ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች: በተማሪዎች የሚከበሩ "ቀናቶች" ጠቃሚ ወይንስ ጎጂ?
Description
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ወጣቶች የተለያዩ ቀናቶችን ሲያከብሩ ይስተዋላል ፡፡ አይነቶቹ ብዙ ቢሆኑም ከለር ዴይ ፣ ክሬዚ ዴይ ፣ ጋቢ ዴይ ፣ ስናክ ዴይ እና በርገር ዴይ ፣ የመሳሰሉት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው ፡፡ ወጣቶቹ በእነኝህ ቀናቶች ብር በማሰባሰብ ፣ ተመሳሳይ ቲሸርቶችን በመልበስ እና በመገባበዝ ያሳልፋሉ ፡፡
የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ እና የ12 ክፍል ተማሪ የሆነችው ማሪያማዊት ዳዊት ቀናቶቹን ማክበር ችግር የለውም ትላለች ፡፡ ተማሪ ማሪያማዊት ተማሪዎች ቀናቶች ማክበራቸው እርስ በእርስ በመተዋወቅ አንዳቸው ከሌሎቻቸው የህይወት ልምድና ገጠመኝ ሊማማሩ የሚችሉበትን ዕድል ይፈጥራል የሚል እምነት አላት፡፡
ከቤት ወጪ ከሌሎች ሰዎችና በተመሳሳይ ዕድሜ ከሚገኙ ጓደኞቻቸው ጋር በመዋል በራስ መተማመንን ለማዳበር እንደሚያስችል የምትናገረው ተማሪዋ “ ሰዎች እነኝህን ቀናቶችን ምክንያት አድረገው አብሮነትን የሚያጠናክሩ ወጣቶች ከሌሎች እንደጫት ፣ ሺሻ ወይንም መጠጥ ቤቶች ከሚውሉት ለይተው ማየት አለባቸው ብዬ አምናለሁ “ ብላለች ፡፡
ሌላኛዋ የ12 ክፍል ተማሪ የሆነችው ሊያ በላቸው ቀናቶቹ ከጅምሩ ከውጭ የገቡና ኢትዮጵያ ዊ መሠረት የሌላቸው ናቸው ትላለች ፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ተማሪዎች ክሬዚ ዴይ በሚል ያልተገባ አለባበስ በመልበስና ከሥነ ምግባር ውጪ የሆኑ ባህሪያትን ሲያንጸባርቁ እንደሚታዩ የጠቀሰችው ተማሪ ሊያ “ ወጣቶች ቀናቶቹን ለማክበር የሚስፈልጋቸውን ወጪ ለመሸፈን አቅም የሌላቸውን ቤተሰቦቻቸውን ሲያስቸግሩ ይታይል ፡፡ ቤተሰብ ካልሰጣቸው ወደ ሥርቆት ሊገቡ ይችላሉ “ ብላለች ፡፡
በተጨማሪም አንዳንዶቹ በመሰባሰባቸው ምክንያት መጠጥን ጨምሮ በተለያዩ ጎጂ ነገሮችን በመጠቀም ጭምር የሚያከብሩበት ሁኔታ እንዳለ የምትናገረው ሊያ “ ይህም ወደ አላሥፍላጊ ድርጊት ሊገፋፋና ህይወታቸውን ሊያበላሽ ይችላል ፡፡ በአጠቃላይ እንደ እኔ ቀናቶቹ ባይከበሩ ቢቀር ይሻላል ፡፡ እናከብራለን መብታችን ነው ካሉ ደግሞ ቦታው በሆቴሎችና ወይንም በሌላ ሥፍራ ከሚሆን በትምህርት ቤቶች ግቢ ውስጥ ቢሆን የተሻለ ነው” በማለት አስተያየቷን ሰጥታለች ፡፡
ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ
ታምራት ዲንሳ