገቢ አኳያ ያለው ምጣኔ እንዲጨምር አድርጓል። ይህ የበርካታ ኢኮኖሚዎች ቁልፍ የተጋላጭነት መነሾ ሲሆን የተወሰኑ ሀገራት የዕዳ ፈተና ውስጥ ገብተው የአከፋፈል ማሻሻያ እንዲፈልጉ አድርጓቸዋል” በማለት አብራርተዋል።
በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የ2025 የኢኮኖሚ ዕድገት ትንበያ ሠነድ መሠረት ከሰሐራ በርሐ በታች ከሚገኙ 35 ሀገራት መካከል 19ኙ በዕዳ ጫና ውስጥ ወድቀዋል አሊያም ዕዳ ጫና ውስጥ የመግባት ከፍተኛ ሥጋት አለባቸው። መንግሥታት ወጪን በመቀነስ ከችግሩ ለማምለጥ ከዚህ ቀደም የሚያደርጉት ሙከራ “ለልማት እና ለዕድገት እንቅፋት መሆኑን በተደጋጋሚ” መረጋገጡን አበበ ገልጸዋል።
“በ1980ዎቹ ተሞክሮ እጅግ አስቸጋሪ፣ ፈታኝ እና የዕድገት ማነቆ” ሆኖ የተገኘውን የወጪ ቅነሳ የአፍሪካ ሀገራት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እንደማይመክር ጠቁመው ብድርም ቢሆን አዋጪ አማራጭ እንደማይሆን ተናግረዋል። የቀረው ገቢን የማሳደግ አማራጭ ነው።
የዓለም አአፉ የገንዘብ ድርጅት የአፍሪካ ክፍል ኃላፊ “ይህ ማለት ገቢን ማሳደግ ቀላል ነው ማለት አይደለም። እጅግ ከባድ ነው” ሲሉ በአጽንዖት ገልጸዋል። የአፍሪካ መንግሥታት ገቢያቸውን ማሳደግ ከፈለጉ “ፖለቲካዊ ውይይት ብቻ ሳይሆን በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ያለውን ማኅበራዊ ውል ለማጠናከር ሊሰብሰብ የታቀደው ገቢ ለትክክለኛው ዓላማ እንደሚውል ማስረዳት ያስፈልጋል” ሲሉ መክረዋል።
ከፍተኛ ብድር ካለባቸው የአፍሪካ ሀገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ በአንድ በኩል የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ እየጠበቀች በሌላ በኩል ለመሠረተ-ልማት ግንባታዎች አማራጭ የገንዘብ ምንጭ እያፈላለገች ይመስላል። የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ኢዮብ ተካልኝ መንግሥታቸው ከቻይና የንግድ ባንኮች ጋር ንግግር እያደረገ እንደሚገኝ ለሬውተርስ አረጋግጠዋል። ለአዲስ አበባ ቀላል ባቡር እና ለአውሮፕላን ማረፊያ ማስፋፊያ የታቀደውን ገንዘብ ከቻይና የወጪ እና ገቢ ንግድ ባንክ እና ከቻይና ልማት ባንክ ለመበደር ውይይት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ለሬውተርስ ተናግረዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ከዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን (DFC) ኃላፊዎች ጋር ጭምር ንግግር አድርገዋል። “ትኩረት ከሚሰጧቸው ቀዳሚ ሀገሮች” አንዷ ኢትዮጵያ ናት የሚል ዕምነት ያላቸው ኢዮብ ሀገራቸው ከአሜሪካ “ተጨማሪ ኢንቨስትመንት” እንድታገኝ ይፈልጋሉ።
የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት አዳዲስ የፋይናንስ አማራጭ በትጋት ማፈላለግ የያዙት ሀገሪቱ ከዚህ ቀደም የተበደረችውን ለመክፈል ተቸግራ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ለማድረግ በተዘጋጀችበት ወቅት ነው። በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ በኩል ከጫፍ የደረሰው የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ በመጪዎቹ ወራት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። ሽግሽጉ ተግባራዊ ሲሆን እስከ ጎርጎሮሳዊው 2028 ባሉት ዓመታት ብቻ ኢትዮጵያ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ከዕዳ ክፍያ ታድናለች።
ይሁንና የቦንድ ባለቤት ከሆኑ የግል አበዳሪዎች ጋር የሚደረገው ድርድር ገና ፈር አልያዘም። በአቶ አሕመድ ሽዴ የተመራው ልዑካን ቡድን ከቦንድ ባለቤቶች ጋር ተገናኝቶ መወያየቱን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል። የቦንድ ባለቤቶች በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የሚዘጋጀውን የኢትዮጵያ የዕዳ ትንተና እየተጠባበቁ በመሆናቸው በአከፋፈል ረገድ ተጨባጭ ውይይት መጀመር እንዳልተቻለ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ለሬውተርስ ተናግረዋል። ከቦንድ ባለቤቶች ጋር የተደረገው ውይይት ውጤታማ እንደሆነ የገለጹት ኢዮብ በአከፋፈል ረገድ መደበኛ ድርድር በመጪዎቹ ወራት ሊጀመር እንደሚችል ጥቆማ ሰጥተዋል።
አርታኢ ፀሀይ ጫኔ

























