የቀድሞው የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኒኮላ ሳርኮዚ ከእስር ተፈቱ
Description
ዛሬ ያስቻለው አንድ የፓሪስ ፍርድ ቤት የቀድሞው የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኒኮላ ሳርኮዚ ከእስር እንዲለቀቁ ወሰነ። የአምስት ዓመት እስር ተፈርዶባቸው ባለፈው መስከረም ላ ሶንት የተባለ እስር ቤት ከወረዱ 20 ቀን የሆናቸውሳርኮዚ ከእስር ተለቀው ዛሬ ቤታቸው ገብተዋል። የ70 ዓመቱ ሳርኮዚ በመስከረም የተበየነባቸውን የአምስት ዓመት እስር ከጀመሩ ከሳምንታት በኋላ ዛሬ ጠዋት ነበር ከእስር እንዲለቀቁ ለፍርድ ቤቱ ይግባኝ ያሉት። ሳርኮዚ ዛሬ ከእስር የተለቀቁት በገደብ ነው።
የታሰሩትም በጎርጎሮሳዊው 2007 ዓም ለተካሄደው የፈረንሳይ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የቅርብ ረዳቶቻቸው ከቀድሞ የሊቢያ ፕሬዝዳንት ሞአመር ጋዳፊ ባካሄዱት ገንዘብ የማሰባሰብ ሙከራ፣ በወንጀል ሴራ ጥፋተኛ ከተባሉ በኋላ ተፈርዶባቸው ነው። የቀድሞው ወግ አጥባቂፕሬዝዳንት ሳርኮዚ ባለፈው መስከረም የአምስት ዓመት እስር ሲበየንባቸው በእለቱም ሆነ ከዚያም በፊት ምንም ስህተት እንዳልፈፀሙ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ቆይተዋል። የበቀልና የጥላቻ ሰለባ ሆኛለሁ ሲሉም በምሬት ገልጸው ነበር ።
ፈረንሳይን ከጎርጎሮሳዊው 2007ዓ.ም. እስከ 2011 ዓም የመሩት ሳርኮዚ በፈረንሳይ ፕሬዝዳንቶች የቅርብ ጊዜ ታሪክ ዘብጥያ የወረዱ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ናቸው። ስለ ሳርኮዚ ዛሬ ከእስር መለቀቅ የፓሪስዋን ዘጋቢያችንን ሃይማኖት ጥሩነህን ስቱድዮ ከመግባቴ በፊት በስልክ አነጋግረናታል።























