በኢትዮጵያ ከ12,000 ዓመታት በኋላ የፈነዳው ሐይሊ ጉብ እሳተ ገሞራ በረራ አስተጓጎለ
Description
በኤርትዓሌ የእሳተ ገሞራ ሰንሰለት ሥር ከሚገኙ ተራሮች በአንዱ ላይ ባለፈው እሁድ የተከሰተ ፍንዳታ እስከ 14 ኪሎ ሜትር ወደ ሰማይ የሚትጎለጎል አመድ አስከትሏል። አመዱ የኢትዮጵያን ድንበር እና ቀይ ባሕርን ተሻግሮ በሕንድ በረራዎች ላይ ተጽዕኖ ያሳደረ ነው። ፍንዳታው የተከሰተው በአፋር ክልል ኪልበቲ ራዕሱ ዞን ከአፍዴራ ወረዳ ስምንት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የሐይሊ ጉብ ተራራ ነው።
በአካባቢዉ የነበሩት የአፋር ክልል ቱሪዝም ቢሮ ባለሥልጣን መሐመድ ሐሰን ሦስት ፍንዳታዎች መሰማታቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ባለሙያዎች ጋር ወደ ቦታው አቅንተው የነበሩት አቶ መሐመድ ሁለቱ ፍንዳታዎች “ጭስ ያላቸው” መሆናቸውን አስረድተዋል።
“ከአቅም በላይ ሥጋት እና ፍራቻ” የፈጠረው ፍንዳታ እና ያስከተለው ዕይታ የሚጋርድ ጭስ የአካባቢውን ነዋሪዎች ወደ ጸሎት እንደመራ አቶ መሐመድ ገልጸዋል። “ትላላቅ ሰዎች ከድንጋጤ ብዛት ድንጋይ ላይ ወደቁ” ያሉት አቶ መሐመድ “እንስሳውም ገደል ለገደል ይሮጥ ነበር” በማለት በወቅቱ የተከሰተውን አብራርተዋል።
አቶ መሐመድ በነበሩበት አካባቢ በሰዎች ላይ የደረሰው “የመሰባበር የመላላጥ” “ትንሽ የሆነ አካል” ጉዳት መሆኑን ገልጸዋል። ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በወረዳው አስተዳደር ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል። በፍንዳታው በተከሰተው አመድ ምክንያት “አይናችንን እና አፍንጫችንን በማስክ ሸፈንን” ሲሉ አቶ መሐመድ አብራርተዋል።
የአፋር ክልል ጤና ቢሮ በፍንዳታው ምክንያት የተከሰተው አመድ እና ብናኝ የጤና ጉዳት ስለሚያስከትል ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ማሳሰቢያ ሰጥቷል። እሳተ ገሞራው በፈነዳበት ቦታ 30 ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ 9,000 ሰዎች ገደማ እንደሚኖሩ የገለጸው የአውሮፓ ኅብረት የሰብአዊ ርዳታ እና ሲቪል ጥበቃ ማዕከል (ECHO) በተከሰተው ብናኝ ሊጎዱ እንደሚችሉ አስታውቋል።
ፍንዳታው “በተለይ ከኤርትዓሌ ዙሪያ ሰዎችን” አንድ ቀን ተኩል እንዳፈናቀለ አቶ መሐመድ ተናግረዋል። ምግብ እና መጠለያ ተዘጋጅቶ ከአካባቢው 40 ኪሎ ሜትር እንዲርቁ የተደረጉ ሰዎች መኖራቸውንም አስረድተዋል።
በፍንዳታው የተከሰተው አመድ እስከ ማታ ዕይታ ጋርዶ ከቆየ በኋላ “ከነጋታው ከጠዋት ከ11:30 ተኩል ጀምሮ መክፈት ጀመረ” ሲሉ አቶ መሐመድ ተናግረዋል። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የበርኻሌ ከተማ ነዋሪዎች እንደሚሉት ባለፈው እሁድ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ገደማ የሰሙትን ድንገተኛ ድምጽ ከቦምብ እና ከመድፍ ቢያመሳስሉትም በወቅቱ በምን ሳቢያ እንደተከሰተ ግን መረጃ አልነበራቸውም።
ከበርኻሌ 45 ኪሎ ሜትር ገደማ በምትርቀው አመዴላ የተባለች ቦታ እና በአፍዴራ አካባቢ ጉም መሳይ ጭስ መመልከታቸውን ነዋሪዎች አስረድተዋል።
ፍንዳታው የተከሰተበት ቦታ ከአፍዴራ እስከ ዳሎል 80 ኪሎ ሜትር ገደማ የሚሰፋው የኤርትዓሌ የእሳተ ገሞራ ሰንሰለት አካል ነው። በተደጋጋሚ ስሙ የሚነሳው ኤርትዓሌ፣ ሐይሊ ጉብ እና አሊ ባጉ ወይም አማይቶሌ የተባሉ እሳተ ገሞራዎች የሰንሰለቱ አካል ናቸው።
ኤርትዓሌ የሚገኝበት አካባቢ ወትሮም የእሳተ ገሞራ እንቅስቃሴ ተለይቶት አያውቅም። “ኤርትዓሌ አመቱን ሙሉ የማያንቀላፋ” እንደሆነ በሰመራ ዮኒቨርሲቲ የሥነ-ምድር ተመራማሪው ኖራ ያኒሚኦ ይናገራሉ። “ከሶስት ወይም ከአራት ወራት በፊት ኤርትዓሌ አካባቢ ላይ ተመሣሣይ አይነት ነገር ተከስቶ ነበር” የሚሉት ኖራ ያኒሚኦ “ከኤርትዓሌ በስተደቡብ በኩል ከ10 እስከ 13 ኪሎ ሜትር ርቀት በምትገኝ ቦታ ላይ እንፋሎት ይወጣ ነበር” በማለት አስረድተዋል።
እንፋሎት የወጣበት ቦታ አሁን እሳተ ገሞራ የፈነዳበት መሆኑን የገለጹት የሰመራ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ምድር ተመራማሪው ወደ ሰማይ የተወነጨፈው አመድ የአፍዴራ፣ በርኻሌ እና ከአፋር ክልል ውጪ የተወሰኑ የትግራይ አካባቢዎችን እንደሸፈነ ገልጸዋል።
በአካባቢው ከጥቂት ወራት በፊት የቀለጠ አለት ወደ ምድር ያፈሰሰ ክስተት ቢፈጠርም የአሁኑ ፍንዳታ ግን በኤርትዓሌ ከተለመደው የተለየ ነው። “ኤርትዓሌ ላይ እንደዚህ አይነት ነገር ይከሰታል ተብሎ የሚጠበቅ ነው” የሚሉት ኖራ የቀለጠ ዓለት ወደ ገጸ ምድር ወጥቶ የሚፈስበት ወደ ሰማይ የማይወነጨፍ (non explosive eruption) ከዚህ በፊት ይከሰት እንደነበር ገልጸዋል። ይሁንና አሁን የተከሰተው “በጣም ከፍተኛ አመድ” ወደ ሰማይ ያጓነ (explosive eruption) ሆኗል።
ባለፈው እሁድ እሳተ ገሞራ የፈነዳበትን ቦታ የሥነ-ምድር ጥናት ባለሙያ እና አገር አስጎብኚው እንቁ ሙሉጌታ ከአመት በፊት እንደተመለከቱት ይናገራሉ። እንቁ ወደ ቦታው ያቀኑት ከሌላ የእሳተ ገሞራ ተመራማሪ ጋር ነበር።
በሐይሊ ጉብ እሳተ ገሞራ እንፋሎት እና ጋዝ ሲያወጣ መመልከታቸውን ለዶይቼ ቬለ የገለጹት እንቁ ሙሉጌታ ከባልደረባቸው ጋር “ብዙ ነገሮችን” በማንበብ እና “እዚያው ሁለት ቀናት በማደር አንዳንድ ምርመራዎችን በማካሔድ፤ አሁን ወይም ወደፊት እሳተ ገሞራ ፍንዳታ ሊከሰት” ይችላል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰው ነበር።
ይሁንና በእሳተ ገሞራው “እየተጥመለመለ በአየር ላይ ወጥቶ በንፋስ አማካኝነት ቀይ ባሕርን አቋርጦ የመን እና ሰሜናዊ ሕንድ” የሚጓዝ አመድ ይከሰታል ብለው አልጠበቁም።
በፍንዳታው እስከ 14 ኪሎ ሜትር ወደ ሰማይ የተጉተለተለው ብናኝ ቀይ ባሕርን ተሻግሮ በየመን፣ ኦማን፣ ሕንድ እና ሰሜን ፓኪስታን እንደደረሰ በፈረንሳይ የሚገኘው ቱሉዝ የእሳተ ገሞራ አመድ ጉዳይ አማካሪ ማዕከል አስታውቋል።
በአመዱ ምክንያት ኤየር ኢንዲያ የተባለው የሕንድ አየር መንገድ ትላንት እና ዛሬ 11 በረራዎች መሰረዙን አስታውቋል። አክሳ የተባለ ሌላ አየር መንገድ ጅዳ፣ ኩዌት እና አቡዳቢን ወደ መሳሰሉ የመካከለኛው ምሥራቅ መዳረሻዎች በሁለቱ ቀናት የነበሩትን በረራዎች ሰርዟል።
የአሜሪካው ስሚዝሶኒያን ተቋም ዓለም አቀፍ እሳተ ገሞራ ጥናት ማዕከል ከበረዶ ዘመን መጨረሻ ወዲህ ባሉት 12,000 ዓመታት በሐይሊ ጉብ ፍንዳታ እንዳልተከሰተ አስታውቋል። “የባሕር ሥር እሳተ ገሞራ” በአሁኑ ሐይሊ ጉብ ተከስቷል ተብሎ በሚታመንበት ወቅት አካባቢው በውኃ የተሸፈነ እንደነበር የሥነ ምድር ተመራማሪው እንቁ ሙሉጌታ አብራርተዋል።
የሐይሊ ጉብ እሳተ ገሞራ የፈነዳው በአፋር እና ኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙ አካባቢዎች አምና በተደጋጋሚ ከተከሰቱ የመሬን መንቀጥቀጦች በኋላ ነው።
አርታዒ ነጋሽ መሐመድ























