ማሕደረ ዜና፣ የኢትዮጵያ-ኤርትራ ምድር ሌላ ጦርነት እየተደገሰለት ይሆን?
Description
የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥትና ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ፕሪቶሪያ-ደቡብ አፍሪቃ ላይ ግጭትን የማቆም ስምምነት ከተፈራረሙ ባለፈዉ ጥቅምት 23 ሶስኛ ዓመቱን ደፈነ።በሁለት ዓመቱ ጦርነት ለተጎዳዉ ህዝብም ሆነ አስከፊዉን እልቂት ለታዘበዉ ሰላም ወዳድ ወገን ጦርነቱ የቆመበት 3ኛ ዓመት ሙታን የሚዘከበሩበት፣የሥምምነቱ ገበራዊነቱ የሚገመገምበት፣ አሳዛኙ ጥፋት እንዳይደገም፣ለሰላም ፅናት ቃል የሚገባበት በሆነ ነበር።አልሆነም።በተቃራኒዉ የዛሬ ሶስት ዓመት አንድ የነበሩት ኃይላት ሁለትም፣ ሶስትም ሆነዉ ሌላም ጨምረዉ ለመከረኛዉ ሕዝብ የዳግም ግጭት፣ጦርነት ሥጋት፣ ዉንጀላ ዛቻና አፀፋ ዛቻ ሲግቱት ሳምንቱ በሳምንት ተተካ።ከእንግዲሕስ? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።
የሰመራ-መቀሌ፣ የስምረት-ህወሓት መወነጃጀል
ጥቅምት 26፣2018 የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባወጣዉ መግለጫ «ከጥፋቱ የማይማር» እና «ጉጅሌ» ያለዉ ህወሓት በአፋር ክልል ዞን ሁለት የሚገኙ 6 መንደሮችን ወርሮ «በሰላማዊ ሰዎች ላይ «የተለመደ የሽብር ተግባሩን በግልፅ ጀምሯል» ይላል።
ዴሞክራሲያዊ ሥምረት ትግራይ (ስምረት-ባጭሩ) ጥቅምት 28 የአፋር ክልልን ወቀሳ የሚያጠናክር መግለጫ አዉጥቷል።የቀድሞዉን የትግራይ ክልል ጊዚያዊ ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸዉ ረዳን ጨምሮ ከህወሓት የተለዩት የትግራይ ፖለቲከኞች የመሠረቱት ስምረት፣ ህወሓትን «አጥፍቶ ጠፊ፣ ከሻዕብያ ጋር ፅምዶ የሚል ጥምረት የመሠረተና «ኋላ ቀር» በማለት ያራክሰዋል።
የስምረት መግለጫ እንደሚለዉ የህወሓት ታጣቂዎች አፋር ክልል ብቻ ሳይሆን እዚያዉ ትግራይ ዉስጥ በዓዲ ወጅራት እና በራያ ዓዘቦ ወረዳዎች በሚገኘዉ የትግራይ የሰላም የሰላም ኃይል ላይ ጥቃት ሰንዝረዋልም።
የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደርባወጣዉ አፀፋ መግለጫ ግን በሁለቱ መግለጫዎች ደረሱ የተባሉትን ጥቃቶች አይቀበልም።የጊዚያዊ አስተዳደሩ መግለጫ «ትግራይን ለማወክና እርስበርስ ለማዳማት ሆን ተብሎ በአፋር ክልል፣ ታጣቂዎች እንዲደራጁና እንዲታጠቁ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር፣ በመደገፍና ተልዕኮ በመስጠት በትግራይ ላይ ተደጋጋሚ የጠብ አጫርነት ተግባር ሲፈፅም ቆይቷል።አሁንም እያካሔደ ነዉ።» ይላል።
የአፋር መሬት የኃይል መፈታተሻ ወይስ የዕለታዊ ግጭት ሥፍራ?
በተቃራኒ መግለጫዎቹ የተጠቀሱትወረራ፣ ግጭቶች ወይም ጥቃቶች ሥላደረሱት ጉዳት እስካሁን ድረስ አንዳቸዉም በዝርዝር የገለፁት ነገር የለም።ይሁንና ሶስቱም መገለጫዎች እንዳሉት አንዳዴ የትግራይ ኃይል፣ ብዙ ጊዜ የትግራይ መከላከያ ኃይል (TDF) ተብሎ የሚጠራዉ የህወሓት ታጣቂ ቡድንና ከቡድኑ አፈንግጦ የትግራይ ሠላማዊ ኃይል (TPF) በሚል ሥም የተደራጀዉ ወገን በተለያየ ጊዜ አንዳቸዉ ሌላቸዉን ማጥቃታቸዉን ወይም መጋጨ,ታቸዉን ሶስቱም መግለጫዎች ያረጋግጣሉ።
ደራሲና የፖለቲካ ተንታኝ ዩሱፍ ያሲን የሁለት ፍንካቾች ግጭት በአፋር መሬት ይላሉ።
«ጦርነቱ በሁለቱ የTDF ፍንካቾች መካከል በአፋር መሬት፣ እነሱ ሐራ መሬት፣ እነ ጌታቸዉ እነ ፃድቃን ሐራ መሬት የሚሉት-----እነሱ እዚያ ራሳቸዉን በመዳራጀት ላይ ሥለሆኑ በዚያ ምክንያት ደግሞ እነሱ የሚቃወሟቸዉ ኃይሎች እስከ አፋር ዘልቀዉ የሚያደርጉት ጦርነት ነዉ ወይ ነዉ።ይሕ ግልፅ መሆን አለበት።»
የህወሓት አዲስ ክስ በፌደራዊዉ መንግሥት ላይ
ጦርነት ይሁን የዕለት ግጭት ዓላማዉ በርግጥ ግልፅ አልሆነም።ባለፈዉ አርብ ከቀትር በኋላ ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ያወጣዉ መግለጫ በመወቃቀስ፣ መወነጃጀሉ የኢትዮጵያ ፌደራዊ መንግሥትንም በግልፅ አካትቷል።ህወሓት እንደሚለዉ የኢትዮጵያ መንግሥት ትግራይ ክልል የሚገኝ አካባቢን በሰዉ አዉልባ አዉሮፕላን (ድሮን) ደብድቧል።ድብደባዉ የፕሪቶሪያዉን ግጭት የማቆም ሥምምነትን የጣሰ ነዉ በማለትም የፌደራሉን መንግስት ወንጅሏል።
የህወሓት መግለጫ በድብደባዉ ጉዳት ደርሷል ከማለት ሌላ የደረሰዉን የጉዳት መጠን አልጠቀሰም።የኢትዮጵያ የፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት ሥለ ጥቃት፣ ግጭት፣ ዉግዘትና ክሱ እስከ ዛሬ ድረስ በይፋ የሰጡት መግለጫ የለም።
የዓብይ መንታ መልዕክት-ሽምግልናና ዛቻ
ይሁንና 2018 ከባተበት ጀምሮ የኢትዮጵያ ፈደራዊ መንግሥት፣ የህወሓትና የኤርትራ ባለሥልጣናት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሚፅፉት ደብዳቤ ጭምር ያልተወቃቀሱ፣ ያልተወነጃጀሉና ያልተካሰሱበት ጊዜ የለም።ባለፈዉ ጥቅምት 18፣ 2018 ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በተለይ ወደብን በተመለከተ ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት መልስና ማብራሪያ ያስተላለፉት መልዕክትም ብዙ ተንታኞች እንዳሉት የሽምግልና ጥሪን ከኃይል ዛቻ የቀየጠ ነዉ።
«የዉጊያ መሻት የለንም።በሕጋዊና ንግግር ሊፈታ ይችላል ነዉ።ለብዙ ሐገራት በተናጥል ተናግሪያለሁ፣ ምክር ቤቱ ከፈለገ ግን ለአሜሪካ፣ ለቻይና፣ ለራሺያ፣ ለአዉሮጳ፣ ለአፍሪቃ አሁን በተከበረዉ ምክር ቤት ፊት መግለፅ እምፈልገዉ ነገር የኢትዮጵያ የቀይባሕር አክሰስ ጉዳይ አይቀሬ ሥለሆነ፣ ቅድሚያ የምንሰጠዉ ሠላምና ንግግር ሥለሆነ፣ እባካችሁ ሸምግሉንና መፍትሔ አምጡልን።ሚሊዮን ፐርሰንት እርግጠኛ ነኝ ኢትዮጵያ ተዘግታ አትኖርም።ማንም ፈለገም አልፈለገም።»
ከአዲስ አበባ የሽምግልና ጥሪ፣ ከብራሥልስ ለግብፅ ድጋፍ
የጠቅላይ ሚንስትሩ መልዕክት ከአዲስ አበባ ከመሰማቱ ከ6 ቀናት በፊት በሕዳሴ ግድብ ሰበብ ከኢትዮጵያ ጋር የምወዛገበዉ ግብፅ፣ ጠቅላይ ሚንስትሩ ለሽምጋይነት ከጋበዟቸዉ አንዱ ከሆነዉ ከአዉሮጳ ሕብረት ድጋፍ ይንቆረቆርላት ነበር።
ፕሬዝደንት አብዱልፈታሕ አል ሲሲ የመሩት የግብፅ የመልዕክተኖች ቡድንና አዉሮጳ ሕብረት መሪዎች ባጋራ ባወጡት መግለጫ «ግብፅ የዐባይን ወንዝ ዉኃ የመጠቀም መብቷን» ሕብረቱ እንደሚደግፍ በድጋሚ አስታዉቋል።
በነዚሕና በተያያዥ ምክንያቶች ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ያደረጉት ጥሪበመግለጫ-አፀፋ መግለጫ፣ በደብዳቤና ማስተባባያ የተካረረዉን የአዲስ አበባ፣ መቀሌ፣ አስመራ-ካይሮን ጠብ ለማርገብ እስካሁን የተከረዉ ነገር የለም።ታዛቢዎች እንደሚሉት የአዲስ አበባ ባለሥልጣናት ከሞቃዲሾዎች ጋር ይጣሉ፣ ከአስመሮች ወይም ከሐገር ዉስጥ ኃይላት ጋር ካይሮዎች ሁሌም ከአዲስ አበባ ተቃራኒዎች ጎን እንደቆሙ ነዉ።
የሰሞኑ የጥቃት-አፀፋ ጥቃትም ሆነ መወጋገዝ የፖለቲካ ተንታኝ ዩሱፍ ያሲን እንደሚሉት መሠረቱ የግብፅ-ኤርትራ፣ የህወሓት-ስምረት-አዲስ አበባ ጥልፍልፍ ፍትጊያ ዉጤት ነዉ።ከትግራይ መከላከያ ኃይል ያፈነገጡት ኃይላት አፋር ክልል እንዳይሰፍሩ አፋሮች ያደረጉት ሙከራ ከከሸፈ በኋላ ጠቡ በአፋር መሬት እንደሚጫር ይታወቅም ነበር።-አቶ ዩሱፍ እንደሚሉት
«እነዚሕ ሰዎችን መጀመሪያ አታምጡብን ብለዉ፣ መጀመሪያ ሌላ ቦታ ነበር የወሰዷቸዉ፣ ኮነባ ወረዳ ነበር የወሰዷቸዉ፣ እዚያ ህዝቡ እምቢ ብሎ ከዚያ ወጡ።እንደገና ሌላ ቦታ ነዉ የወሰዷቸዉ።እና እንደቀልድ የሚሉት ከፈለጋችሁ በሻሻ ዉሰዷቸዉ ወይም ጭፍራ ዉሰዷቸዉ ነበር።ትግሬዎቹም ቢሆኑ እነዚሕ ሰዎች ከናንተ ካልወጡ እነሱን ፍለጋ ወደዚያ መምጣችን አይቀርም ይሉ ሥለነበር ጦርነቱ እንደሚነሳ ይታወቅ ነበር።»
የለየለት ጦርነት ይጫራል-አይጫርም ልዩነት
እስካሁን በርግጥ ግልፅ ጦርነት የለም።ባጭር ጊዜ ዉስጥ ጦርነት መጫር-አለመጫሩም ተንታኖችን ለሁለት ገምሶ እያከራከረ ነዉ። አንዳድ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚገምቱት የኤርትራ መሪዎች ይሁኑ ነባር የጦር አዛዦች እድሜያቸዉ ገፍቷል።የተራዉን ተዋጊ የዉጊያ መንፈስ ማደስ፣ አዳዲስ ወጣቶችን መመልመል ለአስመራ ገዢዎች አስቸጋሪ ነዉ።ህወሓትም በ,2013 የነበረዉ የዉጊያ አቅም ምክንያትም አሁን የለዉም።የሰዉ፣ የጦር መሳሪያና የገንዘብ ምንጩም ተመናምኗል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ጦርም ቢሆን አማራና ኦሮሚያ ክልሎች በሚደረገዉ ግጭት እየባተለ ነዉ።የትግራይ የሰላም ኃይልም ይሁን ሌሎች የኢትዮጵያ መንግሥትን ሊደግፉ የሚችሉ ኃይላት ገና በቅጡ አልደራጁም።ሥለዚሕ የቀድሞዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዲፕሎማት ባይሳ ዋቅ ወያ እንደሚሉት ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ተከታዮቻቸዉ ከ,ቃላት ያለፈ ሙሉ ጦርነት መክፈታቸዉ ያጠራጥራል።
«በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል አሁን ከሚደረገዉ የቃላት ጦርነት ያለፈ ሙሉ ጦርነት ይደረጋል ብዬ አላስብም።በብዙ ምክንያት።ምናልባት በጣም ተስፋ አድርጌ ሊሆን ይችላል፤ ይሁንና አሁን ባለንበት ደረጃ ኢትዮጵያና ኤርትራ ሙሉ ጦርነት ለመግጠም መሰረት ያለ አይመስለኝም።»
ጦርነቱ አይቀርም ግን እንዴት?
ሌሎች የፖለቲካ ተንታኞች ግን ጦርነቱ አይቀርም ባይ ናቸዉ።በሱዳኑ ጦርነት ተቀናቃኝ ኃይላትን የሚደግፉት የግብፅና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግሥታትም የኤርትራና የኢትዮጵያ መንግሥታትንና ተከታዮቻቸዉን መደገፋቸዉ አይቀርም።አቶ ዩሱፍ ያሲን እንደሚሉት የሰሞኑ መካካስና መወቃቀስም ሙሉዉን ጦርነት ማንጀመረዉ ለሚለዉ ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ጥያቄ አንዱ ሌላዉን ለማጋለጥ እየተጠቀሙበት ነዉ።
ኢትዮጵያ በየሥፍራዉ ከሚደረጉ ግጭቶች በተጨማሪ የኑሮ ዉድነት፣ ሰዎች ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ደሕንነት እጦት፣ እገታና ግድያን የመሳሰሉ የሕግና ሥርዓት መጓደሎች አቃርጠዉ እንደያዟት ነዉ።ትግራይን ጨምሮ ከአራት ሚሊዮን የሚበልጥ ተፈናቃይ በየመጠለያ ጣቢያዉ እንደሰፈረ ነዉ።የኤርትራ ሁኔታም ከኢትዮጵያ የባሰ እንጂ ያነሰ አይደለም።በዚሕ ላይ አካባቢዉ ሌላ ጦርነት ይችል ይሆን?
ነጋሽ መሐመድ
ታምራት ዲንሳ























