«ሐይማኖትን መሰረት ያደረገ ጥቃት ይቁም»
Description
በተላለዮ የሐገሪቱ አካባቢዎች ሐይማኖትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እንዲቆሙ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት አስፈላጊውን ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ ቀረበ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ቋሚ ሲኖዶስ እና የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በምዕራብ አርሲ በኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች በቅርቡ የደረሰውን ግድያ በጽኑ ያወገዙ ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክርቤት በበኩሉ በመስከረም ወር መጨረሻ በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን መካነ ሰላም ከተማ በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ላይ የደረሰውን ግድያ በጽኑ አውግዟል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ቋሚ ሲኖዶስ ባወጣው መግለጫ «በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በምስራቅ አርሲ ዞን ጥቅምት 14 ለ 15 አጥቢያ 2018 ዓ.ም በጉናና መርቲ ወረዳዎች 17 ክርስትያኖች፤ ጥቅምት 17 ለ18 አጥቢያ በሸርካ ወረዳ 3 ክርስትያኖች እንዲሁም ጥቅምት 18 ለ19 አጥቢያ በሆኖንቆ ዋቤ ወረዳ 5 ክርስትያኖች በድምሩ በጥቅምት ወር ብቻ 25 ኦርቶዶክሳውያን ወገኖች አገራችንና ምድራችን ብለው በሰላም በተኙበት ማንነታቸው ባልታወቀ ታጣቂዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል።» ብሏል ። ግድያውም ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው «የምስራቅ አርሲ ሐገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት የላከውን ሪፖርት ቋሚ ሲኖዶሱ የተመለከተው በከባድ ጥልቅ የሐዘን ስሜት» እንደሆነም አክሏል።
የአይን እማኝ አስተያየት
በጉና ወረዳ ጥቅምት 13 ለ14 አጥቢያ ስለደረሰውጥቃትአንድ ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይገለጽና ድምጻቸው እንዲቀየር የጠየቁ የአይን እማን ለዶይቸቨለ በሰጡት አስተያየት ሌሊት በግምት ከ5 እስከ6 ሰዓት አካባቢ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በእምነቱ ተከታዮች ላይ በፈጸሙት ጥቃት 16 ሰዎች መገደላቸውን ገልጸዋል።
የመንግስት የጸጥታ አካል ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ መድረሱን የገለጹት እኒህ የአይን እማኝ ሟቾቹ በአካባቢው ሕብረተሰብ መቀበራቸውን ገልጸዋል። የአይን እማኙ አክለውም ግድያው በተፈጸመበት ጊዜ ከአካባቢው ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች መፈናቀላቸውን ገልጸውልናል። የቆሰሉ እንዳሉም በማከል።
የቋሚ ሲኖዶስ መግለጫ
«በምስራቅ አርሲሀገረ ስብከት እንዲህ አይነቱ አሰቃቂ ድርጊት ሲፈጸም የቆየው በተደጋጋሚ መሆኑን የገለጸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ቋሚ ሲኖዶስ«እንዲህ አይነቱ አስነዋሪ ድርጊት በቅዱሳት መጻሕፍት ሆነ በሰው ልጅ ሰብዓዊ መብት ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው፤ በነጻነት የማምለክ ሕገመንንግስታዊ መብትን የሚጋፋ፤ ተከባብሮና ተቻችሎ የመኖር መንፈሳዊ እሴቶቻችንን የሚያጠፋ፤ ክብረ ነክ እና ሊወገዝ የሚገባው ኢ ስነምግባራዊ ድርጊት በመሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ቋሚ ሲኖዶስ በጽኑ አውግዞታል።» ሲል ድርጊቱን ኮንኗል።
ቋሚ ሲኖዶሱ በመግለጫው «በጉዳዮን በቀጥታ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ይህን ኢሰብአዊ የሆነ ተግባር በጽኑ በማውገዝና በሕገመንግስቱ የተረጋገጠውን በሕይወት የመኖርና የዕምነት ነጻነት መብትን እንዲያስከብሩልንና« ይህ አስነዋሪ ድርጊት የፈጸመትን ወንጀለኞችን ለሕግ በማቅረብ የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ በተጨማሪም፤ በቀጣይ እንዲህ አይነቱ ህገወጥ ተግባር እንዳይደገም አስፈላጊውን የሕግ ከለላ በመስጠት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ቋሚ ሲኖዶስ መንፈሳዊ ጥሪውን ያስተላልፋል።» ብሏል።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ መግለጫ
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ባወጣው መግለጫም «በአንጋፋዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ካህናትና ምዕመናን ላይግድያና ስቃይ መፈጸሙን የሰማነው በታላቅ ድንጋጤና ሐዘን ነው» ብሏል።
መግለጫው አክሎም «መንግስት የዜጎቹ በሰላም ወጥቶ የመግባት ነጻነት የማረጋገጥ ዋነኛ ሃላፊነት ያለበት በመሆኑ ችግሩ ከዚህ በላይ ተባብሶ ተጨማሪ ሐዘንና ሰቆቃ ከመከሰቱ አስቀድሞ አስፈላጊውን የሕግ ማስከበር ሥራ እንዲሰራ ጉባኤው በአጽንኦት ያሳስባል» ሲል ጥሪውን አቅርቧል።
የአዲስ አበባ ከተማ የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት መግለጫ
በተያያዘ ዜና የአዲስ አበባ ከተማ የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት መስከረም 24 ቀን 2018 ባወጣው መግለጫ «መስከረም 23 ቀን 2018 ዓ.ም በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን በመካነ ሰላም ከተማ በኑር መስጅድ ኢማምና ምእመን ላይ ምሽትን ተገን በማድረግ የተፈጸመውን አሰቃቂና አረመኔያዊ ጭፍጨፋ በፅኑ ያወግዛል»ሲል መግለጫ ማውጣቱ ይታወቃል።
በክልሉ ባለፉት ዓመታት ሙስሊሞች በዕምነታቸው ምክንያት በክልሉ በሚነቀሳቀሱ ታጣቂ ሀይሎች ተለይተው ተገድለዋል ንብረታቸውም ተዘርፏል ያለው ምክር ቤቱ ፤ ድርጊቱን የሐይማኖት ተቋማት፣ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እና ሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጋ በጽኑ እንዲያወግዝም ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።
በሀይማኖት ሰበብ ይፈፀማሉ የተባሉትን ግድያዎች አስመልክተን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን የምዕራብ አርሲ ሐገረ ስብከት፣ ከኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሚኒኬሽን እና ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክርቤት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት ለጊዜው አልተሳካም። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በበኩሉ ድርጊቱን የተመለከቱ መረጃዎች እያሰባሰበ መሆኑን ገልጾ በሚቀጥሉት ቀናት ይፋ እንደሚያደርግ ገልጾልናል።
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሄር
ፀሐይ ጫኔ























