ግብጽ እና ኢትዮጵያ በዚህ ሰሞን ያደረጉት የቃላት ምልልስ
Description
ግብፅ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ መመረቁን ተከትሎ አንድም ከውኃ ክፍፍል፣ በሌላ በኩል ከጎርፍ አደጋ ጋር የተያያዙ ሃሳቦችን በማንሳት በኢትዮጵያ ላይ ተደጋጋሚ ክስ ከማቅረቧ ባለፈ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ሰሞኑን ሀገራቸው "ጥቅሟን እና የውኃ ደህንነቷን ለማስጠበቅ አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ እንደምትወስድ" መግለጻቸው ተሰምቷል።
ኢትዮጵያ በውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በኩል በሰጠችው ምላሽ "ጠብ አጫሪ" ያለችው የግብጽ አካሄድ በኢትዮጵያ ላይ ያላትን የጥላቻ ንግግር የማጠናከሯ ማሳያ አድርጋ መግለጫውን ውድቅ አድርጋለች። ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ "የግብፅ የቅኝ ግዛት ወቅት አስተሳሰብ ትብብርን ከማጠናከር ይልቅ ሀገሪቱ በኢትዮጵያ ላይ የተሳሳተ ፖሊሲ እንድትከተል አድርጓል" ሲል ይወቅሳል።
በዚህ ላይ የተሰጠ የውኃ መሃንዲስ መምህር አስተያየት ዶክተር በለጠ ብርሃኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውኃ ምህንድስና መምህር ናቸው። የዓባይ ውኃን መነሻ ያደረገው የሁለቱ ሀገራት ምልልስ ግንኙነታቸውን ወዴት ይመራው ይሆን ብለን ጠይቀናቸዋል። መምህሩ "ግንኙነታቸው ባለበት ይቀጥላል" ሲሉ መልሰዋል።
"እነዚህ ሁለት ሀገራትኢትዮጵያ እና ግብጽ ውኃው የሚያስተሳስራቸው፣ ሁል ጊዜም የሚገናኙ፣ የሚነጋገሩ፣ መሆናቸው አይቀርምና ግንኙነታቸው ይቀጥላል ብለን እናምናለን" ሲሉ ዓለም አቀፍ መርሆዎች እና ማዕቀፎች በውኃ "ተስማምቶ የመልማት እና የመጠቀም ሂደትን" የሚያበረታቱ ናቸው ብለዋል።
"እንዲህ አይነቱ ምልልስ መቼ ሊቆም ይችላል?"
"እንደዚህ አይነት ንግግሮች [መግለጫዎች] ሁሌም አሉ። ሀገራቱ ለውስጣዊ ፍጆታቸው የሚሆን ንግግር እንጂ በወሰን ተሻጋሪ ውኃ ጉዳይ ላይ የሚሆን ንግግር አይደለም። አንድና አንድ መድረክ ነው የውኃ ጉዳይ ያለው። ድርድር ነው። በሰላም ማስፈፀም ነው ያለው እና የትብብር መስክ ላይ ይገባሉ ብለን እናምናለን።"
"የውኃ ክፍፍል የሚባል መርህ አለ?"
"መርሁ አለ። አጠቃላይ መርሁ ጉልህ የሆነ ተጽዕኖ ሳያደርሱ [በሌላው ላይ] ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም ማምጣት ነው። ይህን ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም ለመዘርጋት ሀገራት የሚኖርባቸው ሂደት ድርድር ነው። በቁጥር መወሰን ሊኖር ይችላል፣ በጥቅሙ ላይ መወሰን ሊሆን ይችላል፣ በተለያየ መልኩ ውኃን የመጠቀም መብት ማስፈን ይቻላላ። መርሁ አለ። መርሁ ብቻም ሳይሆን መንገዶችም አሉ።" ሲሉ መልሰዋል።
"ውኃ ምን ያህል የግጭት መነሻ፤ ወይስ የልማትና የትብብር መሣሪያ ነው?"
የውኃ ምህንድስና መምህሩ እንደሚሉት "እስካሁን ባለው ሁላችንም እንደምናውቀው በውኃ ምክንያት ጦር የተማዘዘ የለም። በዲፕሎምልሲ ጠንካራ የሆኑ ሀሳቦች ለመሸናነፍ፣ ድርድሮች፣ ክርክሮች ይኖራሉ። ከዚያም በኋላ ደግሞ አንዱ በተረዳው መጠን ውጤታማ ይሆናሉ። ስለዚህ [የውኃ ሀብቶች] የልማት፣ የትብብር፣ አብሮ የማደግ መንፈስ እንጂ የግጭት መንፈስ የላቸውም።
ያለንበት ዘመን አንድ ሀገር አንዱን ሀገር ወርሮ የሚያስገብርበት ዘመን አይደለም። ስለዚህ የሚኖረን መንገድ የግጭት ሳይሆን የትብብር መንገድ ነው።"
የውኃ ደህንነት "ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም" ማለት ነው - ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ ውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ግብጽ በዓባይ ወንዝ ውኃም ሆነ በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ባለው የሦስትዮሽ ድርድር "በቅን ልቦና ተወያይታ አታውቅም" ብሏል። የሌሎችን የተፋሰሱ ሀገራትን ፍላጎትና መብት በመዘንጋትም ከቅኝ ግዛት ዘመን የመነጨ ያለውን የ “ታሪካዊ መብት” ጥያቄን ለመጫን ጥረቷን ቀጥላለች ሲል የኢትዮጵያን አቋም ግልጽ አድርጓል።
የውኃ ደህንነት በሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት የወንዙ "ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም ማለት ብቻ ነውም" ብሏል።
ኢትዮጵያ ያልተገባ መግለጫ ከማውጣት ይልቅ ከግብፅ ጋር ዲፕሎማሲያዊ እና የወዳጅነት የግንኙነት መንገዶችን መምረጧን ቀጥላለች ያለው ሚኒስቴሩ በዓባይ ውኃ የመጠቀም መብቷን ግን አሳልፋ እንደማትሰጥ ጠቅሷል።
ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
ታምራት ዲንሳ