DiscoverDW | Amharic - Newsየኅዳር 29 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
የኅዳር 29 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

የኅዳር 29 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

Update: 2025-12-08
Share

Description

በቫሌንሺያ ማራቶን ትውልደ ኤርትራውያን የአውሮጳ ሯጮች ትናንት ድል ቀንቷቾዋል ። አርናል በሽርፍራፊ ሰከንዶች ሽንፈት ገጥሞታል፥ ማንቸስተር ሲቲ ድል አድርጎ በነጥብ ተጠግቶታል ። ሊቨርፑል ግራ ተጋብቷል ። ሞሐመድ ሣላህ በሊቨርፑል እጅግ ሐዘን ገብቶታል፥ ምናልባትም ከሚወደው ሊቨርፑል ሊሰናበት ይችል ይሆናል ። ሊቨርፑል ነገ (ማክሰኞ፤ ኅዳር 29 ቀን፣ 2018 ዓ.ም) ከኢንተር ሚላን ጋር በሚኖረው የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ የመሰለፉም ነገር አጠራጣሪ ነው ። በፍርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ላንዶ ኖሪስ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ዋንጫ አንስቷል ። የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ድልድል ይፋ ሁኗል ።



በቫሌንሺያ ማራቶን ትውልደ ኤርትራውያን የአውሮጳ ሯጮች ድል ቀናቸው



በስፔን ቫሌንሺያ ማራቶን የኬንያ ሯጮች በወንድ በሴትም ድል ቀንቷቸዋል ። ለጀርመን የሚሮጠው ትውልደ ኤርትራዊ አማናል ጴጥሮስ (2፡04፡03) ሁለተኛ በመውጣት በሣሙኤል ፍትዊ ተይዞ የነበረውን የጀርመን ክብረወሰንን ሰብሯል ። ሌላኛው ትውልደ ኤርትራዊ የኖርዌይ ሯጭ አወት ክብረአብ ደግሞ ትናንት ስፔን ውስጥ በተከናወነው የቫሌንሺያ ማራቶን (2:04:25 ) ሦስተኛ ደረጃ አግኝቷል ። ሁለቱ ትውልደ ኤርትራዊ ሯጮች በውድድሩ መገባደጃ አካባቢ ተመካክረው ወደፊት በመግፋት በጋራ ሠርተዋል ። በየመሀሉ እያወሩም ሲጨባበጡ ታይተዋል ።



በቫሌንሺያው የማራቶን ሩጫ ፉክክር ረዥም ርቀት ለብቻው በመሮጥ (2፡02፡24) የኬንያው ጆን ኮሪር ድል አድርጓል ። የእስራኤሉ አትሌት ጋሻው ዐያል (2:05:30 ) የጃፓኑ ሯጭ ሱጉሩ ኦሳካን (2:04:55 ) ተከትሎ አምስተኛ ደረጃ አግኝቷል ። ኢትዮጵያዊው አትሌት ገመቹ ዲዳ (2:06:45 ) 10ኛ፤ ሌላኛው ኢትዮጵያዎ ሲሰሳይ ለማ (2:08:58 ) 25ኛ ደረጃ አግኝቶ አጠናቅቋል ።



አማናል ጴጥሮስ ውድድሩ ከባድ ቢሆንም ኬንያ ሄዶ በኤልዶራደ‍ኦ ኤቴን ከፍታማ የሥልጠና ስፍራ ለስምንት ሳምንታት መለማመዱ እጅግ እንደረዳው ገልጧል ። ከውድድሩ ፍጻሜ በኋላ በሰጠው ቃለ ምልልስ፦ አሯሯጩ ችግር ነበረበትም ብሏል ። ሌላኛው የጀርመን ሯጭ ሣሙኤል ፍትዊ (2:07:01 ) በመሮጥ 12ኛ ደረጃ አግኝቷል ። ጀርመናዊው ሯጭ ሔንድሪክ ፕፋይፈር (2:06:46 ) ሣሙኤልን ቀድሞ 11ኛ ወጥቷል ።



በሴቶች ተመሳሳይ ፉክክር ደግሞ፦ ሌላኛዋ ኬኒያዊት ጆይሴሊን ጄፕኮስጋይ (2:14:00 ) የቦታውን ክብረወሰን በመስበር አሸንፋለች ። የአገሯ ልጅ ፔሬዝ ጄፕቺርቺር (2:14:43 ) ሁለተኛ ደረጃ አግኝታለች ። ሁለቱ ኬኒያዊት ለረዥም ርቀት ከሌሎቹ ሯጮች ተለይተው ተራ በተራ ሲቀዳደሙ ነበር ። የሦስተኛ ደረጃው (2:20:38 ) ሮጣ ያጠናቀቀችው ቤልጂጋዊ ሯጭ ክሎዬ ሔርቢት ሁኗል ።



በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ መሪው አርሰናል ግስጋሴው ተገትቷል



በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ መሪው አርሰናል ግስጋሴው የማታ ማታ በአስቶን ቪላ ተገትቷል ። አርሰናልን የጨዋታው መደበኛ 90 ደቂቃ ተጠናቅቆ በአምስተኛው ጭማሪ ደቂቃ ላይ ግብ በማስቆጠር ጉድ ያደረገው ኤሚ ቦይኒዳ ነው ። በደረጃ ሰንጠረዙ መሪው አርሰናል በ33 ነጥቡ ሲወሰን፤ ቅዳሜ ዕለት ጉድ ያደረገው አስቶን ቪላ በሦስት ነጥብ ብቻ ተበልጦ በ30 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ጉብ ማለት ችሏል ።



ቅዳሜ ዕለት ማንቸስተር ሲቲ ኤቲሐድ ስታዲየሙ ውስጥ ሠንደርላንድን 3 ለ0 ድል አድርጓል ። ነጥቡንም ከአርሰናል ጋር በሁለት ብቻ አቀራርቦ 31 አድርሷል ። ክሪስታል ፓላስ ትናንት ፉልሀምን በገዛ ሜዳው 2 ለ1 አሸንፎ ነጥቡን 26 ደረጃውን 4ኛ አድርሷል ። ከበርመስ ጋር ያለምንም ግብ የተለያየው ቸልሲ በ 25 ነጥቡ ተወስኖ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። 6ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኤቨርተን ኖቲንግሀም ፎረስትን 3 ለ0 ኩም አድርጎ ነጥቡን ወደ 24 ከፍ አድርጓል ።የኅዳር 22 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ



አንድ ተስተካካይ ጨዋታውን ዛሬ ማታ ከዎልቭስ ጋር የሚያደርገው ማንቸስተር ዩናይትድ በ22 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ዎልቭስ እስካሁን ያለው 2 ነጥብ ብቻ ነው፦ ወራጅ ቀጣናው መጨረሻ ግርጌ 20ኛ ላይ ተዘርግቷል ። ለሦስተኛ ጊዜ አጥቂው ሞሐመድ ሣላኅን ሳያሰልፍ ወደ ሜዳ የገባው ሊቨርፑል ከሊድስ ዩናይትድ ጋር ሦስት እኩል ተለያይቶ ነጥቡን ወደ 23 ፈቅ አድርጓል፦ ደረጃውም ቁልቁል 9ኛ ነው ።



ሞሐመድ ሣላኅ ከሊቨርፑል አሰልጣኝ አርኔ ስሎት ጋር ብርቱ ቅራኔ ውስጥ ገብቷል



ግብጻዊው ሞሐመድ ሣላኅ ከሊቨርፑል አሰልጣኝ አርኔ ስሎት ጋር ብርቱ ቅራኔ ውስጥ ገብቷል ። አሰልጣኙ ለሊቨርፑል ለዘመናት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረከተው የ33 ዓመቱን አጥቂ ለሦስተኛ ጊዜ በተከታታይ ተቀያሪ ወንበር ላይ ማስቀመጣቸው አጥቂውን እጅግ አበሳጭቷል ።



ሞሐመድ ሣላኅ በሊቨርፑል ውስጥ ረዥም ጊዜ ቆይተው በደጋፊዎች ዘንድ በልዩ ሁኔታ ከሚታዩ ጥቂት ተጨዋቾች መካከል አንዱ ነው ። እንደ እነ ኢያን ራሽ፣ ኬኒ ዳግሊሽ እና ሽቴፋን ጄራርድ በሊቨርፑል ቡድን በልዩ ሁኔታ የሚታየው ሞሐመድ ሣላኅ ለቡድኑ 420 ጊዜያት ተሰልፎ 250 ግቦችን ማስቆጠር የቻለ ግብ አዳኝ ነው ። ይህ ብቃቱ ግን በዘንድሮ ውድድር ወርዶ ታይቷል ። ባለፉት 13 የፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያዎች ለሊቨርፑል ያስቆጠራቸው 4 ግቦችን ብቻ ነው ።



ግብጻዊው አጥቂ በሚቀጥለው ወር ምናልባትም ወደ ሣዑዲ ዓረቢያ ሊግ ሊያቀና እንደሚችል ይነገርለታል ። ሞሐመድ ሣላኅ የፊታችን ቅዳሜ ከብራይተን ጋር አንፊልድ ሜዳ ላይ በሚኖረው ግጥሚያ ደጋፊዎቹን እንደሚሰናበት ፍንጭ ሰጥቷል፥ ምናልባት ታዲያ በእለቱ ተሰላፊ ከሆነ ነው ። ከዚያ በኋላ ግን ለአፍሪቃ ዋንጫ ለረዥም ጊዜ ገለል ማለቱ አይቀርም ። ሊቨርፑል ነገ (ማክሰኞ፤ ኅዳር 29 ቀን፣ 2018 ዓ.ም) ከኢንተር ሚላን ጋር በሚኖረው የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ አይሰለፍም ተብሏል ።



ቡንደስሊጋ



በጀርመን ቡንደስሊጋ፦ መሪው ባዬርን ሙይንሽን ሽቱትጋርትን በገዛ ሜዳው 5 ለ0 አንኮታኩቶ ነጥቡን ወደ 37 ከፍ አድርጓል ። በ22 ነጥቡ ስድስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሽቱትጋርት ሎሬንዝ አሲኞን 81ኛው ደቂቃ ላይ በቀይ ካርድ ከሜዳ አጥቷል ። 21 ነጥብ ሰብስቦ ሰባተኛ ላይ የሰፈረው አይንትራኅት ፍራንክፉርትን 6 ለ1 ያደባየው ላይፕትሲሽ 29 ነጥብ ሰብስቦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ።



በ28 ነጥቡ በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ትናንት ሆፈንሀይምን 2 ለ0 አሸንፏል ። ሆፍንሀይም በ23 ነጥብ ደረጃው አምስተኛ ነው ። በ13 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ በሚገኘው አውግስቡርግ የ2 ለ0 ሽንፈት የደረሰበት ባዬር ሌቨርኩሰን 23 ነጥብ አለው ። አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ።



ሳንክት ፓውሊ እና ማይንትስ በስምንት እና ስድስት ነጥብ ብቻ ተወስነው ወራጅ ቀጣናው 17ኛ እና 18ኛ ላይ ይገኛሉ ። ከበላያቸው ሐይደንሀይም በ11 ነጥቡ ወራጅ ቀጣናው ግርጌ ላይ ይጠብቃቸዋል ። በ16 ነጥቡ ስምንተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኮሎኝ እና ሐይደንሀይም ልዩነታቸው የአራት ነጥብ ብቻ ነው ።



ሊዮኔል ሜሲ በ38 ዓመቱ ብቃቱን ዕያሳየ ነው



አርጀንቲናዊው የኳስ ጥበበኛ ሊዮኔል ሜሲ በዩናይትድ ስቴትሱ ዋና ሊግ (MLS ) ሚያሚ ቡድን ጋር በመሆን ቅዳሜ ዕለት በፍጻሜው ቫንኮቨር ኋይትካፕስን 3 ለ1 ድል በማድረግ ዋንጫ አነሳ ። ከሚያሚ ቡድን ጋር የቅዳሜውን ጨምሮ ሦስት ዋንጫዎችን ያነሳው የ38 ዓመቱ አጥቂ በዋናው ሊግ ሚያሚን የመጀመሪያ ዋንጫ እንዲያነሳ አስችሎታል ። በአጠቃላይ ሊዮኔል ሜሲ እስካሁን 48 ዋንጫዎች ከፍ ማድረግ የቻለ ድንቅ ተጨዋች ነው ።



የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ድልድል ይፋ ሁኗል ። ፊፋ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕን በቀጣዩ የዓለም ዋንጫ የአገራት ድልድል እጣ አወጣጥ ወቅት የፊፋ የሰላም ሽልማትን ሰጥቷቸዋል ። ፕሬዚደንቱ ለሽልማቱ አመሰግነው ሜዳሊያቸውን አጥልቀዋል ።



ጂያኒ ኢንፋንቲኖ፦ «ክቡር ፕሬዚደንት፤ ይህ ሽልማቶት ነው፤ ይህ የሰላም ሽልማቶት ነው ። ውብ የሆነ ሜዳሊያም አለዎ፤ መሄድ በሚፈልጉት ቦታ ሁሉ ሊያጠልቁት ይችላሉ ።»



ዶናልድ ትራምፕ፦ «አሁኑኑ አጠልቀዋለሁ ።»



ጂያኒ ኢንፋንቲኖ፦ «እሺ ልያዘው ፤ ድንቅ ፤ እጹብ ድንቅ ።»



ዶናል ትራምፕ፦ «በጣም አመሰግናለሁ ። በእውነቱ ይህ በሕይወቴ ከታላላቅ ክብሮቼ አንዱ ነው ። ከሽልማቱ ባሻገር ጂያኒ እና እኔ ይህን ስንወያይበት ነበር ። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት አትርፈናል ።»



የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ድልድል



ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕም የእጣ ማውጣቱ ላይ በተሳተፉበት ሥነ ስርዓት ጀርመን በምድብ «ሠ» ተደልድላለች ። በምድቡ ኤኳዶር፣ ከሁለት ዓመት በፊት የዓለም ዋንጫ ያሸነፈችው ኮት ዲቯር እና ኩራካዎ ይገኛሉ ። የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ጁሊያን ናግልስማን ለጀርመን አገር አቀፋዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ (ZDF) በሰጡት ቃለ ምልልስ፦ «ምድቡ እጅግ ቀላል የሚባል አይደለም» ብለዋል ። ቆይት ብለው ከማጌንታ ቲቪ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ደግሞ፦ «የምንፈተን መሆኑ ጥሩ ነው» ሲሉም አክለዋል ።



ጀርመን በምድቧ አሸናፊ ከሆነች በ16 አገራት ጥሎ ማለፍ ላይ ከፈረንሣይ ጋር ይደርሳታል ። ፈረንሣይ ምድብ ውስጥ የነ ሳዲዮ ማኔ ሴኔጋል፣ የእነ ኧርሊንግ ኦላንድ ኖርዌይ ይገኛሉ ። የኢራቅ፣ የቦሊቪያ አለያም ሱሪናም አሸናፊ ምድቡን ይቀላቀላል ።



የዓለም ዋንጫ የወቅቱ አሸናፊ አርጀንቲና በራልፍ ራኚክ የሚሰለጥነው የኦስትሪያ ቡድንን ይገጥማል ። አልጄሪያ እና ዮርዳኖስም በምድቡ የሚገኙ ቡድኖች ናቸው ። ጀርመናዊው ቶማስ ቱኁል የሚያሰለጥኑት የእንግሊዝ ቡድን ደግሞ ከእነ ክሮሺያ፣ ጋና እና ፓናማ ጋር ተደልድሏል ።የኅዳር 15 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ



በቪዛ ጉዳይ የተነሳ የእግር ኳስ ኮንፌዴሬሽኗ የእጣ ድልድሉን ተቀባይነት የለውም ያለው የኢራን ቡድን ከቤልጂግ፣ ከነ ሞሐመድ ሣላኅ ግብጽ እና ከኒውዚላንድ ጋር ተመድቧል ። ቀጣዩ የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ሰኔ 4 ቀን፣ 2017 ዓም ሜክሲኮ እና ደቡብ አፍሪቃ በሚያደርጉት ግጥሚያ ይከፈታል ። ጨዋታዎቹ የሚከናወኑትም ዩናይትድ ስቴትስ እንዲሁም ተጎራባቾቿ ካናዳ እና ሜክሲኮ ውስጥ በጋራ ነው ።



ላንዶ ኖሪስ በፎርሙላ አንድ ለመጀመሪያ ጊዜ የዐለም ዋጫ አሸነፈ



በአቡ ዳቢ የትናንት የፍጻሜ ሽቅድምድም የማክላረን አሽከርካሪ ላንዶ ኖሪስ በፎርሙላ አንድ ለመጀመሪያ ጊዜ የዐለም ዋጫ አሸነፊ ሆነ ። ባለፈው ሳምንት የኳታር ግራንድ ፕሪ የመኪና ሽቅድምድም የማክላረን አሽከርካሪዎች «ብርቱ ስህተት» የሬድ ቡል አሽከርካሪው ማክስ ፈርሽታፐን እንዲያሸንፍ አስችሎት ነበር ።



ማክስ ፈርሽታፐን በትናንቱ ፉክክር አሸናፊ ቢሆንም፤ ሦስተኛ የወጣው ላንዶ ኖሪስ በአጠቃላይ ነጥብ በልጦ የዓለም ዋንጫውን አንስቷል ። የትናንት አሸናፊው ማክስ ፈርሽታፐን ከላንዶ በአጠቃላይ ነጥብ የተበለጠው ለጥቂት በ3 ነጥብ ብቻ ነው ። ላንዶ ኖሪስ የአራተኛ ደረጃ አግኝቶ ቢሆን ኖሩ፤ ማክስ ፈርሽታፐን ለአራተኛ ጊዜ የዓለም ዋንጫ ያነሳ ነበር ። ሆኖም ላንዶ ኖሪስ በአጠቃላይ 423 ነጥብ በመሰብሰብ ከእጁ የገባውን አጋጣሚ አሳልፎ ሳይሰጥ ድል ተጎናጽፏል ። ሌላኛው የማክላረን አሽከርካሪ ዖስካር ፒያስትሪ በ410 ነጥብ ብርቱ ፉክክር የሦስተኛ ደረጃ አግኝቷል ። በመርሴዲስ ተሽከርካሪው ለሰባት ጊዜያት የፎርሙላ አንድ የዓለም ዋንጫዎችን መሰብሰብ የቻለው ሌዊስ ሐሚልተን በአጠቃላይ 156 ብቻ በ6ኛ ደረጃ የዘንድሮውን ውድድር አናቅቋል ።



ማንተጋፍቶት ስለሺ



ታምራት ዲንሳ

Comments 
loading
In Channel
loading
00:00
00:00
1.0x

0.5x

0.8x

1.0x

1.25x

1.5x

2.0x

3.0x

Sleep Timer

Off

End of Episode

5 Minutes

10 Minutes

15 Minutes

30 Minutes

45 Minutes

60 Minutes

120 Minutes

የኅዳር 29 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

የኅዳር 29 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ማንተጋፍቶት ስለሺ ሥዩም Mantegaftot Sileshi