ኢትዮጵያ ለቢሊዮን ዶላር ዕዳ ሽግሽግ ከቦንድ ባለቤቶች ጋር የሚደረገውን ውይይት ውጤት እየጠበቀች ነው
Description
የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ሀገሪቱ አንድ ቢሊዮን ዶላር የተበደረችበት ቦንድ ባለቤት ከሆኑ የተወሰኑ ባለወረቶች ጋር በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ በዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ላይ ውይይት ማድረግ ጀምረዋል። ሁለቱ ወገኖች በሚወያዩበት ጉዳይ ላይ መረጃ አሳልፎ ከመስጠት የሚከለክል ሥምምነት መፈራረማቸውን ብሎምበርግ እና ሬውተርስ ዘግበዋል።
በውይይቱ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሳሉ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ላይ የተደረጉ ድርድሮችን ሲመሩ የቆዩት የብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ ይሳተፋሉ። ከቦንድ ባለቤቶች ጋር የተወሰኑ ስብሰባዎች እንደሚካሔዱ ለሬውተርስ ያረጋገጡ የገንዘብ ሚኒስቴር ባለሥልጣን ሁለቱ ወገኖች ሥምምነት ላይ ሳይደርሱ ሊቀሩ እንደሚችሉ ገልጸዋል። እዮብ ወደ ፈረንሳይ ያቀኑት የብሔራዊ ባንክ ገዥ ሆነው ከተሾሙ በኋላ ዕዳ ሽግሽግ ላይ ለመወያየት ወደ ቻይና በተጓዙ በጥቂት ቀናት ልዩነት ውስጥ ነው።
መንግሥት ከግል አበዳሪዎቹ ጋር የሚደረገውን ድርድር በታኅሳስ ይካሔዳል ተብሎ ከሚጠበቀው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) የተራዘመ የብድር አቅርቦት አራተኛ ግምገማ በፊት ማጠናቀቅ እንደሚፈልግ የፕራግማ ኢንቨስትመንት አድቫይዘሪ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መርዕድ ብሥራት ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመሪያ የሆነውን በ10 ዓመታት የሚጎመራ ቦንድ በ6.625 በመቶ ወለድ በዓለም ገበያ ሸጣ አንድ ቢሊዮን ዶላር የተበደረችው ኃይለማርያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳሉ በ2007 ነበር። መንግሥት በታኅሳስ 2016 ለቦንድ ባለቤቶች 33 ሚሊዮን ዶላር ወለድ ሳይከፍል ቀርቷል።
ዋናው ብድር ተመልሶ የሚከፈልበት ጊዜ ባለፈው ዓመት ያበቃ ሲሆን ይህ በግል አበዳሪዎች እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል እየተካሔደ በሚገኘው ድርድር ላይ ተጽዕኖ እንዳለው አቶ መርዕድ አስረድተዋል። ብላክ ሮክ እና ጄፒ ሞርጋንን የመሳሰሉ የአሜሪካ የኢንቨስትመንት ተቋማት እና የጡረታ ፈንዶች ከቦንዱ ባለቤቶች መካከል ይገኙበታል።
እነዚህ የቦንድ ባለቤቶች “ዋናውን አንድ ቢሊዮን ዶላር ብድር እንዴት ትከፍሉናላችሁ? የሚሸጋሸግ ከሆነ በስንት ወለድ ነው? እስከ ምን ያህል ጊዜ?” የሚሉ ጥያቄዎች በፓሪስ በሚደረገው ውይይት አጀንዳ እንደሚሆኑ የፕራግማ ኢንቨስትመንት አድቫይዘሪ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከዋናው አንድ ቢሊዮን ዶላር ከ18 እስከ 20 በመቶ እንዲቀነስ ከዚህ ቀደም ያቀረበውን ምክረ-ሐሳብ የቦንድ ባለቤቶች አልተቀበሉም። ገንዘብ ሚኒስቴር እና የግል አበዳሪዎች ኢትዮጵያ የገጠማት የዕዳ ጫና የመክፈያ ጊዜ በማራዘም የሚፈታ የአጭር ጊዜ የገንዘብ እጥረት ወይስ ብድር ለመቀነስ የሚያስገድድ የመክፈል ችግር በሚለው ረገድ ልዩነት አላቸው።
ከኢትዮጵያ የግል አበዳሪዎች ጋር የሚደረገው ውይይት እስከ መቼ ሊቆይ እንደሚችል ዶይቼ ቬለ ከገንዘብ ሚኒስቴር እና የቦንድ ባለቤቶችን ከሚወክሉ የኢንቨስትመንት ድርጅቶች ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።
የዕዳ ሽግሽግ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ተግባራዊ የሚያደርገው የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር አንድ ዓላባ ነው። ገንዘብ ሚኒስቴር በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ የዕዳ ሽግሽግ ከኢትዮጵያ ኦፊሴያል አበዳሪዎች ጋር የመግባቢያ ሰነድ ሥምምነት ላይ መድረሱን ይፋ ያደረገው ሰኔ 25 ቀን 2017 ነበር።
በቻይና እና በፈረንሳይ ተባባሪ ሊቀ-መንበርነት ከሚመራው የአዳሪዎች ኮሚቴ ጋር የተደረሰው ሥምምነት የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የተራዘመ የብድር አቅርቦት መርሐ ግብር ተግባራዊ በሚደረግባቸው ዓመታት ለኢትዮጵያ 3.5 ቢሊዮን ዶላር ከዕዳ ክፍያ ያድናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል። የመግባቢያ ሥምምነቱ ባለፈው ሰኔ ቢፈረምም ተግባራዊ የሚሆነው “ከእያንዳንዱ የኮሚቴው አባላት ጋር በሚደረጉ የሁለትዮሽ ስምምነቶች አማካኝነት” ነው።
ኢትዮጵያ በጎርጎሮሳዊው እስከ ሰኔ 2028 ድረስ የሚዘልቅ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረችው አቶ መርዕድ እንደሚሉት “በእነዚህ አራት ዓመታት ውስጥ ያላትን የውጪ ምንዛሪ ማክሮ ኢኮኖሚ መዛነፍ በሙሉ አርማ በዓለም ገበያ የምትሸጠው ሸቀጥ እና አገልግሎት ጨምሮ ቢያንስ [ብድር] የመክፈል አቅሟ ከፍ ይላል” በሚል ዕሳቤ ነው።
የወጪ ንግድን ለማበረታታት ብርን በኃይል ያዳከመ የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ተግባራዊ የሆነበትን የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የተራዘመ የብድር አቅርቦት መርሐ-ግብር ከመጀመሯ በፊት ኢትዮጵያ ያለፉትን ዓመታት ከፍተኛ የዕዳ ጫና ያለባት ሀገር ሆና ቆይታለች። ሀገሪቱ 33 ቢሊዮን ዶላር የውጪ ዕዳ አለባት።
በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት 3.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር የሚደጎመው የኢኮኖሚ ማሻሻያ በሐምሌ 2016 ተግባራዊ ሲሆን ከዚህ ቀደም ቀፍድዶ የያዛት የውጪ ምንዛሪ እጥረት መሻሻል ማሳየቱን የመንግሥት ሪፖርቶች አሳይተዋል።
ከወጪ ንግድ እና ከሐዋላ የምታገኘው ገቢ ዕድገት አሳይቶ የሀገሪቱ የውጪ ምንዛሪ ክምችት ከፍ ቢልም ዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በቅርቡ ይፋ ያደረጉት የዕዳ ትንተና ኢትዮጵያ አሁንም የዕዳ ጫና ውስጥ እንደምትገኝ አስጠንቅቋል። ሰነዱ እንደሚለው ሀገሪቱ ያለባት የውጪ ዕዳ ዘላቂ አይደለም።
የኢትዮጵያ “የውጪ ዕዳ ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) አኳያ ሲታይ ዝቅተኛ ነው” የሚሉት አቶ መርዕድ ብድር መክፈል አቅሟ በዓለም ገበያ ከምትሸጠው ሸቀጥ እና አገልግሎት አንጻር ስምንት ቢሊዮን ዶላር ገደማ ብቻ በመሆኑ ጫና ውስጥ እንደከተታት አስረድተዋል። “ብድር የመክፈል አቅሟ አሁንም በዓለም ገበያ ከምትሸጠው ሸቀጥ እና አገልግሎት አኳያ መጨመር አለበት” ሲሉ ተናግረዋል።
የዕዳ ክፍያ ከኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ያለው ምጣኔ በሚቀጥለው ዓመት ብቻ 36.6% ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ የዕዳ ትንተና ሰነድ ያሳያል። ኢትዮጵያ የዕዳ ክፍያ እፎይታ ባገኘችበት በጎርጎሮሳዊው 2025 ምጣኔው 5.6% ብቻ ነበር።
በጎርጎሮሳዊው 2027 ወደ 15.3% ዝቅ ይላል ተብሎ የሚጠበቀው የዕዳ ክፍያ ከወጪ ንግድ ያለው ምጣኔ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ብድር የሚደጎመው የኢኮኖሚ ማሻሻያ በሚጠናቀቅበት የጎርጎሮሳዊው 2028 በአንጻሩ ወደ 15.9% ይደርሳል።
ኢትዮጵያ ከአበዳሪዎቿ በሚደረግላት የብድር አከፋፈል ሽግሽግ ያለባት የዕዳ ጫና መካከለኛ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ለመንግሥት ቢያንስ ከሁለት ዓመታት በላይ የክፍያ ፋታ የሚሰጠው ሽግሽግ ሲያበቃ ግን ሀገሪቱ ዕዳዋን መክፈል አለባት። ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ መንግሥት በዓለም ገበያ ቦንድ በመሸጥ ዳግም የመበደር ፍላጎት ካለው ድርድር ላይ የሚገኘውን አንድ ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ከፍሎ ተዓማኒነት ማግኘት አለበት።
በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የዕዳ ሽግሽግ ሒደቱ በቶሎ እንዲያልቅ ፍላጎት መኖሩን ያስረዱት የፕራግማ ኢንቨስትመንት አድቫይዘሪ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መርዕድ ብሥራት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሲመረቅ ይፋ ያደረጓቸው ዕቅዶች የኢኮኖሚ ማሻሻያው ከተጠናቀቀም በኋላ ቢሆን ብድር እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል።
የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር ተግባራዊ በሚደረግባቸው ዓመታት ውስጥ ብቻ መንግሥት ለሚያከናውናቸው ሥራዎች ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያስፈልገዋል ተብሎ እንደሚገመት የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ የዕዳ ትንተና ሰነድ ያሳያል። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት 3.4 ቢሊዮን ዶላር ሲያበድር ዓለም ባንክ 3.8 ቢሊዮን ዶላር የበጀት ድጋፍ ያደርጋል። የተቀረው 3.6 ቢሊዮን ዶላር የዕዳ ሽግሽግ በሚሰጠው እፎይታ የሚሸፈን ነው።
የኢትዮጵያን የዕዳ ጫና ያቃልላል ተብሎ የሚጠበቀው የኢኮኖሚ ማሻሻያ በፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ጫናዎች ምክንያት መንግሥት ተግባራዊ የሚያደርጋቸው ፖሊሲዎች ሊቀለበሱ አሊያም ሊዘገዩ እንደሚችሉ ዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሥጋት አላቸው።
የሀገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች በመሠረታዊ ሸቀጦች እጥረት፣ የዋጋ ጭማሪ እና በብር መዳከም ምክንያት በሚከሰት የዋጋ ግሽበት ማኅበራዊ አለመረጋጋት ሊያመጣ ይችላል። የሀገሪቱ የጸጥታ ቀውስ ይበልጥ ካሽቆለቆለ ኢኮኖሚውን የበለጠ ሊረብሽ እና ዓለም አቀፍ ድጋፍ ሊያሳጣ እንደሚችል ሁለቱ ተቋማት ሥጋታቸውን ገልጸዋል።
አርታዒ ነጋሽ መሐመድ






















